በሰከረ ትውልድ፣በሞትና በረሃብ መቆመር ይቁም!

የኢትዮጵያችን ነገር ከተሳከረ ቆይቷል። አገሪቱ የተከለችበት እምነት፣ ባህል፣ ወግና ማህበራዊ መስተጋብሮች አንቀው ይዘዋት እንጂ እንደ ፖለቲከኞቻችን ስካር ቢሆንም ድሮ በጠፋን፣ ባከተመልን፣ ለወሬ እንዳንተርፍ ሆነን በተበተንን ነበር።

በፊት ሰክረው የሚያሳክሩን በስልሳዎቹ የፖለቲካ መጋኛ የተመቱ፣ ቋንቋቸው መገዳደል የሆነ፣ ተቀምጠው ለመነጋገር የማይወዱ የ”የትም ፍጪው” አባዜ የተጠናወታቸው ነበሩ። ከዛ ጀመሮ ሲነከባለሉ የመጡ ዛሬ ድረስ ስካርቸው ሞቅ በረድ እያለ አሳራችንን ያበሉናል።

ከነሱም መካከል የባሰባቸውና በስሱ የዘመኑ እንደሆኑ የሚገልጹት በዘርና በጎሳ በልተውን በግብር ከፋዩ በጀት ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ አለመግባባትን፣ አዳዲስ የመከፋፈል ትርክቶችን በትምህርት መጥሃፍት ሳይቀር አሳትመው እየጋቱ ትውልዱን ” የተፈጥሮ ሰካራም” አደረጉት። ይህ አካሄድ እንደማያዋጣ የሚሰብኩትን መቀመጫ በማሳጣት፣ በመፈረጅ፣ በማሳስደድ የክፋት ትርክት እንዲንሰራፋ ሆነ። በዚህ ሶስት አስር ዓመት በዚህ መልኩ እየሰከረና እየተላተመ የተሰራ ትውልድ እንደ መስከረም አበባ በፈላበት ወቅት አዲስ ለውጥ መጣ።

ለውጡ ሲመጣ ይኽ እንደ መስከረም አደይ አበባ የፈላውና ” የተፈጥሮ ሰካራም” የሆነው ትውልድ የተዘጋጉት የሚዲያ አውታሮች ሲከፈቱለት የድሮ አልበቃ ብሎት አክቲቪስት፣ ተንታኝ፣ ዩቲኡብ፣ ማህበራዊ አንቂ፣ የፖለቲካ መሪ፣ የመብት ተሟጋች … ተፈለፈሉለት። በነጋ ጠባ ሆነ ብለው ይህን የጥላቻና የዘር አንቡላ እንዲግት ተደርጎ ያደገ ትውልድ ይጠዘጥዙት ጀመር። ዴሞክራሲና የዴሞክራሲ ፍሬዎች በአገራችን የዘርና የጣላቻ እርሾን በመቆስቆስ ማለተም ሆነ።

ይህን አውድ በፍጥነት ወደ ስልጣን ለመስፈንጠር የቋመጡና ያኮረፉ ተጋምደው ምንጩ ከሚታወቅና ከማይታወቅ በጀት ጋር ጋለቡበት። ሲጀመር ሴራና ክፋት ያልተለየው የአገራችን ፖለቲካ ላለፉት ሶስት ዓመታት ከስካርም በላይ ሆኖ አበደ፣ ቆጣሪው ተነቀለ። ደም እየቆጠሩ ማፈናቀል፣ መግደል፣ ገድሎ መጨፍጨፍ፣ ጨፍጭፎ መስቀል፣ ሰቅሎ መጨፈር፣እየጨፈሩ ቪዲዮ ማዘጋጀት፣ ይህንኑ ቪዲዮ በማህበራዊ ገጾች ማሰራጨት የታላቅነት ማሳያ ሆኖ አረፈው። “ትልቅ” የምንላቸው የነበሩ ከቁማሩ ጀርባ ሆነው፣ ላባቸውን በኩራት ነፍተው ” ሂሳቡን እኔ ፣እኛ እናወራርዳለን” ሲሉ መስማትም የስካሩ መገለጫ እንጂ ነወር መሆኑ ቀረ።

ብዙ ወደሁዋላ ሳንሄድ በዚሁ በለውጡ ማግስት ሰው ሆኖ የማህጸን ቆይታውን ያላረጋገጠ፣ እንኳን ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልልና አገር እናቱ ሆድ ውስጥ በወጉ መዝለል ያልቻለ ህጻን ሆድ ተቀዶ ተገድሏል። ልጅ እንዲያይ ተደርጎ አባት ታርዷል። ሚስት እያነባች ባል ተሰይፏል። ተወልደውበት ባደጉበትና የልጅ ልጅ ባዩበት ቀዬያቸው አዛውንቶች ደማቸው ተቆጥሮ ተጨፍጭፈዋል። ከዚህ አንሳር ሲታይ ሌሎቹ ግፎች ቀለል ስለሆኑ እንተዋቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉ ነጻ አውጪና ነጻነት ጠያቂ እንዲሆን ተደረገ። ጠንሳሾቹ በሚለቁት በጀት መተን ክልልና ዞን እንሁን የሚል አጥር የማጠር አባዜ ከዛም ከዚህም አበበ። ከላይ የገለጽነው ዓይነት ትውልድ ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቅ የተሰራበትን እርሾ እየነካኩ በመማገድ ቆመሩበት። አንዳንዶቹን ወደ ጫካ ነዱዋቸውና የምስኪኖችን ጎጆ አንድዶ መሞቅ፣ የምስኪኖችን ከብት መዝረፍና አርዶ መብላት፣ ያሻቸውን መዝረፍ ህጋዊ እንደሆነ አሳዩዋቸው። በሁሉም መስክ የሚፈጸመው ሃፍረት ሊሆን ሲገባ ሚዲያዎቻቸው ይህን ጉድ እንደ ጀብድ ይዘገቡ፣ ማህበራዊ ሚዲያውም እየተቀበለ አከፋፋይ ሆነ። በድምሩ ሁሉም ጉዳይ ለያዥ ለገናዥ ግራ ያጋባ የጨረባ ተስካር ሆነ። የስከነ ልብ ያላቸውን ጎዳ። በርካታ ወላጆች በውጤቱ ከሁሉም ወገን ተጎዱ። ልጆችም ቤተስባቸው ጎድለ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ፍትህ ጠያቂ ሲጮህ፣ የተበደሉ በደሉ እያራዳቸው እያለቀሱ ሲናዘዙ፣ ” እኔም እገሌ ነኝ” የሚሉ የመርዙ ተሸካሚዎች ሃፍረት በማያውቀው የዘር መለክያ እያሰቡ ሲፎለሉ እንደ አገር ” ከሽፈናል” በሚል ተስፋ የቆረጡ ጥቂት አይደሉም።

በዩኒቨርስቲዎች ሳይቀር ጉድ አየን። ፊደል በቆጠሩና ሊቆጥሩ ወደ ሀሁ ሰፈር ያቀኑ በጎሳ ጎራዴ ተባሉ። መርቃና ሰንቃ ልጇን የላከች እናት ሬሳ ተላከላት። አብት፣ እህት፣ዘመድ፣ ቤተሰብ ሃዘን ጠበሰው። ስካሩ እዛም እዚህም ለቅለም የሂዱትን ሳይቀር ከያይነቱ በላ። የብሄር ፖለቲካ!! በዚህ ሁሉ ውስጥ ህዝብ ሲያነባ የዚሁ የዘር ፖለቲካ ጠማቂዎች ቁማራቸውን አጦፉት። አንዳንዶቹ የደም ላይ ንግስና ለማውጅ ካባቸው የተነከረው ደም እየተንጠባጠበ አየር ላይ ተሰቅለው አስረጂና አብራሪ ይሆኑ ነበር። ዛሬም ይኸው ጉዳይ ቢኖርም እንደወትሮው ሳይሆን መልኩን ስለቀየረ ነው “ነበር” ያልነው።

በዚህ ተሟሙቀን ትግራይ ላይ የተፈጸመውን ጉድ ሰማን። የመከላከያ ሰራዊት ላይ የሆነው ሁሉ ከስካርም በላይ የቢጫ ወባ እብደት ተግባር እስኪመስለን ጥርጣሬ ገባን። ግን እውነት ነበር። በምላሹ የሆነው ሆነ። ዝርዝር አይስፈልግም ንብረት ወድመ። ሰው አለቀ። አገር ከፍተኛ ሃብት አውጥታ ያከማቸችውን መከላከያ ህብቷን አጣች። ሕሳናት፣ አዛውንት፣ ሴቶች … የዚሁ እብደት ጣጣ ሰለባ ሆኑ። በሰማነውም ባየነውም እገሌ ከገሌ ሳንል አፈርን።

እስኪ ቆም ብለን እናስብ። በምድር ላይ የሆነና እኛ አገር በዜጎች ላይ ያልደረሰ ምን ክፉ ነገር አለ። ሆድ ተቀዶ ሕጻንን ከመግደል በላይ ምን ክፉ ነገር ሊጠራ ይችላል? ወንድም ወንድሙን እየገደለ ሲጨፍር ከማየት በላይ ምን ሃዘን አለ? ጥጋበኞች ለስልጣን ሲሉ እያጋደሉ አገር ሲወድም፣ ህዝብ ሲሰቃይ፣ ሲሰደ፣ ሲነገላታ፣ሲለምን፣ ይህን ሁሉ ታሪክ ዓለም እየተቀባበለ የችጋርና የድንቁርና ምሳሌ ሲያደርገን አልፈርም።

አክቲቪስት፣ ተንታኝ፣ አስተንታኝና ባለ ሚዲያ ነን የሚሉ በአብዛኛው በሳንቲም ነዋይ ስቃይን በ”ሰበር ዜና” እያዳመቁ ሲነግዱበት ከማየት በላይ ምን አስደንጋጭ ጉዳይ አለ? እንደ ድሮ የህንድ ፊልም ፎቶ እየገጠገጡ፣ እንደ ጀግና የራሳቸውንም እየጨመሩ ሳንቲም የሚሰሩትን በየትናው መስፈሪያ እንያቸው። ከስካርም በላይ ሚዛን የሳቱ “ተንታኞች” ከመንግስትና ከባለስልጣን ስርስር እየሄዱ አንድ ሃረግ እየመዘዙ ” አክተር” ፈጥረው፣ ታሪክ ሰርተውለት፣ በሰሩለት ታሪክ ደም የሚያቃባ ማሳረጊያ የሚያበጁ ክፉዎችን እንዴት አድርገን ስሜታቸውን አውቀን እንረዳ? ስካሩ፣ አሰካከሩ፣ ማበዱና የአብደቱ አይነት ብዙ የሚሆነው ከመላ ጎደል እንዲህ ሲታሰብ ነው።

ዛሬ በትግራይ የአገር መከላከያ ወጣ ገባ፣ የትህነግ ሃይል አሸነፈ፣ የትኩስ አቁሙ ቀልድ ነው … ክርክር መስማት ከሳንቲም ለቀማው በተጨማሪ እሳቱ ውስጥ ለከረሙት የቀጣዩ ጦርነት ማሟሟቂያ ሆኗል። ችጋር በድጅ መሆኑንን እየሰበኩን ጎን ለጎን ስለ ጦርነት ይነግሩናል። ከዚህም ከዚያም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ሆኖ ሳለ ዛሬም መነጋጋር ወንጀል እንደሆነ የሚሰብኩ አሉ።

ጎበዝ ዛሬ በአገራችን ባለው እውነታ ከመንጋገር ውጭ ምን አማራጭ አለን? ኮቪድ እየደፋን ነው። የኑሮ ውድነት እየፈጀን ነው። አንበጣ መታሁ ቀረሁ እያለ ያመረትነውን እያወደመ ነው። ምንም ምክንያት ቢቀርበትም በትግራይ ወንደምና እህቶች እዱር ናቸው። በመተከልና ካባቢው የተፈናቀሉ የጎጆ ያለ እያሉ ነው። አጣዬና አካባቢዋ ወድመው መልሶ ለማንሰራራት አፈር እየላሱ ነው። ኢኮኖሚያችን በባለጠጎቹ ጡንቻ ተጠርቅሞበት እየቃተተ ነው። ከዚህ በላይ ምን እንድንሆን ተፈልጎ ነው መነጋገር ውርደት ሆኖ የሚታየው?

መንግስት ብዙ ጉድለቶች አሉበት። ለመከር፣ ለዘከር፣ ሊወቀስ ይገባል። በተመሳሳይ ሊበረታታና ሊደግፍ በሚገባበት ጉዳይ ማበረታታት የዜጎች ተግባር ነው። በሌሎችም ወገን በተመሳሳይ ይህ ሊደረግ ይገባል። ከዚህ የዘለለው አጓጉል ጀብድ፣ አጓጉል ትዕቢት፣ ከቀድሞው ስህተት ያለመማር በሽታና በዜጎች ችግር መነገገድ ማንም ይሁን ማን ነገ ያስጠይቀዋል።

እርቅ ፍትህን የሚጨፈልቅ ባለመሆኑ ፍትህን የሚያሰፍን ንግግር ማድረግ የጊዜው ጥሪ ነው። ሕዝብ ሰላም ናፍቆታል። በግልጽ በተደረገ የምርጫ ውድድር አዲስ አበባ ላይ አስር የማይሞላ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ በነጋ ጠባ መንግስት እያማ የሽግግር ጊዜ ጠያቂ ሲሆን ” ዞር በል” ማለት ግድ ነው። ከዕንቅላፋቸው በነቁ ቁጥር ችግር የሚጠምቁ ክፉዎች ውይይትና እርቅ ስለማይፈልጉ በመተራመስ እንድንገፋበት እየወተወቱ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል። ልብ ከሌለን አባይም ወንዝ ሆኖ እደገላመጠን ይኖራል። እናስተውል። ካላስተዋልን መገልበጥ ይከተላል። እናቁም!! በረሃብና በደም መነገድ ይብቃ!! ከስካር እንለይ!! አለያ ወደማያበራው ቀውስ እንገባና ያከትምልናል። ይህ የጠላቶቻችንና ይህንኑ እንዲያስፈጽሙ የተመደቡ የኛው ሰዎች ከንቱ ምኞት ብቻ እንዲሆን አድርገን ካላሳየናቸው ለጸጸት የሚሆን ጊዜ እንኳን አይኖርም። አሁንም ልብ እንበል!!

አዋቂዎች፣ ዝም ያላችሁ፣ ስካሩ የሚያስደነብራችሁ ይህን አስፈሪ ዘር ታደርቁና አዲስ ዘር ታዋልዱ ዘንድ ከተደበቃችሁበት ቀፎ ውጡ። አሳብ አቅርቡ። አገር በአሳብ እንጂ በነውጥና በጦርነት እንደምትወድም በእውቀታችሁ አስተምሩ። ይህን እያደረጉ ያሉትን አድንቁ፣ አገዙ … ዛሬ ዝምታ አያዋጣም። የናንተ ዝምታ ሌሎች በመርዝ የተለውሰ አሳባቸውን እንዲሸጡ፣ አገር ላይ እንዲቆምሩ በር ከፍቷል። የሚገርመው በርካቶች ጥሩ አስተማሪ አጥተው አገራቸውን ለሚይፈርሱ እያዋጡ ነው። ይህ ውድቀትና ክሽፈት ይዞን እንዳይሄድ የናንተ መነሳት ግድ ነው ለማለት እንወዳለን!!

ሰላም ለአገራችን ይሁን!!

የኢትዮ12 አቋም

Leave a Reply