በትግራይ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን በቀይ መስቀል በኩል ለማስወጣት መንግስት እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታወቀ

በክልሉ በሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ፈተና ለመዉሰድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ ተማሪዎቹ በቀይ መስቀል አማካኝነት ሊወጡ ይችላሉ ለዚያም መንግስት አስፈላጊዉን ትብብር ያደርጋል ነዉ ያሉት፡፡

የተማሪዎቹን ጉዳዩን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እየተከታተለዉ እንደሚገኝ የተናገሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በቅርቡም የተደራጀ መረጃ ይዘን እናሳዉቃለን ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ ፈተና ለመዉሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸዉን የገለፁት አምባሳደሩ ፣ ተማሪዎቹ የመዉጣት ፍላጎት ካላቸዉም በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ና በሌሎች ድርጅቶች አማካኝነት መዉጣት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግስት የሚችለዉን ሁሉ እንደሚያደርግ ነዉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ያስታወቁት፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችን በተመለከተ ከዩኒቨርስቲ አመራሮች ጋር ተወያይተው ፣ተማሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያሉም እንዳሉ ነግረውናል ማለቱ ይታወሳል፡፡

ስለሆነም የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው በመልካም ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ተረድተው በመንግስት የተጀመሩ ጥረቶችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በቀጣይ ተማሪዎች ፈተና ወስደው ሲጨርሱ የሚኖሩ ጉዳዮችን እናሳውቃለን እናም የተማሪ ወላጆች በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መረጃዎችን ብቻ እንዲጠቀሙ እና ተረጋግተው እንዲጠብቁ ማሳሰቡ የሚታወስ ነዉ፡፡

የኢትዮ ኤፍ ኤም

Leave a Reply