በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ተካሄደ

በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ተካሄደ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚውል የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር “እኛ ለእኛ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተካሄደ።

ከአካባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የተቋቋመው የሃብት ማሰባሰብ ዓቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ችግሩ ከተከሰተ ወዲህ በመንግስት በዞኖቹ የደረሰውን የአደጋ መጠን የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ የዳሰሳ ጥናት ማከናወኑን ተናግረዋል።

የክረምት ወቅት እየደረሰ ስለሆነ በመጠለያ ለሚገኙ ዜጎች ጎጆ ለመቀለስ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ለነዚህ ወገኖች እንደርስላቸው” ያሉት ዶክተር ፋንታ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም ባለሃብቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአማራ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው ችግር ላይ ያሉትን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም በመንግስት ብቻ የሚደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አስተላልፈዋል።

የእለቱ መርኃ ግብር የገቢ ማሰባሰቢያ ተየከናወነበት ሲሆን ባለሃብቶች ቃል የሚገቡበት ቅጽ ተሰጥቷቸዋል።

በቀጣይ ቃል የተገባው ገንዘብ እንደሚሰበሰብም ተጠቁሟል።

ግብረ ኃይሉ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞቸን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በቀጣይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የአጭር የጽሁፍ መልዕክት ድጋፍ ማሰባሰቢያ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።

በቀጣይ ቴሌቶን በማዘጋጀት ገቢ የማሰባሰብ ዕቅድ እንዳለም ተጠቅሷል።

አቶ መላኩ በቀጣይም ባለ ሃብቱ፣ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራውና ከክልሉ ውጭ ያለው ዜጋ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በገንዘብና በቁሳቁስ ለሚደግፉ እንደየፍላጎታቸው ማስተናገድ እንደሚቻልም ተጠቁሟል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በዞኖቹ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ሁኔታ በተመለከተ ጽሁፍ ያቀረቡት የአማራ ክልል አደጋ ስጋትና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአደጋ ስጋት ክትትል ባለሙያ እንደገለጹት፤ 351 ሺህ 744 ሰዎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለእናቶችና ህጻናት ለስድስት ወር ከ11 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ አልሚ ምግብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

አጠቃላይ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

“እስካሁን 56 ሺህ 732 ኩንታል እህል ድጋፍ ተደርጓል” ብለዋል።

Ena

Leave a Reply