የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት 2.39 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በ2013 በጀት ዓመት 2.39 ቢሊዮን ብር ትርፍ መሰብሰቡን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ባንኩ የ2020-2021 በጀት ዓመት ጠቅላላ የስራ አፈፃፀም በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን አንደገለፀው አጠቃላይ የካፒታል መጠኑንም 4.6 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ደርቤ አስፋው በበጀቱ ዓመቱ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን 1.65 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል ብለዋል።
አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 72.69 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው ገልፀዋል።
ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ከዓምና ተመሳሳይ ወቅት አንፃር እድገት ማስመዝቡንም ነው የገለፀው።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 343 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜ አንፃር የ20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ዘንድሮ ብቻ የባንኩ የደንበኞች ቁጥር 1.48 ሚሊዮን አዲስ አባላት የተመዘገቡ ሲሆን በአጠቃላይ የባንኩ ደንበኞች ብዛት 7 ሚሊየን ደርሷል ተብሏል።
ባንኩ ዘንድሮ በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች ባንኩ 49 አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈቱን እና በአጠቃላይ ቅንጫፎችን ብዛት 469 ማድረሱን አስታውቋል።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ባለሀብቶች አርሶ አደሮች መሆናቸው ከሌሎች ባንኮች የተለየ ያደርገዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የሸሪዓ ህግን በመከተል በሰራቸው ስራዎችም 1.86 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት መቻሉንም የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ያስታወቀ ሲሆን ባንኩ አጠቃላይ ሀብቱ 81.54 ብሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል።

ምንጭ፡-ኢቢሲ

Leave a Reply