በጉጂና ቦረና የኦነግ ሸኔ ሃይል ላይ እርምጃ ተወሰደ፣ ሕዝብ ጥቆማ በማድረጉ ሃይሉ ተከቦ ማምለጥ አልቻለም ነበር

በጉጂና በቦረና ዞን በተደረገው ዘመቻ ዘጠና አምስት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። ይህንኑ ዜና ተከትሎ የክልሉ መሪ አቶ ሽመልስ ” የቦረና ልማት ወደ ኃላ መቀልበስ በማይችልበት ደረጃ ተገንብቷል በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቁጥር ያልተገለጹ መቁሰላቸውንና 95 የሸኔ ተጣቂዎች መገደላቸውን ይፋ ያደረገው የክልሉ ፖሊስ ከመንግስት ወገን የተከፈለ ዋጋ ስለመኖሩ አልተናገረም።

ታጣቂዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ብዛት ያላቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ያሰራጨው ዜና ያስረዳል።የሸኔ ታጣቂዎች ሲጠቀሙበት የነበሩ ሞተር ሳይክሎችና የተለያዩ ቁሳቁሶችን መያዝ መቻሉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ ለዘመቻወ ስኬት ህዝቡ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርቧል።

ታጣቂዎቹ ሊወስዱ ያሰቡትን ጥቃት ከመፈጸማቸው በፊት በህዝብ ጥቆማ ባሉበት ተከበው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ታውቋል። ለዚህም ይመስላል ፖሊስ ሕዝብ በጥቆማ ስላደረገው ትብብር አድናቆቱን ሰጥቷል። ይህ ታጣቂ ሃይል ከምዕራብ ኦሮሚያ ተንቀሳቅሶ ወደ ቦረና ያመራ መሆኑንና ምርጫውን ተከትሎ እክል ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል።

የጉጂ አባገዳ መንግስትን በመቃወም በጫካ ውስጥ ያሉትን ሃይሎች ክፉኛ የሚያወግዙና በአካባቢያቸው እጅግ የተወደዱ ናቸው። ” እኛ ስንፈናቀል የት ነበራችሁ” ሲሉ እነ ጃዋርን ሳይቀር እንደማያውቋቸው በገሃድ የተናገሩ መሆናቸው አይዘነጋም።

ዜናውን ተከትሎ መሪያቸው ጃልመሮም ሆነ ኦነግ ሸኔ ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጡም። ይህ ሃይል በተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሰ አንዳንዴም ታጣቂዎችን፣ በብዛት ሰላማዊ ዜጎችን የሚያጠቃ በመሆኑ ” አሸባሪ ” ተብሎ ከትህነግ ጋር የተፈረጀ ነው።

ከዚህ ኦፕሬሽን ጋር ይያያዝ ወይም አይያያዝ በግልጽ ባይናገሩም “የቦረና ልማት ወደ ኃላ መቀልበስ በማይችልበት ደረጃ ተገንብቷል በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለቦረና ህዝብ ተናገረዋል። የሕዝቡ ታላቅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመልክተው የለውጡ መንግስት በትኩት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። አያይዘውም ስለ ዩኒቨርስቲው ምርቃት ገልጸዋል።

“የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለውጡ መንግስት በመደበው በጀት የቦረና ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱ የብልፅግና ጅማሮ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ቀጣዩ ምዕራፍም በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ተደምጠዋል።

፡፡በክልሉ ከተገነቡ 7 አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በቦረና ዞን የተገነባ ሲሆን ተማሪዎች በሙሉ ትኩረት እውቀት እንዲገበዩ ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ፡፡

እውቀት የሁሉም መሰረት በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ግንባታውን በማስጀመር አጠናቀቀን እናስመርቃለን በቅርቡ የቦረና አየር ማረፊያ ግንባታን በይፋ እናስጀምራለን ብለዋ ፕሬዝደንት ሽመልስ፡፡

ህዝቡን በኢኮኖሚ ለማሳደግም በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡የዴሞክራሲ መሰረት የሆነው የገዳ ስርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገርም ሌት ከቀን ይሰራል ብለዋል፡፡ከኬንያ የመጣችሁ ልዑክ ቡድን የደስታችን ተካፋይ በመሆናችሁ እናመሰግናለን፤ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር የምታከናውኑት ጠንካራ ስራ የሚያኮራ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል አቶ ሽመልስ፡፡

የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዎች ለማስተሳሰር የመሰረተ ልማቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡የኦሮሞ ህዝብ አንድነትን ማጠናከር የኢትዮጵያን ብሎም ምስራቅ አፍሪካን መገንባት በመሆኑ የኃላ ቀር አመለካከቶችን ለመግታት በጋራ እንስራ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ለቀድሞው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀ/ማሪያም ደሳለኝ ለቦረና ዩንቨርሲቲው ግንባታ እውን መሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦ የወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡በተጨማሪም ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ወይፈን እና ጊደር ተበርክቶላቸዋል፡፡ እንዲሁም ለቦረና ዩንቨርሲቲ ግንባታ እውን መሆን የበኩላቸውን ላበረከቱ አካላት ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡ ሲል የዩኒዘርስቲውን ዜና የዘገበው ኦቢ ኤን ነው።


DONATE US – ቢረዱን አስፍተን ለመስራት አቅም ይፈጥሩልናል

About topzena1 2659 Articles
A journalist

Be the first to comment

Leave a Reply