December 3, 2021

ሩሲያና ኢትዮጵያ ግኑኝነታቸውን ውደ ላቀ ደረጃ አሳደጉ

ሩሲያና ኢትዮጵያ ግኑኝነታቸውን ውደ ላቀ ደረጃ አሳደጉ። በትግራይ ክልል የተወሰዱ እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናወኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስትን የሞራል ፅናት እና የፖለቲካ ብቃት እንደሚይሳዩ ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ አስታወቁ።

ይህ የተገለጸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ሞስኮ ራሽያ ተገናኝተው ከመከሩ በሁዋላ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ነው። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በራሺያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ የመልሶ ማቋቋም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ ለመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲሰጡ ማመቻቸት እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ውንጀላዎችን የማጣራት ተልዕኮ እና ህጋዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን እና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር መሰረት የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች ለህዝብ ይፋ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያ አሁንም አፍሪካዊ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሄ የመስጠት አካሄድን በመከተል በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አቋሟን አጥብቃ እንደምትቀጥል አስረድተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት በሁለቱ ሃገራት መካከል ችግሮችን በጋራ መፍቻ ስርዓት የተበጀ ቢኖርም፤ ሱዳን አጋጣሚን ተጠቅማ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቷ ከዓለም-አቀፍ ስርዓት ውጪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ግጭት በዲፕሎማሲ ጥረት መፍትሄ ለማበጀት ኢትዮጵያ የጀመችው ጥረት በቀጣይ ተጠናክሮ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ራሺያ እንደቀድሞ ሁሉ በመርህ እና የሃገር ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እና የምትወስደውን አቋም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንደሚያደንቁ የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዕምነታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ራሺያ ፎረም አዲስ አበባ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው “በትግራይ ክልል መንግስት በሃላፊነት የወሰዳቸው እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስት የሞራል ፅናት እና የፖለቲካ ብቃት ማሳያ ናቸው” ብለዋል፡፡

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሩሲያ በታዛቢነት እንድትሳተፍ መደረጉ የታሪካዊ ግንኙነቱ ከፍታን ያንፀባረቀ መሆኑን በመጠቆም፣ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

በህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት የተጀመረው ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ራሽያ እንደምታምን፤ ለዚሁም አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር እና ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት የምትከተለውን ጤናማ አካሄድ አድንቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ራሽያ እንደማትደግፍ ገልፀው፤ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ራሺያ ፎረም በአፍሪካ ህብረት መዲና አዲስ አበባ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁ መሆኗ መገለፁን አድንቀዋል፡፡

በሁለትዮሽ ግንኙነቱ በተለይ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሊጂ አጠናክረው ለማስቀጠል፤ የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር ለማስገባት እንዲሁም በሂደት ላይ ያሉ ስምምነቶችም በፍጥነት እንዲፈረሙ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱም ሚኒስትሮች ያካሄዱት ውይይት ፍሬያማ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት ትርጉም-ባለው ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ሚኒስትሮቹ ማረጋገጣቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

መነሻ ዜና ኢዜአ

Leave a Reply

Previous post የምርጫውን ሂደት ለማወክ የሞከሩ 123 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ! ፀረ ሰላም ሃይሎች ተመደምስሰዋል
Next post “ትህነግ ድል ቀናው፤ ትህነግ በጀት ተደበደበ”ቢቢሲ፤
Close
%d bloggers like this: