ከባድ ወነጀል ፈጽመው ሱዳን የተሸሸጉትን ጨምሮ ከውጭ ተረክቦ ለህግ ለማቅረብ ከጫፍ መደረሱን ፌ/ፖሊስ አስታወቀ

co, zelalem mengeste

ኮሚሽኑ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ከሚፈለጉበት ሀገር ለማምጣት ከኢንተርፖል ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል። የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ እንዳሉት ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የተደበቁ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

“በቅርቡ ከጅቡቲ መንግስት ጋር በተደረገ ውይይት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፈው ሰጥተውናል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በሱዳን፣ በኬንያ እና በሌሎች ሀገራት ያሉ ተፈላጊ ተጠርጣሪዎችን ለመረከብ ውይይቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት በመሸሽ በስደተኛ ጣቢያዎች ያሉትንም ሆነ ከዚያ በፊት የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈጸም በሌሎች ሀገራት የተደበቁትን ለመያዝ ከሚኖሩባቸው ሀገራት እና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ወይም ኢንተርፖል ጋር በይፋ ውይይት እየተደረገ ነው።

“ተጠርጣሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል ሀገራት እየተባበሩን እና ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩን ነው” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም፣ ሀገራቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያስቀመጧቸው እርምጃዎች ስራቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ነግረውናል። ኮሮና ቫይረስ ባይከሰት ኖሮ እስካሁን በብዙ አገራት ያሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ይረከቡ እንደነበርም ገልጸዋል።

ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እና እየተያዙ መሆኑንም ዘላለም መንግስቴ አመልክተዋል።ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በሁለት መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያእንደሚያስገቡ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም አንደኛው እንደ አዋጭ የንግድ ዘርፍ በማየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሀገርን ለማፍረስ በማሰብ ነው።

“ኮሚሽኑ የመሳሪያ ዝውውሩን ለማምከን ተጠርጣሪዎችን እየተከታተለ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እያደረገ ነው። የጦር መሳሪያዎቹ ከሚመጡባቸው ከቱርክና ሌሎች ሀገራት ጋር በመምከር ላይ ነን” ሲሉን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች በሱዳን፤ኬንያ ቱርክ እና ሌሎች ሀገራት እንዳሉ ስለሚታወቅ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ከሀገራቱ ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።ከዚያ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳድር አዋጅ መሰረት የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።ምዝገባውን ለመፈጸም የጦር መሳሪያ ዝውውር አዋጅ ደንብ እና መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ በቅርቡ ምዝገባው ይጀመራል ብለዋል። ለዜናው ግብአትነት አላይን የሚባለውን ድረ ገጽ ተጠቅመናል።

Leave a Reply

%d bloggers like this: