ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ እናንተም አትፀፀቱም!

መቀመጫውን ብሪታኒያ ያደረገው ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር ኤፕሪል 11/2016 ባስነበበው ፅሁፍ ባራክ ኦባማ “በሊቢያ ላይ ያደረግነው ጣልቃ ገብነት የፕሬዝዳንትነት ዘመኔ አስከፊው ስህተት ነው::” ሲሉ መናዘዛቸውን አስነብቦ ነበር።

አሜሪካ በሊቢያ የተከሰተውን የውስጥ ችግር እኔ እፈታዋለሁ በሚል ሰበብ ከአጋሮቿ ጋር በሉዓላዊት ሊቢያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት የወሰደችውው እርምጃ እንኳንስ የሊቢያን ችግር ሊፈታ ይቅርና ሀገሪቱ እንድትፈርስ፣ ዜጎቿ ለሞት፣ ስደትና እንግልት እንዲዳረጉ አካባቢውም አይ ኤስ አይ ኤስን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች መፈልፈያ እና መራቢያ እንዲሆን አድርጎት አረፈው።

በፈረንጆቹ ማርች ወር 2011 ላይ በአሜሪካ አስተባባሪነት በኔቶ መራሹ ጦር በተወሰደባት ወታደራዊ እርምጃ ሊቢያ እንድትፈራርስ የሚያደርጋት ውሳኔ እውን እንዲሆን የአሜሪካ ሚና ጉልህ ነበር።በአንዲት ሉዓላዊት ሀገርና ህዝብ ላይ ይህ ዘግናኝ ድርጊት ተፈፃሚ እንዲሆን በነጩ ቤተመንግስት ውስጥ ሆነው ውሳኔ ያስተላለፉት ደግሞ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማ ናቸው።

እናም ውሳኔያቸው ሊቢያን አፈራርሶ፣ የዜጎቿን ህይወትና ንብረት ነጥቆ፣ የመሪዋን አስክሬን ከጉድጓድ ውስጥ አስጎትቶ ወዘተ ካለፈ ከአምስት አመታት በኋላ “ያኔ ያሳላለፍኩት ውሳኔ የፕሬዝዳንትነት ዘመኔ ትልቁ ስህተት ነበር” ሲሉ ስላቅ የሚመስል ኑዛዜ ተናዘዋል።የኦባማ እና አጋሮቻቸው ውሳኔ ሰለባዎች ይህን የኦባማ ስላቅ ሲሰሙ “እና ምን ይጠበስ ሚስተር ኦባማ?” ቢሉ አይገርምም።

የኦባማ ‘ተሳስቼ ነበር’ ኑዛዜ ለሊቢያ ህዝብ ምኑ ነው? በእነ አሜሪካ እሳት የተቀጠፉ ሊቢያዊያንን ህይወት ይመልስ ይሆን? የፈራረሰችውን ሊቢያ መልሶ ይገነባላቸዋልን?ኑዛዜው የመሪያቸውን አስክሬን እንደ ውሻ ከጉድጓድ ጎትቶ እያወጣ የሚያሳይ ቪዲዮ በመላው አለም በማሰራጨት ያደረሰባቸውን የልብ ስብራት እንዲጠገን ያደርግ ይሆን? በጭራሽ!ኦባማ በፀፀት መግለጫቸው የኛ ጣልቃ መግባት በሊቢያ ያመጣል ብለን የገመትነው ቀርቶ ተቃራኒው በመሆኑ ሊቢያ ላይ የሆነው ሊሆን መቻሉን አስረድተዋል።

የሚገርመው ግን የዓለም ታሪክ፣ የሊቢያ ህዝብና እና የገዛ ህሊናቸው ራሱ ይቅር ከማይሉት የኦባማ/አሜሪካ ስህተትና የዘገዬ ፀፀት መማር የማይፈልጉ አገራትና መሪዎቻቸው መሰል ስህተቶችን ለመድገም ዛሬም ጥረት ማድረጋቸው ነው።

“ኢትዮጵያ ጠዋት ምን መብላት እና ማታ ምን ለብሳ ማደር እንዳለባት ሊነግሩን ይፈልጋሉ።” እንዲሉ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በውስጥ ጉዳያችሁ ገብተን ካላገነፋን የሚሉ ሀገራትን ዛሬ ላይ መመልከት አስገራሚም አሳፋሪም ነው።ሽብርና አሸባርነትን እፀየፋለሁ ብሎም አጠፋለሁ የሚሉ ሀገራት የአንዲት ሉአላዊት ሀገርን የመከላከያ ሰራዊት በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ‘አሸባሪ’ ተብሎ ከተፈረጀ አሸባሪ ቡድን ጋር በጠረጴዛ ዙርያ ተደራደሩ ሲሉ መስማትን የመሰለ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ?

በእርግጥ እነዚህ ሀገራት እና መሪዎቻቸው የኦባማን ስህተት ለመድገም እየዳዳቸው ቢሆንም እኛ ኢትዮጵያዊያንም እንላለን “ኢትዮጵያም አትፈርስም እናንተም አትጸጸቱም”፤“በውጭ ጣልቃ ገብነት የምትፈርስ ኢትዮጵያ ስለሌለች ኢትዮጵያን አፍራሳችሁ ነገ የምትፀፀቱበት እድል አይኖርምና የውስጥ ጉዳያችንን ለኛ በመተው ወደራሳችሁ የውስጥ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጉ!

”እነዚህ ሀገራት ያላስተዋሉት ነገር የኢትዮጵያ እና ሊቢያ ከባቢ አየርና አፈር እንደሚለያዩ ሁሉ ኢትዮጵያዊያን እና ሊቢያዊያን የተለያየ ታሪክ እና ማንነት እንዳላቸው ነው፡፡አንድ ኢትዮጵያዊ ምንም እንኳ በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ቢሆን፣ የቱን ያህል መንግስትን ቢቃወም አገሩን ለማፍረስ የመጣን አካል እንኳን በደህና መጣህ ብሎ የሚቀበልበት ሞራልም ዝግጁነትም እንደሌለው መዘንጋት የለባቸውም።በሌላ አገላለፅ ኢትዮጵያዊያን በህይወት ቆመው ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የምትፈርስበትን ሴራ በማሴር ቢጠመዱም የምስራቅ አፍሪካዋ ፈርጥ ኢትዮጵያ ግን በየቀኑ በሚባል ሁኔታ አዳዲስ ተአምራትን እየሰራች ጠላቶቿ ኢትዮጵያን ለቀቅ በማድረግ በውስጣዊ ችግሮቻቸው ላይ እንዲያተኩሩ ትምህርት መስጠቱንና ልማቷን ማፋጠኑን ተያይዘዋለች።ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌትና ቀጣዩን ምርጫ አሳክታ የጀመረችውን ወደ ቀደመ ከፍታዋ የመመለስ ግስጋሴ የሚገታ ምንም ሀይል የለም።

በታሪክ አጋጣሚ ታላላቅ ሀገራትን የመምራት እድል ያገኛችሁ መሪዎች ሆይ የምትመሩት ሀገርና ኢትዮጵያ ለዘመናት የገነቡትን ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚያጠናክሩ እና ወደ ላቀ ደረጃ በሚያደርሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ብታደርጉ ለሁለቱም ወገኖች የሚበጅ ይሆናል።ለዘመናት በአብሮነት የዘለቀውን የሀገራትን ግንኙነት ከማስቀጠል ይልቅ መልካም ግንኙነቱን ለመናድ መሯሯጥ ታሪክ ይቅር ለማይለው ስህተት እና ጸጸት ስለሚዳርግ ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየትና መያዝ ያስፈልጋል።የኢትዮጵያ ህዳሴ በህዝቦቿ ጥረት እውን ይሆናል!ቸር ይግጠመን!

 በነስረዲን ኑሩ

አስተያየቱ የጸሃፊው ብቻ ነው። አንባቢያችን አቶ ግሩም ከዋልታ ላይ እንዳገኙት ጠቅሰው ከላኩልን

DONATE US – ቢረዱን አስፍተን ለመስራት አቅም ይፈጥሩልናል

About topzena1 2659 Articles
A journalist

Be the first to comment

Leave a Reply