24 ሠዓታት በውትድርና ህይወት- ምስክርነት ክፍል 8 “አይ አንቺ ሀገር ጠላትም ፣ ጀግና ልጅም አታጪም”

መኮንኑ የነበረበት ክፍል ከአድዋ ግርጌ ድብድቦ ተነስቶ ሌላ ቦታ እየሰፋ በአካባቢው መልከአ ምድር እየሰለጠነ አዲግራትና ዛላንበሳ መሀል ፈፄ የተባለ ሥፍራ ደርሷል።

በየቀኑ ዝግጅት ነው።ተዘጋጁ ተነሱ የሚሉ ትዕዛዛትም ተለምደዋል።ዛሬም ተነሱ ሲባል የተለየ ይሆናል ብሎ የገመተ እምብዛም የለም። እናም ዝግጅቱ ቀጠለ።እንደ ተለመደው የተለያዩ መገልገያዎች እንዳልነበሩ ተደረጉ። ጉድጓዶች ተደፈኑ ።ደረቅ ቆሻሻዎች ተቃጠሉ።አመዱ ጭምር እንዳይታይ አፈር ለበሰ።

በግለሰብ የታጠቀው መሣሪያ ደህንነት፣ የሚያስፈልገው የጥይት ብዛት ፣ በአጠቃላይ የመጀመሪያ ህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን ጨምሮ እራስን ችሎ በችግር ወቅት ተልዕኮ ለመፈፀም የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ያጠቃልላል።

በቡድን የሚያዙም አሉ። ቁስለኛ ቢያጋጥም ማግለያ እስትሬቸር አለ።ምሽግ ቆፍሮ ድንገተኛ ምሽግ ለመያዝ ዶማና አካፋ ከትጥቅና ስንቅ በተጨማሪ በወል የሚያዙ ናቸው።

አንድ ግለሰብ እስከ ሰላሣና አርባ ዓይነት ቁሳቁሶች ይይዝ ይሆናል።ወስፌ መርፌ ክርን ሁሉ ይጨምራል።በኋላ በተግባር እንደተረጋገጠው ሁሉም በወሻኝ ወቅት የማይተካ ሚና አላቸው። የጋራ የዝግጁነት ማቴሪያሎችም በውጊያ ወቅት የሚገጥሙ ችግሮች መፍቻ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው በግንባር የተሰለፈ በውጊያ ውስጥ ያለፈ ሁሉ ያስታውሳቸዋል።ከዚህ በላይ ዝርዝሩ አስፈላጊ አይደለም ብለውናል ተራኪያችን።

በነዚህ ቀናት በምንም ምክንያት ከክፍል ወጥቶ መንቀሳቀስ አይቻልም።ለአስፈላጊና አስቸኳይ ሥራ እንኳን ቢሆን በየደረጃው ያለ አመራር አውቆ መሆን አለበት።ሁሉም ሲቪል ሠራተኞች ለጥንቃቄ ሲባል ይሰናበታሉ።

አንዳንዴ ግን ያለታሰበ ነገር ይገጥማል።

በነዚህ ሃያ አራት ሠዓታት ጦሩ ለጉዞ መዘጋጀቱ ግልፅ ሆኗል።የበር ጥበቃ አከባቢ ድንገት ሁኔታቸው ከሩቅ እንደመጡ የሚያሳብቅባቸው ሲቪሎች ታዩ።አባት ከነሴት ልጃቸው ፣ አንድ ጎልማሳ ከእናቱ ጋር እና አንድ እናት ብቻቸውን በዚህ ሥፍራ የተገኙት ዘመድ ልጆችና ወንድሞቻቸውን ፍለጋ ነው። በዚያን ወቅት አላስችል ያላቸው ቤተሰቦች ልጃቸው ታየ ወደ ተባለበት ሁሉ ይጓዙ ነበር።

ለክፍሉ አዛዥ ተነግሮ እንዲገቡ ተደረገ።ጊዜያዊ ማረፊያ ተዘጋጀ።ግማሹ ቡና ሌላው ምግብ ማሰናዳት ጀመረ።ቡና አፍይዎችም ሆኑ ምግብ አዘጋጆቹ ወንዶች ናቸው።

ቤተሰባቸው ፍለጋ ከመጡት የተሳካላቸው አንድ እናት ብቻ ናቸው።የሌሎቹ ለጊዜው አድራሻቸውን ማወቅ አልተቻለም።እናት ከልጃቸው ጋር በእንባ የታጀበ ሠላምታ ከተለዋወጡ ቦኃላ የልጃቸውን የማያቋርጥ ጥያቄ መመለስ ይዘዋል።

ልጁን የቤተሰብ አባላትን ደህንነት ብቻ ሳይሆን የቤት እንሰሳትን ጭምር በስም እየጠራ ይጠይቃል።እንዴት እንደ መጡ ፣ መንገድ ላይ ምን ችግር እንደገጠማቸው ጥያቄውን ያሽጎደጉዳል። መምጣት እንዳልነበራባቸው ግዳጅ ላይ ያለው እሱ ብቻ እንዳልሆነ አንስቶ ከድል በኋላ መጥቶ እንደሚያያቸው ቃል ይገባል። ብቻ ዝም ብሎ ያውራ እንጂ በዚህ ወቅት እናቱ በመምጣታቸው የተሰማውን ስሜት መረዳት አቅቶታል።

እናት ልጃቸውን እያዳመጡ ሁሉንም እንግዶች ለማስተናገድ ወዲያ ወዲህ የሚሉትን ወጣቶች ላይ ዓይናቸውን ያንከራትታሉ።ወጣቶች ፊት ላይ የሚታየው ደስታ ቤተሰቦቻቸውን ያገኙ ያህል ነበር።

እዚህ መስተንግዶ እየተካሄደ ሻለቃ አመራሮች ከጓድ መሪዎች ጋር ተሰብስበው በአንድ ሐሳብ ተስማምተዋል።መቶ መሪዎች – ጓድ መሪዎችን ፣ ጓድ መሪዎች – አባላትን አዋያይተው ሐሳቡ በሙሉ ድምፅ በከፍተኛ ጭብጨባ ተቀባይነት አግኝቷል።አመራሮቹ እንደ አባላቱ ሁሉ ደስተኛ ቢሆኑም በአንድ ጉዳይ ግን ቅሬታ ገብቷቸዋል ።ቢሆንም እርስ በርስ እንጅ አባሉ ፊት አውጥተው አልተናገሩም።

በሚገርም ፍጥነት በውሳኔያቸው መሠረት ልጃቸውን ያገኙትም ሆነ ያላገኙት ቤተሰቦች መሸኛ የሚሆን ከአርባ ሺህ ብር በላይ ተዋጣ።ብቻቸውን የመጡትን እናት ልጃቸው እንዲሸኛቸው ይዘጋጅ ዘንድ ተነገረው።አመራሮቹን ቅር ያላቸውም ይሄው ነበር።ምክንያቱም ወታደሩ በተግባር የተፈተነ እጅግ በጣም ጎበዝ መትረየስ ተኳሽ ነበር።እውነት አላቸው።ጦርነቱ ዛሬ ይሁን ነገ መቼ እንደሚጀመር አይታወቅምና።

ክፍሉ ካለው ሁኔታ አንፃር እንግዶችን ማቆየት እንደማይችል፤በዚህም ምክንያት ቤተሰቦች ወደ ትውልድ ሥፍራቸው መመለስ እንዳለባቸው ለዚህም ልጆቻችሁ ባይኖሩም የኛም ወላጆች ናቸው በማለት እዚህ የሚገኙ አባላት የትራንስፓርት ማዋጣታቸውን ተነግሯቸው ከድል በኋላ ለመገናኘት መልካም ምኞት ተመኝተው ገንዘቡን አስረከቧቸው።

ሌላው ክፍሉ በእጅጉ አስቦበት የወሰነው ምንም እንኳን የማይቻልና አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ብቻቸውን የመጡትን እናት ልጃቸው እንዲሸኛቸው የተወሰነው ውሳኔ መሆኑ ተነገረ። ወታደሩ ቢያንገራግርም ጓደኞቹ ገና ቅድም ዕቃውን አሰናድተውለታል።ረዳቱ በደስታ መትረየሱን ከነጥይቱ ተረክቧል።

ሁሉም እጅግ በጣም አመሠገኑ።በእንባ ታጅበው ለነዚህ በሀገር ፍቅር ስሜት ልባቸው ለነደደው የቁርጥ ቀን ልጆች ድል ተመኝተው ለጉዞ ተነሱ። ወታደሩን ቅር እያለው የራሱንና የእናቱ ሻንጣ ይዞ ተነሳ።

እናት ሁሉንም ጓደኞቹ እያገላበጡ ሳሙዋቸው።በስተመጨረሻ ወደ ልጃቸውም ዞረው ልጆቹን በተሰናበቱት መንገድ ሳሙት።ልጁም አለቆቹም ጓጆቹም ግራ ተጋቡ።አንዱ እሱማ አብሮዎት ልሄድ እኮ ነው እማማ አላቸው። ምላሻቸው አይሆንም የሚል ነበር።

ንግግራቸው በሳግ ታፍኖ እንደምንም ችለው እንዲህ አሉ “አንድ ልጄን ፍለጋ መጥቼ ከወንድም በላይ የሚንሰፈሰፉለት ወንድሞቹንና ልጆቼን አየሁ።ከኔ በላይ የሚያስቡለት አመራሮቹን ጎበኘሁ። እኔ ደስተኛ የሚያደርገኝ ወይ ሁላችሁንም ይዤ መሄድ አሊያም ልጄን ከእናንተ ጋር ትቼው መመለስ ነው።ሁለተኛውን መርጫለሁ። ።ምክንያቴ ደግሞ ጥላችኋት መሄድ የማትችሉ ሌላ እናት አለች ።ኢትዮጵያ !” አሉ። የተከራከራቸው አልነበረም።ምላሹ እንባ ነበር።

ከልጃቸው ጋር የመጡት አባት ቀጠሉ።”እናት ያሉትን ተቀበሉ።እኛም ልጆቻችንን ብናገኝ ውሳኔያችን ከዚህ የተለየ አይሆንም ነበር።ብቻቸውን ናቸው ብላችሁም አታስቡ።እስከ አዲስ አበበ መንገዳችን አንድ ላይ ነው።ከዚያ ወዲያ ያለው አይቸግርም።ደግሞ አትተክዙ። እናንተ የኢትዮጵያ ወታደሮች ናችሁ።የኢትዮጵያ ! እናንተ የሚያምርባችሁ እንደ ቅድሙ ፉካራና ሽላላ ነው።በድል ተመለሱ።ለሀገር መሞትም ካለ የአባቶቻችን ወግ ነው።በርቱ።” አሏቸው።ወዲያው ጭብጨባና ፉጨት ሆነ።

እኚህ አባትም በለሆሳሳ “አይ አንቺ ሀገር ጠላትም ፣ ጀግና ልጅም አታጪም” ሲሉ ተደመጡ።

እንግዶች ተሸኙ።እናቱ ያስቀሩት ልጅ ለጓደኞቹ “እጅግ በጣም አመሠግናለሁ”ሲል ተቃወሙት። አንዱ እንዴት ታመሰግነናለህ? የሸኘነው እናታችንን ነው። በነገራችን ላይ እናትህን አቅፌ ስስማቸው የእናቴ የእናና ናፍቆት ወጣልኝ” አለ።ሁሉም እኔም እኔም ተባባሉ።

አንደኛው ቀጠለ።”ስማ እኛ እኮ የጋራ ሀገር ብቻ ሳይሆን የጋራ ቤተሰብ ያለን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ቤተሰቦቻችን የምናይ ከብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ሥር እንደ አዲስ በቃል ኪዳን የተወለድን ጓዶች ነን።’የጓድ አባት አባታችን ፣ እናት እናታችን ፣ ወንድም ወንድማችን ፣ እህት እህታችን ፣ ሚስት ሚስታችን ናቸው’ ሲባል አልሰማህም” ሲል ሁሉም ተያይዘው ሳቁ ።

ደንገጥ ብሎ “ምነው ምን አጠፋው?”ሲል

ወታደሩ ሚስቱ ሚስታችን አልተባለም አለው።

ኦ ይቅርታ ማለቴ እንደገና።ሚስቱም እህታችን ናት ለማለት ነው ሲል አረመ። ይሄንን ሲባባሉ ከከረሙበት ሥፍራ ተነስተው ወታደራዊ ጉዞ ለመጀመር የቀራቸው 30 ደቂቃ ብቻ ነበር። ትረካው ይቀጥላል።

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ

Leave a Reply