የሕወሓት መመለስ አንድምታ

በተዋጊዎቹ ወዲያና ወዲህ፣ በደጋፊነት ወይም በተቃዋሚነት የተሰለፉ ሰዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው የምር ለሕዝቡ አዝኖ ነው ወይስ ተሸንፎ በሚለው ጉዳይ እየተከራከሩ ነው። 

የሕወሓት መመለስ አንድምታ

በፍቃዱ ኃይሉ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጦርነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሁሉ ግዙፉ ነው። ሕወሓት ከቀድሞዎቹ ሦስት ዐሥር ዓመታት ጭቆና እና ብሔር ተኮር ስርዓት ግንባታ ጋር ተያይዟል። ከሕወሓት ጋር አብረው ይሠሩ የነበሩት ደግሞ ሰላማዊ መፈንቅለ ሥልጣን አድርገውበት፣ ራሳቸውን ብልፅግና ፓርቲ ብለው በመሠየም እንዲሁም የቅርፅ እና የርዕዮት ለውጥ በማድረግ የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን ተቆጣጥረዋል። 

በነዚህ ሁለት ኃይሎች መካከል የሥልጣን ሽኩቻ የተለኮሰው ገና በማለዳ ነበር። የሥልጣን ሽኩቻው የመጀመሪያው ደረጃ ድጋፍ ማሰባሰብ ነበር። ሕወሓት የትግራይ ተወላጆች እና የፌዴራሊዝሙ አፍቃሪዎችን ለማሰባሰብ ሲሞክር፣ ብልፅግና ደግሞ የሕወሓትን ተቃዋሚዎችና የተቃውሞ አጀንዳቸውን ማሰባሰቢያ አድርጓቸዋል። በመቀጠል፣ ድጋፍ ማሰባሰቡ የወታደራዊ ኃይል ወደ ማሳየት ትርዒት ተሸጋገረ፤ መቀሌ እና አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ወታደራዊ ትርዒቶች ተጨናነቁ። በዚህ ጊዜ የመቀሌዎቹ አዲስ አበባ፣ የአዲስ አበባዎቹ መቀሌ መግባት እንደማይችሉ ሲታወቅ፥ ከሁለት አንዳቸው ካልጠፉ በስተቀር አንዳቸው ለሌላኛው እንደማይተኙ እርግጥ ሆኖ ነበር። በዚህ ወቅት ሕወሓት ወታደራዊ የበላይነት ያስጨብጠኛል በሚል ሰሜን ዕዙ ላይ ባደረገው ዘመቻ ሰበብ ጦርነቱ ተቀሰቀሰ። ይህም የመጨረሻው መጀመሪያ ሊባል ይችላል።

1) የተኩስ አቁም ወይስ ሽንፈት?

በተዋጊዎቹ ወዲያና ወዲህ፣ በደጋፊነት ወይም በተቃዋሚነት የተሰለፉ ሰዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው የምር ለሕዝቡ አዝኖ ነው ወይስ ተሸንፎ በሚለው ጉዳይ እየተከራከሩ ነው። ለሰብኣዊነት ነው ከተባለው የተናጠል የተኩስ አቁም እወጃው አስቀድሞ ባሉት 10 ቀናት ገደማ በርካታ ውጊያዎች እየተካሔዱ ነበር። በነዚያ ውጊያዎች የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል የቀናው አይመስልም ነበር።  ሠራዊቱ አንድ ወታደራዊ አውሮፕላን በትግራይ ተዋጊዎች ተመትቶ ወድቋል፤ በርግጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት የወደቀው በቴክኒክ ብልሽት ነው ብሎ አስተባብሏል። የኢትዮጵያ ሠራዊት የተኩስ አቁም ማወጅ ብቻ ሳይሆን ይዞታዎቹን፣ ከዋና ከተማይቱ መቀሌ ጭምር ለቅቆ ወጥቷል። ይህ ሲታይ ሠራዊቱ በሽንፈት “አሸባሪ” ብሎ ለጠራው ኃይል የተቆጣጠረውን ቁልፍ ቦታ ለቅቆ ለመሸሽ እንደወሰነ መገመት ይቻላል።

በተቃራኒው የትግራይ ሠራዊት ሕዳር ወር ላይ ጦርነቱ ሲጀመር በነበረው አቅሙ አይደለም። የትጥቅ ትግል መሪዎቹን አግኝተው ካናገሯቸው ቀደምት ገለልተኛ አካላት ዘገባዎች የምንረዳው፣ የመሣሪያ አቅማቸው ተዳክሟል። ማዕከላዊ የትዕዛዝ መሥመራቸው ተበጣጥሷል። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከሕወሓት ውጪ የሕዝብ ጦርነት ሆኗል ሊባል የሚችልበት ደረጃ ደርሷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ከጋዜጠኞች ጋር ምርጫውን አስመልክቶ በቤተ መንግሠት በነበራቸው ጊዜ ያስተላለፉት መልዕክትም ቢሆን የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ተሸንፏል ማለት ግን የሕወሓት ሠራዊት አሸንፏል ማለት አይደለም። በየውጊያው ትንንሽ ድሎች ቢኖሩም በጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች ተሸናፊ ናቸው። ሽንፈታቸው የዜሮ ድምር ውጤት ከሚባለውም የከፋ፥ የአንዱ ሽንፈት የአንዱ ድል መሆን እንኳን የማይችልበት የሁለት ወገኖች ሽንፈት የታየበት ክስተት ነው። ምክንያቱም ከተናጠል ተኩስ አቁሙ በፊት የተፈጠረው ቀውስ በረዥም ጊዜ የማይድን እና ሁለቱንም ወገኖች የሚከተላቸው ቁስል ነው። 

ሁለቱም ወገኖች ከስረዋል። አሁን የሚደራደሩት ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ካሰቡት የተለየ ነገር ነው። ሕወሓት የበለጠ ክልላዊ ነጻነትና ቁጥጥር ከማግኘት እና የብልፅግናን መንግሥት ከማስወገድ ኅልውናውን ለማስቀጠል ወደ መፍጨርጨር ትግል ገብቷል፤ የብልፅግና መንግሥት ደግሞ የበላይነቱን ከማስጠበቅ እና ሕወሓትን ከማስገበር ይልቅ፥ በዓለም ዐቀፍ መድረክ በሰብኣዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ተከሳሽነት እና ከገጠመው የዲፕሎማሲ ቀውስ ራሱን ለማዳን እየታገለ ነው። 

2) የምሥራች ወይስ መርዶ?

የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጥል የተኩስ አቁም አዋጅ ትግራይ ውስጥ ያለውን ቀውስ የማስታገስ ዕድሉ ትንሽ ነው። የትግራይ ገበያ ፈርሷል። መንግሥታዊ መዋቅሩም ፈርሷል። ሕወሓት በቀድሞ ቁመናው አይደለም። ምንም እንኳን ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ቡድን ነው ቢባልም፥ ቅቡልነቱ ብቻውን እነዚህን መልሶ የመገንባት አቅም አይሰጠውም። ይባስ ብሎ ክልሉ በጦርነት ስሜት ውስጥ ባሉ ጎረቤቶች ተከብቧል፤ መጪው ጊዜ ካለፈው ይበልጥ ያስፈራል። የፌዴራል መንግሥቱም በትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ባለማግኘቱ ቂም ቋጥሮ ከሕወሓት ጋር መከራው እንዲቀጥል የሚፈልግ ይመስላል።

አማራ እና አፋር ክልሎች “በሕወሓት መንግሥት በኃይል ተወስዶብን ነበር” የሚሉትን ግዛት እያስተዳደሩ ነው። እነዚህን ግዛቶች ለመከላከል ወደ ሌላ ጦርነት ለመግባት ዝግጁ ናቸው። ይህንንም ቢያንስ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከተኩስ አቁም አዋጁ በኋላ በግልጽ ተናግሮታል። በሌላ በኩል ኤርትራ አለች። አምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት ሕወሓት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት እና በኋላ አድርሶብኛል ለሚለው በደል ማወራረጃ የትግራይ ሕዝብ ላይ የበቀል በትር እንዳሳረፈ ባለፉት ስምንት ወራት አይተናል። አሁንም የሕወሓት መሪዎች እንደዛቱት ለተጨማሪ ለዘመቻ የሚሰናዱ ከሆነ ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። 

በዚህም አለ በዚያ የተዳከመው የሕወሓት ጦር መቀሌ መመለስ ለብዙኃን ተጋሩዎች ተስፋ ሰጪ ሊሆን ቢችልም፣ የሚጠበቅበትን መስጠት ይችላል የሚል እምነት ግን የለኝም። 

3) የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ

የትግራይ ጦርነት የትግራይ ብዙኃን ከኢትዮጵያ ያቆራረጠ ነው ቢባል ማጋነን አይሆን። ፖለቲካው የእያንዳንዳቸውን የትግራይ ተወላጆችን ጓዳ በአንድም በሌላም በኩል አንኳኩቷል። ከ17 ዓመቱ የሕወሓትና የኤርትራ ሕዝቦች ነጻነት ግንባር ጦርነት ዘግናኝ ትውስታ ያልወጣው የትግራይ ሕዝብ፥ የፖለቲካ ኃያላን የሥልጣን ሽኩቻ ዳግም ሰለባ ሆኗል። ብዙዎች እንደሚገምቱት ብዙኃን የትግራይ ተወላጆች ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ላይ መቀጠል አይፈልጉም። ነገር ግን ይህ እዚህ ላይ የሚቆም አይመስልም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት አጥቷል። ቁልፍ የፌዴራል ሥልጣኖችን የተቆጣጠሩት ሰዎች የትውልድ ክልል የሆነችው ኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ የተቃውሞ ስሜት አለ። የዋነኞቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች ታሥረዋል፤ ምርጫ ላይ አልተሳተፉም፤ ወዘተ። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የተከፋፈለ ሲሆን፣ አንደኛው ክፋይ ትላንት ለሊት የኦሮሚያ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ ይታወቅልኝ ብሏል፤ ይህ መግለጫ የመጣው ሕወሓት ወደ መቀሌ መመለሱን ተከትሎ መሆኑ የአጋጣሚ አይመስልም። ይልቁንም፣ መንግሥትን በተለያዩ አቅጣጫዎች ውጥረት ውስጥ በማስገባት ወደ ሚፈልጉት “የነጻነት” አጀንዳ ሊወስዱት የፈለጉ ይመስላል። ሕወሓት የኦነግ የቀድሞ ጠላት ቢሆንም፥ አሁን ግን የአጭር ጊዜ የዓላማ አጋር ሆኗል ማለት ይቻላል። እነዚህ ቅሬታዎች እና ፖለቲካዊ ጫናዎች እያደር ሥር እየሰደዱ መሔዳቸው አይቀርም። ሆኖም፣ ቤተ መንግሥት ውስጥ እነዚህን ቅራኔዎች ከሥር፣ ከሥር፣ በብልሐት፣ በሕዝባዊ ተሳትፎ እና በንግግር ለመፍታት ዝግጁነት ያለ አይመስልም። 

ከሁሉም የፖለቲካ ቀውሶች ለመውጣት ከሁሉ አስቀድሞ የትግራዩ አንገብጋቢ ችግር መፈታት አለበት። የትግራዩን ችግር ለመፍታት መጀመሪያ ሰላምና መረጋጋት የግድ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህንን የሕወሓት መቀሌ መግባት ያመጣዋል የሚል እምነት የለኝም። ቀድሞም የተዳከመው ሕወሓት በጠበኛ የትግራይ አጎራባቾች ተከብቦ ራሱንም፣ ትግራይንም መልሶ የማቋቋም አቅም የለውም። ይልቁንም የዓለም ዐቀፍ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወደ ክልሉ እንዲገባ በመፍቀድ፣ የሚገኝ ከሆነ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ በገለልተኛ አሸማጋዮች ለማግኘት መሞከር ብቸኛው መፍትሔ ይመስላል። የትግራዩን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከተቻለ፣ በሌሎች ክልሎች ላቆጠቆጡት ቀውሶችም ትምህርት መቅሰም ይቻል ይሆናል። 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም። DW

Leave a Reply