“ተረሽነዋል” ዝርዝሩን እነሆ

እጅግ አስቸጋሪ፣ እልህ አስጨራሽ፣ህሊናንና ትዕግስትን የሚፈታተን፣ የጭካኔ ጥግ የደረሰ፣ ለሰሚውም ሆነ ለተመልካቹም ግራ ያጋባ፣ ከዳር እስከዳር ያላቀሰን፣ ጾታ፣ እድሜና ጤንነት ያልገደበው ጭካኔ ተፈጽሟል። በሴራ አምራቾች ዜጎች ተፈናቅለዋል። ነብሰጡር እህቶቻችን እዱር ያለ ረዳት ተገላግለዋል። እርጥብ አራስ ህጽናት ገና ከማህጸን እንደወጡ ግፍ በረከት ሆኖላቸው በማያውቁት በሃሩርና በቁር ተገርፈዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት በነቀለችው ጋሬጣ እየተወጋች፣ በጋሬጣው ፍልፈል ኩርንችቶች እየደማች፣ ከዛም ከዚህም በሚከፈላቸው ክፉዎች እየተናጠች ዜጎቿ የሃዘን ማቅ ለብሰው እንዲከስሙና እንድትበታተን የሚፈነቀለው ዓለት ሁሉ በፈነቀልም የአረሞቹ አሳብ አልተሳካም። ሊያባሉትና በደም ሊያጥቡት ያመቻቹት ህዝብ ሁሉን ፈተና አልፎ ዛሬ ደረሰ።

ሕዝብ ባካሄደው ኦፕሬሽን ሁሉም የክፋት ሃይሎች ዘሬ ተረሽነዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ መርጣለች። ያልመረጡ እጅግ ጥቂት ስፍራዎች ይመርጣሉ። ሕዝብ የሚያካሂደው ኦፕሬሽን ከሽፎ አያውቅምና የዛሬው ቀን ለኢትዮጵያ ሁሉ ታሪካዊ ቀን ነው። ይህ ቀን

  • ይህ ቀን፣ ዛሬ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ትህነግ የሚባለው አምባገነን በሕዝብ ቁጣ ተፈንቅሎ የተካሄደ የመጀመሪያና አንደኛው ታሪካዊ ምርጫ ሲሆን፣ ከዚህ በሁዋላ በታሪክ ትህነግ ሕዝብ በሃይል ያስወገደው የመጨረሻው የኢትዮጵያ አምባገነን ድርጅት ተብሎ ትውልድ ይማርበት ዘንድ በታሪክ ይጻፋል።
  • ከዚህ በሁዋላ በኢትዮጵያ በዓመጽ፣ በሃይል፣ በግርግር፣ በዱላ፣ በነውጥ፣ በሴራ የሚወገድ መንግስት እንደሌለና መንግስት የሚቀየረው በድምጽ ብቻ መሆኑ በይፋ የተረጋገጠበት ቀን ሆኖ ለትውልድ ይመዘገባል።
  • በዘመናዊ ዴሞክራሲን የመትከል ሂደት ኢትዮጵያ በታሪኳ ዴሞክራሲን በዓመታት ምጥ የተገላገለችበት ቀን ተብሎ ይታወጃል። በዚህም መሰረት ጸረ ዴሞክራሲ የሆኑ ተቋማት ለይመለሱ ይዘጋባቸዋል።
  • መፈንቅለ መንግስት ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልቡናና አዕምሮ እንዲሰረዝና ” በምርጫ ብቻ” የሚል ዘመናዊ የዴሞክራሲ እሳቤ በአደባባይ የተሞሸረበት ቀን ነውና ” ግንቦት 20″ የሚባለው የከፋፍለህ ግዛው ማስፈጸሚያ በዓል ሙት ይሆናል። እንዲሁም የአጋፋሪዎቹ የስህተት ትርክቶች በገሃድ ከኢትዮጵያ ላይ መነሳታቸው ይታወጃል።
  • ይህ ዴሞክራሲ የተወለደበት ቀን የቆየውን ክፉ ትርክት የሚነቅል ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ያስችል ዘንድ የብሄራዊ ዕርቅና መግባባት የተጸነሰበት ቀን ነውና ኢትዮጵያ በይቅርታ ችግሮቿን ለመቅበር፣ ልጆቿ አመላቸውን አቻችለው እንዲተቃቀፉ ቀን የምትቆጥርበት ቀን በምሆኑ የጥላቻ መንፈስ የሚረሸንበት እለት ይሆናል።
  • በታዳጊዎችና በአዲሱ ትውልድ ህይወትና ደም መነገድ ከዛሬው የዴሞክራሲ መወለድ በሁዋላ ዋጋ ቢስ እንደሆነ፣ በሃሳብ እንጂ በደም የሚመጣ ውጤት እንደማይኖር ትውልድ ውል የሚያስርበት ቀን ሆኖ ይዘከራል።
  • ተራራ እንቀጥቅጥ፣ የጦርነት ፈጣሪ፣ የብሄር ተሟጋች … ነን እያሉ ሲያምታቱና አገሪቱን በደም የነከሩ፣ ያረጡና ያረጀ አሳብ ያላቸው ፖለቲከኞች በጓሮ የሚሸኙበትና በአሳብ ልዕልና የሚያምኑ ወደፊት የሚመጡበት ዘመን ቀን ጅማሮ ሆኖ ዛሬ ይመዘገባል።
  • ካሁን በሁዋላ በኢትዮጵያ የሚንቀጠቀጥ ሳይሆን በደን የሚሸፈን ተራራ፣ ጦርነት ሳይሆን መደመር ባህሉ የሆነ ትውልድ፣ ብሄር መገዳደያ አጀንዳ ሳይሆን እንደቀደመው ዘመናችን ውበት ይሆናል።
  • ዛሬ ዴሞክራሲ ሲተከል ከላይ የተዘርዘሩት ሁሉ ተረሽነዋል።

አዲስ መንግስት በአዲስ አቁማዶ እንዲሉ ከይህ ቀደም ሕዝብ የተጠየፋቸው ነገር ግን ወቅቱ የሽግግር በመሆኑ በዝምታ የታለፉና አገሪቱን ለዲፕሎማሲ ውድቀት የዳረጉ አምባሳደሮችና የተባበሩት መንግስታት ወኪላችን፣ በፌደራል ስልታን ላይ ያሉ ለፋራው የማይመጥኑ ባለስልጣኖች፣ ቢመጥኑም የጎደፈ ታሪክና ህዝብን በገሃድ ሲዘልፉ የነበሩ ሙሉ በሙሉ የሚወገዱበት ቀን ከዲሞክራሲው መወለድ ጋር የሚከወን ጉዳይ ይሆናል።

ከሁሉም በላይ ያበቁና የጨረሱትን ሰብስቦ ማንከስ ከዚህ በሁዋላ አያስኬድም። ልምድ ያላቸውን መጠቀም አግባብ ቢሆንም በገደብ ይሁን። ካድሬ ስልችቶናልና አዳዲስ ሰው ሰው የሚሸቱ መሪዎች ወደፊት ይምጡ። ልክ ለውጡ ሲጀመር እንደሆነው እስር ቤቶች በርቅና በመጋባባት ሰረገላ ይዘጉ። ኢትዮጵያ አሸንፋለችና እንኳን ደስ ያለን። ኢትዮጵያ ጉድፎቿን በልጆቿ ረሽናለች፤ ዳግም ተወልዳለች ሰኔ 14 !!

ቀጣዩ ግድባችን ነው። ድግባችንን ከሞላን ሁሉም ይሰክናል። ሌላው መከላከያችን ነው። ጸዳሉ የሚአበራው አለኝታችን በትነውትና አፍርሰውት ማዕረጉን ገፈውት ነበር። ዛሬ ፓራ ኮማንዶ፣ አየር ወለድ፣ መደበኛውን የምድር ሃይል አድምቀውታል። ሙያዊ ብቃቱና የግዳጅ አፈጻጸም ክህሎቱ ዲጂታል ሆኗል። በዚህ ኮርተን ሳንበቃ የባህር ሃያልችን በሰርጓጅ መረከቦች ቀይ ባህር ላይ እየተንሳፈፈ ከአጋራችን ጋር የሰላም ዋስትና ሊሰተን፣ የኦፕለቲካ ዋግችንን ከፍ ሊያደርግ ከጫፍ ደርሷል። ኢትዮጵያ ጋሬታዎቿን መንቀል ብቻ ሳይሆን ተቋሞቿንም መልሳና አሻሽላ መትከል እንደምትችል አሳይታለችና መጪው ጊዜ ተስፋ ነው። ስንዴ በገፍ ማምረታችን የኩራታችን መጀመሪያ ነው። የከተሞቻችን መዘመን የክብራችን ጅማሬ ነው … ኢትዮጵያ በልጆቿ ታብባለች!!

You may also like...

Leave a Reply