የዛሬ አጫጭር ዜናዎች – 150 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት በደረሰ የህንጻ መደርመስ አደጋ እስካሁን 150 የሚሆኑ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም፡፡

ባሳለፍነው ሃሙስ በተከሰተው በዚህ አደጋ ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር ዘጠኝ ሲደርስ÷ 150 የሚሆኑት ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ነው የተባለው፡፡

የነፍስ አድን ሰራተኞች በአደጋው የጠፉ ሰዎችን ለማግኘት እና በህይወት ያሉ ዜጎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ተስፋ የተቀናጀ አሰሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡

የአካባቢው አመራሮች የአደጋው መነሻ ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የምህንድስና ባለሙያዎችን አሰማርተው እያስጠኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ዙሪያ እመከሩ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በተለይም የህንፃውን መሰረት፣ የኮንክሪት ሙሌት እና ከመሬት ውስጥ የሚመነጭ ውሃ መኖሩን ለማጥናት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ እስከዛሬ ድረስ ለህንፃው መደርመስ ምክንያቱ በውል አለመታወቁንም ነው የአካባቢው ባለስልጣናት የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው እንዲሳካ ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋና  አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው “ከስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ አንድ ሳምንት በኋላ ዛሬ ጠዋት ከፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝቼ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና የወጣችበት ሰላማዊ ምርጫ እንዲሳካ ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋናዬን አቅርቤያለሁ” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ገና በጅምር ላይ ያለውን ዴሞክራሲያችንን ለማጠናከር በምርጫ ሂደቱ ውስጥ የታዩ ተግዳሮቶች እና ክፍተቶችን በመገምገም ምን እንደተማርንባቸው ተወያይተናል ሲሉም አክለዋል፡፡


በዓለም ባንክ ድጋፍ የአንድ መቶ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

አውቶቡሶቹ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓ ስታንዳርድ ተጠናቀው የሚገቡ እያንዳንዱ አውቶቡስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ግዥው የሚፈፀም ይሆናል ተብሏል፡፡

የአውቶቡሶቹ ግዥ ተፈፅሞ ሲጠናቀቅም ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሚሰጡ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አውቶቡሶቹም የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ እና አሁን የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል ነው የተባለው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ ምቹ፣ አስተማማኝና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡


የላሙ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የወደቡ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግዷ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስ የታመነበት መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለዘመናት የቆየውን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በኢኮኖሚው ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደር መለስ፣ አገራቱ በንግድና ኢንቨስትመንት መተሳሰራቸው የህዝቦቹን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡

የኬንያ የወደቦች ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ ኢንጂነር አብዱላሂ ሰመተር በበኩላቸው፣ ከፊል ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት በሆነው የላሙ ወደብን ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ተጠቅመው የንግድ ሥራቸውን እንዲያቀላጥፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኃላፊው የላሙ ወደብን ለጎበኘው የኢትዮጵያ የሚዲያ ቡድን እንደገለጹት፣ ተጨማሪ ሁለት የመርከብ ማቆያ ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል። አሁን ላይ አጠቃላይ የወደቡ የግንባታ ሂደት 90 በመቶ መጠናቀቁም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በወደቡ መርከቦቿ የሚያርፉበት ቦታ እየተዘጋጋ እንዳለ የተገለፀ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ረጅም ጊዜ የሚፈጀውንና ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉበትን የወደብ ክፍያ በመቀነስ በጥቂት ቀናት ብቻ ወጪና ገቢ ንግዳቸውን ማቀላጠፍ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

የላሙ ወደብን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለምን ጨምሮ ዲፕሎማቶች፣ የላሙ ግዛት አስተዳዳሪዎች እና የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጎብኝተዋል፡፡

(በአስታርቃቸው ወልዴ) WALTA

Leave a Reply