የኬንያው ፕሬዝዳንት ቆይታ ውጤታማ ነበር – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ቆይታ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከተሳተፉበት የቴሌኮም የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በጥቅሉም ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በትግራይ የሚከናወነውን የመልሶ ማቋቋም ሥራ በተመለከተ ገለጻ እንደተደረገላቸውም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በውይይቱም በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ፣ የጤና፣ ትራንስፖርት፣ የስልክ አገልግሎትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በተመለከተ ማብራሪያ መሰጠቱን አስረድተዋል።

በተጓዳኝም በክልሉ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ያለበት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መሰጠቱን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

ከዚህ ተቃራኒ የሚሰራጩት የሃሰት ዘገባዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን በመድረኩ አጽንኦት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተወካዮች በትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ እንዲረዱ ተደርጓል ነው ያሉት።

ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተም ባለፈው ሳምንት በችግር ላይ የነበሩ 1 ሺህ 136 ዜጎች ከሳኡዲ አረቢያ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮችም በአገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለተወከሉበት አገራት ትክክለኛ መረጃ እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአንዳንድ አገራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገቢ ከዲያስፖራው የማሰባሰብ ሥራ መሰራቱን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

Ena

Leave a Reply

%d bloggers like this: