ህዝቡ ለምን ግራ ተጋባ?

ፖለቲካ ቆሻሻ ቁማር መሆኑን የሚገባው ይገባዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያልታደሉ አገሮች ደግሞ ቁማሩ በመርዛማ ዘርና በጥላቻ የተለወሰ ነውረኛ ጨዋታ ነው። ህወሃቶች ከተፈጠሩ ጊዜ ጀምሮ ዘረኝነትና ጥላቻን ለውሰው የተጫወቱት የፖለቲካ ቁማር ለውድቀታቸውና ውርደታቸው ዛሬ ከጉራና ቀረቶ በቀር ሌላውን ሁሉን በዜሮ እንዲያጣፉ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

ከትናንት ስህተታቸው ተምረው፣ ዛሬ ላይ ቆመው ለነገ የተሻለ ራዕይ ማየት የተሰናቸው እኩዮች በረሃብና በችግር እየጠበሱ ለሚነግዱበት ለሞትና ለስደት ለሚዳርጉት የትግራይ ህዝብ እንኳን ሳይራሩ ዳግም አውዳሚ ጦርነት ጫሩ። ሰይጣናዊ እቅዳቸው እልተሳካም እንጂ ቢሳካ ኖሮ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ አውድመው ህዝቡን እርስ በእርስ እያፋጁ እሳቱን እየሞቁ የለመዱትን የደም ንግድ ሊያጧጡፉ ነበር። ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ይሁናና ህወታቸውን ገብረው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው አነሰም በዛም ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ ታድገዋታል።

የሰራዊቱ ወደር የለሽ ውለታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሰሞኑን ሰራዊቱን ከበርካታ የትግራይ ከተሞችና አካባቢዎች ለማስወጣት የተወሰነው የመንግስት ውሳኔ በጣም ግራ የሚያጋባ በመሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል። እስኳሁን ድረስ የጦሩ የበላይ አዛዥ ከሆኑት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ይሁን ከየትኛውም የመንግስት ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ ኦፊሴላዊ መግለጫ አልተሰጠም። ይሄ ደግሞ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ አመቺ ክፍተት ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ሰጡት የተባለው ማብራሪያ ሰሞኑን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተጠራ አንድ ስብሰባ ላይ ብቻ በተጓዳኝ የተናገሩት ነው። ታዳሚ ነበርን ከሚሉ ግለሰቦች ከወጣው ቅንጭብጫቢ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መንግስት በትግራይ ጉዳይ ላይ እንደ ፍጥርጥራችሁ የሚል አቋም የያዘ ይመስላል። ለዚህ አቋሙ አሳማኝ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችሉም የውጭ መንግስታት ጫናና የጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከምክንያቶቹ በዋነኛት ሊጠቀሱ መቻላቸው አጠያያቂ አይደለም። ከዛም በላይ በሁለቱም በኩል የሚያልቀውና ደሙን የሚያፈሰው የድሃ ገበሬዎችና እናቶች ልጆች መሆኑ ለጦርነቱ እልባት መፈለግ አስተዋይነት መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እኔ እይታ ግን ለአሸባሪና ሃላፊነት የማይሰማው የሽፍታ ቡድን አገር ምድሩን ለቆ መውጣት ነገ የበለጠ ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው። ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎትና ጸሎት ሊመጣ እንደማይችል ታሪክ ከበቂ በላይ አስተምሮናል።

ጦሩን ከትግራይ የማስወጣቱ ውሳኔ በስህተቶች የታጀበ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ከሁሉም በላይ ግዙፉ ስህተት ይሄን ያህል ወሳኝ የሆነ ውሳኔ ሲደረግ ያለ ምንም ፍንጭ ግብታዊ በሚመስል ሁኔታ ጦሩ ትግራይን ለቆ እንዲወጣና መንግስት በተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉ መታወጁ ነው። ለዚህም ተኩስ አቁም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው ደግሞ የትግራይ ጊዚያዊ አስተደዳር ገበሬዎች በእርሻ ስራቸው ላይ እንዲሰማሩ የፌዴራል መንግስትን ስለጠየቀ መሆኑን በመንግስት ሚድያዎች በኩል ሰማን። ይሁንና የተሰጠው ምክንያት እንኳን የኢትዮጵያን ገበሬ የሩቅ ታዛቢዎችን የሚያሳምን አልነበረም።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ያለበት ትልቁ ክፍተት ህዝቡም ይሁን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግራ እንዲጋባ አስተዋጾ አድርጓል። ፖለቲካ 95 በመቶ ኮሚዩኒኬሽን ነው ይባላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በተለያየ እርከን ላይ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት መናገር በሚገባቸው ጉዳይና ሰአት አይናገሩም፣ መናገር በማይገባቸው ሰአት ደግሞ መናገር በሌለባቸው ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ይታያል። በግብር ከፋዩ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱ የሚድያ ተቋማት ወሳኝ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም እርባና ያለው ስራ ሲሰሩ አይታይም። ፕሬዚዳንቷ እንግዳ ተቀበሉ ወይ ሸኙ፣ ግፋ ቢል በሚድያ ፍቅር የወደቁ እንደነ አዳነች አበቤ አይነት ባለ ስልጣናት በየእለቱ ለጥቃቅን ጉዳዮች ሁሉ ካሜራ እየሰበሰቡ በህዝብ ሲቀልዱ ከልካይም መካሪም የለም።

በነፍስና በደም ከተከፈለው መስዋትነት እጅ ከባድ ከመሆኑ አንጻር በዚህ በሰሞኑ ውሳኔ ህዝቡ ግራ የገባውና በውዥንብር የተመታው መንግስት ስራውን በአግባቡ ስላልሰራ ነው። ውሳኔው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ለህዝቡ ማብራሪያና ገለጻ ሊደረግ ይገባ ነበር። ከዛም አልፎ ለአለም አቀፉም ማህበረሰብ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ አስረድቶ ውሳኔው ለምን እንዳስፈለገ ከመግለጽ ይልቅ በቁንጽሉ የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ማወጅ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እያየንና እየሰማን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በየእርከኑ ስልጣን ላይ የተቀመጡ ባለስልጣናት ተጠያቂነታቸው ለህዝቡ መሆኑን ፈጽሞ ሊዘነጉት አይገባም። በእነርሱ ውሳኔ ሰራዊቱም ይሁን ህዝቡ ግራ መጋባት አይገባቸውም። በመንግስት ውስጥ የሚታየውን የኮሚውኒኬሽን ክፍትት መሙላት ወሳኝ በመሆኑ ከሙያው ጋር ምንም ትውውቅ የሌላቸውን አጫፋሪዎች ሰብስቦ ህዝብን ግራ ከማጋባት ይልቅ ባስቸኳይ ባለሙያዎችን ቀጥሮ በአገር ውስጥም ይሁን በአለም አቀፍ ደረጃ ክፍተቱን መሙላት ያስፈልጋል።

ወሳኝ የሆኑን አገራዊ ውሳኔዎች ለውዥንብርና አሉባልታ መተው የሚያስከትለው ፖለቲካዊ ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን መዘንጋት ዋጋ ያስከፍላል። ጦሩ ባይሸነፍም መንግስት ግን በራሱ ላይ አክሳሪ ጎል ማስቆጠሩን ማመን ነገ ስህተቶችን ለማረም የሚጠቅም ይመስለኛል።

አበበ ገላው ፌስ ቡክ

Leave a Reply