ሠላም ሚኒስቴር ያስጠናው “ሕዝቡ ምን ይላል” ጥናት ይፋ ተደረገ- ‘እኔ አውቅልሃለው’

ሠላም ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ያስጠናውን “ሕዝቡ ምን ይላል” ጥናት ይፋ አድርጓል።

የሠላም ሚኒስትሯ ጥናቱ ይፋ በሆነበት መርሃ ግብር ባስተላለፉት መልዕክት ዘመናትን የተሻገረው ሕዝብን ‘እኔ አውቅልሃለው’ የማለት የተሳሳተ እሳቤ ሊታረም ይገባል።

የ’እኔ አውቅልሃለሁ’ እሳቤ የሰፈነው የሕዝብን ጥያቄ አድምጦ ፈጣንና ውጤታማ ሳይንሳዊ ምላሽ የሚሰጥ የአሰራር ስርዓት ባለመዘርጋቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም መንግስታት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም የሕዝቡን ጥያቄ “አኔ አወቅልሃለሁ” በሚል በራሳቸው መንገድ ምላሽ ለመስጠት መሞከራቸው ውጤት አላመጣም ብለዋል።
ይህን አሰራር ለማሻሻል ሚኒስቴሩ ላለፉት 10 ወራት አይ.ዲ.ኢ.ኤ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ጋር ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል።

ጥናቱ የሕዝቡን ችግሮች በአግባቡ ለይቶ ሳይንሳዊ መፍትሔ የሚያገኙበትን ዘዴ የሚያመላክት መሆኑንም አብራርተዋል።

ለሠላም ጠንቅ የሆኑ መዋቅራዊ አሰራሮች እንዲስተካከሉ የሚያስችል ይሆናልም ብለዋል።

የሕዝቡን ችግሮች በመፍታት የመወሰን አቅሙን መደገፍ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ሳይንሳዊ ምላሽ የሚሰጠው አሰራር የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ችግሮችን ስርዓት አበጅቶ መመለስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ በተካሄደው ጥናት ከኅብረተሰቡ በብዛት የተነሱት የስራ አጥነት፣ የሠላም፣ የመኖሪያ ቤትና የጤና አገልግሎት ችግሮች መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

በየጊዜው የሚከለስ መሆኑ በተገለፀው ጥናት በመላ አገሪቷ የሚገኙ ከ3 ሺህ 200 በላይ ዜጎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ጥናቱ ይፋ በተደረገበት መርሃ ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የጥናቱ መካሄድ መልካም መሆኑን ገልጸው፤ አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። ENA

Leave a Reply