ʺየእማዬ እምባ አልታበሰም፣ የልቧ ስብራት አልታደሰምʺ

የሚወዱትን የአካልን ክፋይ እንደመነጠቅ፣ በግፍ ዘመን እንደመማቀቅ፣ ሬሳ አጠገብ አስቀምጦ እንደመሳቀቅ ምን የከፋ ነገር ይኖር ይኾን? የሞት ጥላው ከባድ ነው። ልብ ይሰብራል፣ ያከሳል፣ ያጠቁራል፣ ብቻን ሲኾኑ ደግሞ የበለጠ ይከፋል። ኢትዮጵያውያን ስሪታቸው ሀዘንና ደስታን መጋራት ነው። ተላቅሶ መቅበር፣ እልል ብሎ መዳር ያውቁበታል። ይህን ያላደረገ ኢትዮጵያዊ ውግዝ ነው፣ ከሰውም የተለዬ ነው። በጋራ ደስታ መደሰት፣ በጋራ ለቅሶ ማልቀስ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ ነውና።

ፀሐይ በሌላው ዓለም ብርሃኗን ከልክላ በዚያ አካባቢ ብቻ የምታበራ ይመስላል፣ ጨረሯ ምድርን እያመሳት ነው። ወበቁ ያስጨንቃል። የነጭ ወርቁ ምድር ማዕበል እንደረጋለት ውቅያኖስ ተኝቷል። ፀሐይ ያን ሁሉ በትሯን የምታሳርፍበት ምድር ውበቱን አልተቀማም፣ አረንጓዴነት አራቀውም። በተስማማው ምድር አድማስ ሲመለከቱ ሰማይ ምድርን ተመርኩዟት የቆመ፣ ምድርም የተቋጨች ይመስላል። በአካባቢው አቀማመጥ፣ በሰው ፍጥነት፣ ጀግንነት፣ እንግዳ ተቀባይነት ከሁሉም በላይ ጥንቁቅነት አግራሞቴ ከፍ ብሏል። “ሀገራችን ጎንደር ወልቃይት ጠገዴ፣ ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጓንዴ” እንዳለ ከያኒው ማረስ፣ በሰፊ አውድማ ማፈስ፣ አልሞ መተኮስ፣ ጠላትን በአሻገር መመለስ መታወቂያው ነው። ድንቅ ሕዝብ ውብ ሀገር። በኢትዮጵያ ይኮራሉ፣ እርሷም በእነርሱ ትኮራለች፣ ኢትዮጵያ በዚያ አካባቢ አያሌ ጀግኖችን ወልዳለች፣ አያሌ ጀብዱም ፈፅማለች፣ ከሰንደቅሽ በፊት እኔን ያድርገኝ እያሉ በተዋደቁላት ልጆቿ አብዝታ ትኮራለች። አሁንም በዚያው ምድር ጀግና ወልዳለች፣ በብቃት ትጠበቃለች፣ ነገም ትወልዳለች እንደተጠበቀችና እንደ ተከበረች ትዘልቃለች።

አዳሬ ከተከዜ ዳሯ እመቤት፣ ከበረሃዋ ንግሥት ሑመራ ነበር። ሙቀቷ የሚያስጨንቀው ሑመራ ውበቷ ሁሉንም ነገር ያስረሳል። ሰማይ ብርሃኑን እየዘረጋ ነው፣ ምድር የጨለማ ካባዋን እያወለቀች ነው። ሑመራ የጀንበርን መዝለቅ ተከትላ በጠዋቱ መሞቅ ልትጀመር ነው። ከዚያ በፊት ግን እግሬ ያርፍባት ዘንድ የተመኘኋት ከተማ ነበረችና ወደዚያው ለመሄድ አቀናሁ። ከሑመራ ወደ ደቡብ ምዕራብ ንፍቅ ፊቴን አዙሬ ገሰገስኩ። መዳረሻዬ የማደርጋት ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልካም ትዝታ የላትም። ከወራት በፊት በከተማዋ ያጠላው ክፉ ደመና የወረደው በረዶ የከፋ ነበርና ጠባሳውን በቶሎ ለመርሳት ያስቸግራል። ዳሩ ያም ኾኖ ከአለፈው ጊዜ የሚመጣው ይበልጣል እንዲሉ ሀዘናቸውን በቤታቸው አድርገው ኑሯቸውን ቀጥለዋል። ጉዞዬን ቀጥያለሁ። ጀንበር በጠዋቱ መጋረፍ ጀምራለች። የበረሃው አረንጓዴአማነት ቀንሷል። ቅጠላቸውን ያረገፉት የአካባቢው እፅዋት የሚዋጉ ይመስላሉ።

አይኔ እያማተረ ጉዞዬ ቀጥሏል። ጉዞው ረጅም አልነበረም እና መዳረሻዬ ካልኳት ከተማ ከትሜያለሁ። ከተማዋ ከወራት በፊት አባታቸውን በግፍ የተነጠቁ ሕፃናት ዋይታ አሰምተውባታል፣ እንባቸውን እንደ ዥረት እያፈሰሱ አንብተውባታል፣ እናቶች አንጄታቸው እየተላወሰ በሀዘን ማዕበል ተውጠውባታል፣ ነብስና ስጋዋ እስክትለያይ የምታቃስት ክፉ በትር የወደቀባት ነብስ በሚያሳዝን ድምፅ አቃስታበታለች፣ በዚያች ከተማ ከፉው ነገር ሁሉ ተፈፅሟል፣ ደም እንደ ወራጅ ውኃ ፈሷል፣ ያን ያዬና የሰማ ሁሉ ጌታ ሆይ ምነው ጨካኞች እንዲኖሩ ፈቀድክ፣ ሥራህ በከንቱ ሲፈርስስ ለምን ዝም አልክ፣ ከአንተ ርቀው አረመኔዎች ሲኾኑስ እንዴት ታገስካቸው፣ ለምንስ እድሜን ሰጠሃቸው፣ በግፍ ተቀልተው ወደ አንተ የመጡትንስ እንዴት ነው የምትቀበላቸው፣ የክብር አክሊል፣ የፅድቅ ዘውድ አላዘጋጀህላቸውምን፣ ገዳዮችንስ በምድር እየተቅበዘበዙ እንዲኖሩ አልፈረድክባቸውምን ይላል። ሀዘኑ ከባድ ነውና። ዘመን ሲከፋ የሚወዱትን ሰው በግፍ ያጡታል። ለብቻ እያለቀሱ፣ አንጄትን እያላወሱ ይቀመጣሉ፣ እግዚአብሔር ያፅናህ የሚል ሲጠፋ፣ ከአጠገብ ጥላ ሲታጣ ሀዘኑ ከፍ ይላል። ሰው ሲርብ ከባድ ነው። ረሃቡ ልብ ይሰብራልና። ከረሃቦች ሁሉ ሰው የማጣት ረሃብ የከፋ ነው። ዘመንን ያጨልማል፣ ደስታን ያደበዝዛል፣ ለዘላለም ያስተክዛልና።

የወያኔ የግፍ በትር ካረፈባት ከተማ ገብቻለሁ። የጥፋት መርከብ ወደብ ይሏታል ነዋሪዎቿ ማይካድራን። በዚያች ከተማ ልባቸው የተሰበረ እናት አግኝቻለሁ። ወይዘሮ የሺ ላቀ ይባላሉ። ባለቤታቸው አየነው ሙላት ይባላሉ። ለ14 ዓመታት በፍቅር ተሳስረው፣ ጎጆ ቀልሰው፣ ልጆች ወልደው ኖረዋል። አባወራው አየነው መሬት እየተከራዩ እያረሱና በሁለት እግር ተሽከርካሪ ሰርተው በሚያመጡት ገንዘብ ነው ቤተሰቡ የሚደጎመው። ትልቁ ገቢም የእሳቸው ነው።

ታዲያ የሞተር ብስክሌታቸው ሥራ በወያኔ ታጣቂዎች መልካም ፈቃድ የተመሰረተች ነበረች። ሲያሻቸው ብር ይቀጧቸዋል፣ ከፍሲል ደግሞ ሞተሯን ዘግተው ከሥራ ውጭ ያደርጓቸዋል። ለማን አቤት ይባላል። በጨለማ ዘመን ነውና የሚኖሩት አቤት የሚባልበት ዳኛ፣ እባክህን የሚባል ወዳጅ አልነበረም። ገንዘብ መውሰዱ ወይንም ሞተሯን መቀማቱ ብዙም አልጎዳቸውም ነበር። በማንነት የተነሳ የሚወርድባቸው ስድብ ግን ከሁሉም በላይ ነበር። አንጄታቸውን ያሳርረዋል። ወንድነታቸውን ይፈታተነዋል፣ “ኧረ ልጅ ማሰሪያው ኧረ ልጅ ገመዱ፣ ጎጆማ ምን ይላል ጥለውት ቢሄዱ” እንደተባለ ጎጇቸውን ጥለዋት ብን ብለው ይጠፉ ነበር። የአብራካቸው ክፋዮች ምን ይውጣቸዋል። ለ14 ዓመታት አካላቸው የኾነችው ባለቤታቸውስ የት ይወድቃሉ። በየቀኑ እርር ትክን እያሉ ዝም ይላሉ እንጂ።

“እንዳይሄድም ወልዶ፣ እንዳይቀርም ነዶ፣ እንዴት ያለው ጀግና ቀረ ተጨማዶ” እንዳለ ጃሎ ባይ አባወራው አዲስ ቀን እንደሚመጣ፣ የእኩል ጀንበር እንደሚወጣ ተስፋ ይዘው ዝም አሉ። የወያኔ የግፍ ግፍ ሥራ እየተበራከተ ሄደ። መከራው በዛ፣ የእነ ወይዘሮ የሺ ላቀ ቤተሰብም ጫናው በዛበት። መከራው ጠና። ወይዘሮ የሺ ላቀና አቶ አየነው በትዳር ዘመናቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። ወይዘሮዋ ያን ዘመን ሲያስታውሱ “ባለቤቴ በሞተሯ ከበረሃ ወደ ከተማ ከከተማ ወደ በረሃ ሰው ያጓጉዛል፣ ታዲያ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይታሰራል፣ ትራፊክ ባገኘው ቁጥር አንተ በማን ሀገር ነው የምትንደላቀቀው እያሉ ያሰቃዩት ነበር። በተለይም በአብደራፊ መስመር ቆይቶ ከመጣ ከፋኖ መረጃ ተቀብለህ ነው የመጣህ እየተባለ ይሰቃይ ነበር።” ነው ያሉኝ።

ያም ኾኖ መኖራቸው ለልጆቻቸው ኩራት ነውና ቀን ቢወጣ ከመሞት ይሻላልና ግፉን እየተጎነጩ ዝም አሉ። መልካም ጊዜ መጣ ሲባል የከፋ ጊዜ መጣ። ይሄ እንደቀድሞው ተሰድቦ መታለፍ፣ ብር መቀጣት ብቻ አልነበረም። ለዘለዓለም ሕይወትን መቀማት ነበር እንጂ፣ ወያኔ ጥጋብ ሲወጥራት ኢትዮጵያውያን የሚመኩበትን መከላከያ ነካች፣ የትዕግስት ጥግ አለቀ። የግፍ ፅዋ ፈሶ ተደፋ። በእሳት ተገረፈች። ቤተመንግሥት በዋዛ አይገኝም ነበርና ግፍ የመረረው ሁሉ ወጋት፣ አሳደዳት፣ መከራው ሲፀናባት ሽምጥ ሮጠች።

ክፉ አመል አይለቅም ነበርና ወያኔ ዝም ብላ አልሮጠችም፤ ከውልደት እስከ ሞት አምርራ የምትጠላውን አማራን እየጨፈጨፈች ትሮጥ ነበር እንጂ። የእነ ወይዘሮ የሺ ቤት በሁለት ሀሳብ ተመልታለች። የሀገር መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ እየገፋ ከመጣ ነፃነታቸውን ያውጃሉና ደስ የሚል ስሜት እየተሰማቸው ነው። ወያኔ ገፍታ ከሄደች ግን የመከራው ዘመን ሊቀጥል ነውና መጨነቃቸው አልቀረም። ብቻ ፈጣሪ የሚያደርገውን እየተጠባበቁ ዝም አሉ።

ተስፋ ያደረጓት ቀን የቀረበች ትመስላለች። ወያኔ መግፋት ሳይኾን መፈርጠጡን ተያይዘዋለችና። መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ እየገፋ ነው። የእነ የሺ ቤት ተስፋዋ እየለመለመ ነው። ወያኔ ጦርነቱን እንደምትሸነፍ እየገባት ሄደ። ከጀግናው ግንባር መቆም የማይታሰብ ኾነ፣ በመካከል የእነ የሺን ተስፋ የሚያደበዝዝ ክስተት ተፈጠረ። የወያኔ ታጣቂዎች ማይካድራን የደም ምድር ሊያደርጓት ተነሱ። ታስቦበት የተደራጀው ቡድን ንፁሃንን መጨፍጨፊያ መሳሪያውን አዘጋጀ። በከተማዋ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ሳይደርስ ጠላት ተብለው የተፈረጁት አማራዎች ለእርድ ተዘጋጅተዋል።

“ዛሬ እሞት ነገ እሞት መች አውቄው እኔ፣ ቢላ እየተሳለ ጭድ ይበላል በሬ” እንዳለ አዝማሪው የዋሁ አማራ ከገዳዩ ጋር አብሮ ነበር። የሞት ጊዜ ደረሰ። አማራዎች ተፈለጉ። ያመኑት ከዳቸው፣ ያልጠረጠሩት ገደላቸው፣ የደም ማእበል ፈሰሰ። የእናት አንጄት ተላወሰ። ከተማዋ ተጨነቀች። የግፍ ግፍ ተፈፀመ። ልጆች አለቀሱ፣ እናቶች ጭንቃቸው በዛ፣ ለማንም አቤት አይባልም። ገሚሱ ቤቱን ዘግቶ ይማፀናል። ገሚሱ የሞቱን ሰዓት ይጠብቃል። የማይካድራ ጎዳናዎች በሬሳ ተመሉ። እኒያ እየተመረጡ የሚገደሉት ንፁሃን ከጦርነቱ አስቀድሞ ገንዘብ አዋጡ፣ ለልዩ ኀይል ድጋፍ አምጡ እየተባሉም ይሰቃዩ ነበር። እምቢ ቢሉስ ማን ገላጋይ አላቸው ይሰቃያሉ እንጂ።

ወይዘሮ የሺ ያን ጊዜ ያስታውሱታል “ይገድሉናል ብለን አላሰብንም ነበር። ቤታችን ውስጥ ነበርን፣ ባለቤቴ የትም መሄድ አልቻለም፣ ይልቅ ከቤት እሳት ይለቃሉ እናንተ ውጡ አለን፣ ታጣቂዎች ግን ቤት ውስጥ እንዳትወጡ አሉን፣ ለካስ ማንም እንዳያመልጥ ኖሯል፣ እኛም ከቤት ውስጥ ነበርን፣ ባለቤቴ ልውጣ ቢል እንኳን መውጫ አልነበረውም…” ወይዘሮ የሺ ሲታገላቸው የቆዬው እንባ በጉንጫቸው ፈሰሰ። ሳግ ተናነቃቸው። እንባ የውስጥን ሀዘን ይጠርጋልና የውስጣቸውን ምሬት በእንባቸው መጥረግ ጀመሩ። የምናገረውን አጣሁና ዝም አልኳቸው። መናገር እስኪያቅታቸው ድረስ ይፈታተናቸው ነበርና ያፈናቸውን እንባ ያለ ከልካይ አፈሰሱት። እናት ስታለቅስ ከማዬት በላይ ምን ልብ የሚሰብር ነገር ሊኖር ይችላል? እንባቸው እየገነፈለ ሲሄድ ላፅናናቸው ሞከርኩ። እንደምንም ተቋቁመው ከአዕምሯቸው የማይጠፋውን ትዝታ ቀጠሉ።

“ታጣቂዎቹ በሌላ ሰፈር ሲገድሉ ቆይተው ወደ እኛ ሠፈር መጡ። ከተማው በኡኡታ እየተናወጠ ነው፣ ባለቤቴ የሚከላከልበት እጁ ላይ ምንም አልነበረውም። መሳሪያ ይቀሙ ስለነበር መያዝ አይችልም ነበር” እንባቸው እየባሰበት መጣ። የተረበሸው ስሜታቸው ያቺን ክፉ ቀን ትናገራለች። የእንባ ማዕበል ይዟቸው ሄደ። የልባቸው ሀዘን ተፈታተነኝ። ይህ ሀዘን ልጆቻቸውን እና ቤታቸውን ባዩ ቁጥር እንደሚብስባቸው ሳስብ ደግሞ የበለጠ ጨነቀኝ። እንደምንም ታግለው ቀጠሉ “ትልቋ ልጄ አሥር አመቷ ነበርና ትግርኛ መናገር ትችል ነበር፣ ገዳዪቹ ቤት ውስጥ ሲገቡ ‘አባቴን ተውልኝ፣ እባካችሁ አባቴን ተውልኝ’ አለች አልሰሟትም ነበር። ይባስ ብሎ እየተሳደቡ አመናጨቋት። እኔም ለመንኳቸው። እንኳን ሊሰሙኝ ሊገድሉኝ ፈለጉ። አሁን ዝም በይ። የልጆችሽ ቀንም እየጨለመ ነው። ነገ ይገደላሉ፣ አሁን ወንዶችን እንጨርስ አሉ፣ ባለቤቴን በገጀራና በፋስ ከተከቱት” የአሁኑ አለቃቀስ የተለዬ ነው። እንባቸው በመንታ በመንታ ወረደ።

“ጎባጣ ኑሮዋን የሚያቃናው አጥታ

ታለቅሳለች ዛሬም በመንታ በመንታ” እንዳለ ከያኒው እንባቸውን በመንታ በመንታ ለቀቁት።

እኔ ይህን በመስማቴ የዘገነነኝ የ14 ዓመት የትዳር አጋራቸው ሲገደሉ ያዩት እናት ምን እንደ ተሰማቸው ለማሰብ ከባድ ነው። ከሁሉም በላይ ከእግራቸው ስር ተወሽቃ እባካችሁ አባቴን ተውልኝ እያለች ስትማፀን የነበረችው የአሥር ዓመቷ ሕፃን እና በወቅቱ 2 ዓመት ከ6 ወር የነበረችው ታናሿ ብላቴና መቅበዝበዝን ሳስብ ውስጤ ተፈተነ። ምን አይነት ስነልቦና ይዘው እንደሚያድጉ ሳስብ መንፈሴ ተረበሸች። እውን ፈጣሪ ይህን አይቶ ዝም አለን። የፍርድ ቀኑስ እንዴት አልቸኮለችም። ፀሐይስ ለምን ብርሃኗን አልከለከለችም፣ ምድርስ ለምን አልተንቀጠቀጠችም፣ የነፋስ አውታሮችስ ለምን ምድርን አላጠፏትም አልኩ በልቤ።

አቤቱ ከአፅናፍ አፅናፍ በተዘረጋው ዓለም የፍጥረታትን ክፋት እያየ ዝም የሚለው አምላክ ምን ያክል ቻይ ነው። ምን ያክልስ ሩሕሩሕ ነው። እንደ ምድር ክፋት ቢኾን መኖር ባልነበረ ነበር። ሲማፀኗቸው ምን ይሏቸው እንደነበር ሲያስታውሱ “ለአማራ ምንም አይነት ርህራሄ የለንም ይሉናል፣ ከእኛ ቤት ለሥራ የመጣ ሌላ ልጅ ነበር እርሱንም ገደሉት፣ ከዚያ በኋላ የምኾነውን አጣሁ፣ ማንም የሚያግዘን አልነበረም። አድኑን አልን የሚያድነን አልነበረም። ሁለት ሬሳ ወደቀብኝ፣ መንገዱ ሁሉ ሬሳ ሆኗል።” መከረኛዋ እናት ሁለት ሕፃናትን ታቅፈው፣ ሁለት አስከሬን ከፊታቸው ላይ ጥለው ሰማይ ተደፍቶባቸው፣ የመከራ ካባ ወርሷቸው በአንድ ቤት ውስጥ እያለቀሱ ቀሩ።

“አይነጋ የለም ነጋ፣ ጠዋት ሴቶች ይገደላሉ ስለ ተባለ ፈራን፣ ልጆቼን ይዤ ወደ ቤተክርስቲያን ሄድኩኝ፣ ሌሎችም ሄዱ፣ በቤቴ ግን አስከሬን ነበር፣ እንዴት ብዬ አነሳቸዋለሁ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥም ተሰባስበን ይገደሉ እየተባልን ነበር፣ በላያቸው ላይ ፈንጅ ይጣል ይሉ ነበር፣ እድሜ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ደረሱልን፣ ታጣቂዎቹ ሮጠው ጠፉ” ነው ያሉኝ። ልዩ ኀይል ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ የወዳደቀው አስከሬን መነሳቱን ነው ያስታወሱት።

የነ የሺ ቤት በሀዘን ድባብ ተመላች። ጭንቅም ኾነ። የመከራውን ዘመን በትዕግስት አልፈው መልካም ዘመን ሲጠባበቁ የነበሩት ተስፈኛ አባት ሲኖሩላቸው የነበሩ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው አሸለቡ። ላይመለሱ ተሰናበቱ። “አሁን ላይ ሰላም ነን። ነገር ግን የሀዘኑ ጥላ አልርቅ ብሎናል፣ የቤታችን መሪ ሞቷልና፣ ደጋፊም የለንም። ደጋፊ ማጣት ከሀዘን ላይ ሲጨመር ሕይወታችን ከባድ አድርጎታል። ድጋፍ እንሻለን። በቤት ኪራይ ውስጥ ነው የምንኖረው” ብለውኛል።

ከሀዘን ጥላ ያራቁት እናት አንድ አካል አንድ አምሳላቸውን አጥተው ያገኙትን ነፃነት ዳግም ለመንጠቅ የሚታትሩ አካላት ነውረኛ መኾናቸውንም ነግረውኛል። የተጎዳው የሞተው አማራ ነው፣ አሁንም እንዲጎዳ የሚፈልግ የውጭ ኀይልን እቃወማለሁ። ዳግም ሞት ይበቃናል። ለቅሷችን ሊሰማ ይገባልም ብለውኛል።

“እንዲህ ገፍቶ ገፍቶ ግፉ ሲጠራቀም

መሰብሰብ ይኾናል የዘሩትን መልቀም” እንዳለ ከያኒው የግፍ ግፍ የሠሩት ወያኔዎች የዘሩትን እየለቀሙ ነው። ያሳድዱ ነበር እየተሳደዱ ነው። አሸባሪ ይሉ ነበር አሸባሪዎች ተብለዋል። የማይጠልቅ የሚመስለው ጀንበራቸው ጠልቆባቸው፣ የድሎት ኑሮ ርቋቸው፣ ማደሪያቸውም መዋያቸውም ዋሻ ውስጥ ኾኗል። በሰለጠነ ዘመን እንደ እንስሳ ማሰብ እና ከሰብዓዊነት መውረድ መጨረሻው ይህ ነውና አይመጣም ያሉት ዘመን መጥቶባቸዋል። ፈጣሪም የበደለኞችን እንባ አይቷል። ገዳዮችን በትኗል።

ዓለም ይህን እውነት ካላዬች መቼም ቢኾን እውነት አይታያትም። ለጥቅም ብላ ይህን እውነት ከደበቀች ይዘገይ ይኾናል እንጂ እርሷም ትቀምሰዋለች። የጭቁኖች አምላክ ይፈርዳልና። ይህን ሁሉ በደል ያዬችውን ምድር ለዳግም ባርነት ትዳረግ ማለትም የግፍ ግፍ ነው። የተረፉት ይገደሉ፣ የቀረ ክፉ ሥራ ካለ ይፈፀም እንደማለት ነው። የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ነፃነታቸውን አብዝተው ይወዱታል፣ ደም ገብረው፣ ለዓመታት በግፍ መንገድ ተሻግረው ነውና ያገኙት ዳግም እንዲነጠቁ አይሹም። ስለ ማንነታችን ለመናገር ከእኛ በላይ የሚቀርብ የለምና ተውን እያሉ ነው።

ወይዘሮ የሺን ተሰናበትኳቸው፣ በጉንጮቻቸው የሚወርደው እንባቸው፣ የሚተናነቀው ሳጋቸው ግን አልተሰናበተኝም። ምስላቸውን እያመጣ ያሳየኛል። የተረበሸው መንፈሳቸው ከአጠገቤ አልርቅ ብሏል። ዓለም ሆይ ከእውነት ጋር ቁሚ፣ እንዲያ ካልሆነ አካሄድሽም ይበላሻል፤ ፍርድም ይመጣብሻል፡፡

በታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)

Leave a Reply

%d bloggers like this: