ምርጫው የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥም መተናቀቁን ብርቱካን አስታወቁ

የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው ሃገር ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የጎላ የፀጥታ ችግር አለመከሰቱን አስታወቀ። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በአብዛኛው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎችም ወደ ድምጽ ቆጠራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከተከሰተው መጠነኛ ችግር ውጭ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁንም አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በስጋት ምስራቅ ሐረርጌ ዞን አንድ ምርጫ ጣቢያ አለመከፈቱን እንዲሁም ምዕራብ ሸዋ ዞን ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች በተከሰተ ችግር መዘጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡ይሁን እንጅ በአብዛኛው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ውጤታማ እንደነበርም አንስተዋል፡፡እንደ እርሳቸው ገለጻ በአንዳንድ አካባቢዎች ከተፈጠረው የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት ጋር በተያያዘም ቦርዱ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የተፈጠረውን እጥረት መቅረፍ ሲቻል፥ በሲዳማ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት መፈጠሩን አውስተዋል፡፡በተለይም በሲዳማ የተፈጠረውን የድምጽ መስጫ ወረቀት ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት በተፈለገው ጊዜ ማድረስ ባለመቻሉ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እንዲቋረጥ ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም በነገው እለት ረፋድ ላይ በሲዳማ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ወረቀት ስርጭት ተደርጎ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡በጋምቤላ በአምስት የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ እጥረት በማጋጠሙ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተቋርጦ እንዲቆይ መደረጉን ጠቅሰው፥ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ግን መደበኛው ሂደት መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

“መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን ባከበረና ከፍ ባለ አገራዊ ስሜት ለሰሩት ዘገባ ምስጋና ይገባቸዋል” – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

መገናኛ ብዙሃን የምርጫውን ሂደት ሙያዊ ስነ-ምግባርን ባከበረና ከፍ ባለ አገራዊ ስሜት መዘገባቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሀመድ ኢድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ሙያዊ ስነ-ምግባርና መመሪያን የተከተሉ ዘገባዎችን ሲሰሩ ውለዋል።ጋዜጠኞች መረጃዎችን ለማሰባሰብ በከተማና በገጠር አካባቢዎች ተሰማርተው በተቀናጀ መልኩ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን አቅርበዋል ያሉት አቶ ሙሀመድ፤ “ይህም ጋዜጠኞች መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ያላቸውን ዝግጁነት ያሳያል” ብለዋል።

ዘገባዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ሲያደርጉ በላቀ አገራዊ ስሜት እንደሆነ ያስታወሱት ዋና ዳይሬከተሩ፤ ይህ ተግባራቸው በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም አብራርተዋል።ዋና ዳይሬክተሩ መገናኛ ብዙሃኑ በአገራዊ ምርጫው ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።በተመሳሳይ ምርጫውን ለመዘገብ የገቡ የውጭ መገናኛ ብዙሃንም እስካሁን ባለው ሂደት የምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ሂደትና ትክክለኛነት የሚያሳዩ መረጃዎችን ለዓለም ሕዝብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።በአንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በምርጫው አዘጋገብ ላይ የተወሰኑ ችግሮች ቢስተዋልባቸውም በአብዛኛው ግን በመልካም ሊጠቀስ የሚችልና የምርጫ ሂደቱን እውነታ ያሳየ እንደነበር ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply