ኦነግ መንገድ ሲጠግኑ ውለው ወደ ማረፊያቸው ሲጓዙ የነበሩ አስር ሰዎች ገደለ ” መኪናቸውን ከበው ጨረሷቸው”

“መንገድ ሲጠግኑ ውለው ወደ ማረፊያቸው ሲመለሱ መኪናቸውን አስቁመው ሳያናግሯቸው ጨረሷቸው” ይላሉ ኢትዮ12 ያነጋገራቸው የዓለም ገና ዲስትሪክት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ባልደረባ። ከተረፉት የስራ ባልደረቦቻቸው እንደሰሙት ” የቤተሰብ ሃላፊዎች ነን፤ እኛ ፖለቲካ አናውቅም” ብለው ሲለምኗቸው ሊሰሟቸው እንዳልፈቀዱ አስረድተዋል።

ከሁለት ቀን በፊት በምዕራብ ሸዋ፣ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ በምትባል መንደር የተፈጸመው ግድያ እጅግ አሰቃቂ እንደሆነ ተመልክቷል። ” እኔ ኦሮሞ ነኝ” ያሉት የዲስትሪክቱ ሰራተኛ፣ ከተገደሉት መካከል የኦሮሞ ልጆች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ይህን ያሉት በዘር ለመለየት ሳይሆን የግድያው ዓላማ ለማንም ወገን ግልጽ እንዳልሆነ ለማሳየት እንደሆነ አመልክተዋል።

ባለሙያዎችና ረዳቶቻቸው በተተቀሰው ስፍራ መንገድ ጥገና ላይ እንደነበሩ፣ ስራቸውን አጠናቀው አመሻሽ ላይ ወደ ማረፊያቸው ጎሮ ሲያመሩ መኪናቸውን በሃይል ካስቆሙ በሁዋላ በሃይል በማስወረድ ፍተሻ አካሂደው ያላቸው ገንዘብና ቁሳቁስ እንደወሰዱ፣ በሁኔታው የተደናገጡት ሰራተኞች በኦሮምኛ ሳይቀር እንደለመኑዋቸው፣ አንደናው ትልቅ አባት ተንበርክከው ” እባካችሁን” ቢሉም ሰሚ እንዳላገኙ ምስክሩ ገልጸዋ።


ተጨማሪ ይህን ያንብቡ


ራሱን የኦነግ ነጻነት ጦር የሚለው ክፍል ይህ እስከታተመ ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠም። ከዲስትሪክቱ ሰራተኛ በተገኘ አድራሻ የነጋገርናቸው አንድ የጎሮ አካባቢ ነዋሪ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው እንዳሉት ግድያው በተባለው ቀን ከምሽቱ 11፡ 30 አካባቢ ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የመንገድ ጥገና ሰራተኞቹ አንዳቸውም መሳሪያ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል። ግድያው ከተፈጸመ በሁዋላ አስከሬን ለማንሳት የመንግስት ሃይሎች ወደ ስፋራው ሲመላለሱ ማየታቸውንም አመልክተዋል። ስማቸውን እንዳይገለጽ ለመጠየቃቸው ” እፈራለሁ። የልጆች አባት ነኝ። ማን ልጆቼን ያሳድጋል? ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ የቤተሰብ ሃላፊዎች ናቸው… ” ሲሉ ሳግ እየተናነቃቸው ምክንያታቸውን ገልጸዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ፣ ረቡዕ ሰኔ 09/2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ጥቃቱ መሰንዘሩን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። እሳቸው እንዳሉት ከአስሩ መካከል አንዷ ሴት ስትሆን የቀበሌው ነዋሪ ናት። በስም ጠቅሰው ጭፍጨፋውን የፈጸመው ኦነግ ሸኔ መሆኑንን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ተገኝም በተመሳሳይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ዝርዝር መረጃ ለጊዜው ተጠናክሮ እንዳልደረሰ አመልክተዋል።

ድንገት እንዲቆሙ ተደርገው የተጨፈጨፉት ሰዎች አስከሬናቸው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተልኳል። ለቤተሰቦቻቸው መርዶ ተነግሯል። አስከሪናቸውን ዓርብ ለቤተሰብ እንደሚሰጥ ቢቢሲ የጉዳዩን ባለቤቶች አስታውቆ ጽፏል።

” አስከፊ” የተባለውን ግድያ የፈጸመው ኦነግ ሸኔ መሆኑንን ሃላፊው በይፋ መግለጻቸውን ያስነበበው ቢቢሲ፣ “ይህ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል” ሲል ግድያው ስሙን በቅርቡ ከቀየረው ቡድን ጋር እንደሚገናኝ አመልክቷል።

ግድያው ከተፈጸመ ሁለት ቀን ቢሞላውም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የዓለም ዓቀፍ የመብት ተከራካሪዎችና ሚዲያዎ፣ በአዲትዮጵያ የሚገኙ የውጭ አጋእራት ኮርስፖንዳንስና ራሳቸውን አክቲቪስት ብለው የሚጠሩ አካላት እስካሁን ያሉት ነገር የለም። በኦሮሚያ የመንግስት ሰራተኞችን መግደልና ማፈን የተለመደ ቢሆንም፣ በሚደርሰው ጥፋት መጠን የተተቀሱት ወገኖች ለንጹሃን ዜጎች ህልፈት ድምጽ ሲያሰሙ አይሰማም።

ከቀናት በፊት ” የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር ላይ ከአንድ ወር በላይ መቆየታቸው ያሳስበኛል” በሚል መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።

Leave a Reply