በቤተሰብ ሀዋላ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር መግባቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ

ባለፉት 11 ወራት በቤተሰብ ሀዋላ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ሰኔ 9 ቀን የሚከበረውን የቤተሰብ የሀዋላ ቀን በማስመልከት በተካሄደው መርሃ ግብር የውጭ ሀዋላ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሀንስ ሊቁ እንደገለፁት፤ ባለፉት 11 ወራት ውስጥ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ችሏል።

ባንኩ የሀዋላ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ዮሀንስ፤ የጥቁር ገበያ መስፋፋት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለስራው ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ገልፀዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው ከፍ ያለ ገንዘብ እንደሚልኩ ያስታወቁት አቶ ዮሀንስ፣ በህጋዊ መንገድ የሚላከው የገንዘብ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ፤ ከናይጄሪያ፣ ኬኒያና ጋናን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር ስትወዳደር ዝቅተኛ የውጪ ምንዛሬ ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ናት ያሉት ኃላፊው፤ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለመጨመር የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩትን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚያስችሉ የማስተዋወቅ ስራ ማከናወኑንም ጠቁመዋል።

በየአመቱ የሚከበረውን የሀዋላ ቀንን ማክበር ያስፈለገው ‹‹በሀገር ልማት ውስጥ ወሳኝ ቦታ ያለው የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በመደበኛው የባንክ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ መልእክት የማስተላለፊያ መድረክ በማስፈለጉ እንደሆነ ገልፀዋል።

ባንኩ ለላኪና ተቀባዮች ቀላል፣ ከአደጋ የፀዱና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም የጠቆሙት አቶ ዮሀንስ፣ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግዢ መፈጸሙንም አስታውቀዋል።

በሀዋላ መልክ ከውጪ ለታዳጊ ሀገራት የሚላከው ገንዘብ ሀገራቱ ከለጋሾች ከሚያገኙት ይፋዊ የልማት እርዳታ በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥ ጥናቶች እንደሚያሳዩ እንዲሁም እኤአ በ2020 ዝቅተኛና መካለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት 540 ቢሊዮን ዶላር ከሀዋላ ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

በሀዋላው አማካኝነት በሚላከው ገንዘብ ከ200 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከ800 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ እንደሚልኩም ጠቁመዋል።

የቤተሰብ የሀዋላ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ እኤአ ከ2015 ዓ.ም እየተከበረ እንደሚገኝ በወቅቱ ተገልጿል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሰኔ  7/2013

Leave a Reply