ለጋሾች ለትግራይ እጃቸውን እንዲዘረጉ መንግስት ጥሪ አቀረበ

መንግስት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ክልል የሚደረገውን መልሶ ማቋቋም እንዲያግዝ ጥሪ አቀረበ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት የወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም በተመለከተ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅትም መንግስት ከስምንት ወራት በፊት ወደ ህግ ህግ ማስከበር ዘመቻ የገባባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች አብራርተዋል፡፡ የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀና ግቡን የመታ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ክልሉን መልሶ ወደ መገንባትና ወደ ማቋቋም መገባቱንም አስረድተዋል፡፡ የተናጥል የተኩስ አቁሙ በክልሉ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በአግባቡ ድጋፍ ለማድረስና አርሶ አደሩ የእርሻ ወቅቱን በአግባቡ እንዲጠቀም ታስቦ የተወሰነ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖችም የዕለት ደራሽ እና ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ መሰናክል እየፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ የወደሙ እንደ ባንክና ቴሌኮም ያሉ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት መደረጉን ጠቁመው፥ አሁንም ድረስ ቡድኑ መሰል መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንደሚፈጽምም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሃሰት ወጣቶችን እየቀሰቀሰ የክልሉን ሰላም እያወከ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፥ ቡድኑ በሚፈጥረው ሽብርም የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመሩንም ጠቁመዋል፡፡ የህወሃት የሽብር ቡድን ስጋትነት እንዳከተመለትና የመልሶ ማቋቋም ስራው በስፋት እንደሚከናወንም ነው የገለጹት፡፡

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው ቡድኑ አሁንም ትንኮሳዎቹን የሚቀጥልና የማያቆም ከሆነ መንግስት እንደማይታገስና ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በህግ ማስከበር ዘመቻው ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትም ገለልተኛና ተዓማኒ ሪፖርት እንዲወጣ የሚያደርጉትን ጫና እና ተፅዕኖ እንዲያቆሙም ጠይቀዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሰብአዊ ድጋፉን እና በክልሉ የሚደረገውን መልሶ ማቋቋም እንዲያግዝና የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply