ደጀን አለህ – ትልቁ ጥፋት

እናም ወደ ደጀንህ ተጠግተህ ፣ ቂም በቀልን እንደ ትላንቱ ዛሬም ትተህ ፣ ከፍቅር ምክንያታዊ ባልሆነ የዘር ጉዳይ ላይ ተመስርቶ ፣ በጥላቻ ሰክሮ ፣ የካደህ አካል ብርሃንን ከጨለማ ፣ ሰዎችን ከዓሣማ እንዲለይ ጊዜ ትሰጠዋለህ። እኩይ ቢበረክትም ሰውን በጅምላ አትፈርጅምና ከሐጥአን መካከል ላሉ ቅዱሳን ትራራለህ።

24 ሰዓት በወታደር ህይወት – ክፍል 12 (ልዩ) – ደጀን አለህ ።

ትልቁ ጥፋት

ጥፋት አለብህ ከተባለ አንድ ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን ከልብ ከአንጀትህ ትወዳለህ። ይሄ መውደድህ ገደብ የለውም። ፍቅርን ትኖራለህ። እምነትህን ትተገብራለህ። ይህ ጥፋት ሆኖ ይሆን ?

ለከፋፋይ አጀንዳ ቦታ የለህም። ዘር አትቆጥርም። የኔና የሌላ ብለህ አጥር አታጥርም። በአንዱ አከባቢ ያደረኩት በዛ ብለህ ስሌት ውስጥ አትገባም። ሰው ኢትዮጵያዊም ድሪቷ ኢትዮጵያ ከሆነች ምንም ዓይነት በጎ ነገር ከማድረግና ለህልውናው ከመሰዋት አትመለስም። ይህ ጥፋት ነው ወይ ?

ጥፋት አለብህ ከተባለ ወገንህ በምንም ምክንያትና አካለት ተሳስቶ በደል ቢያደርስብህ ቂም አትይዝም። ፋሽስት ላይ ያልተደረገው ክፉ ሁሉ ተደርጎብህም ተመልሰህ የጥፋቱ ምክንያት የሆነውን ደምስሰህ ፣ በጦርነት የተጎዳ ወገንህን እየረዳህ መልሶ ጦርነት ይከፈትበሃል። ጥፋትህ ለእነሱ የመጠላትህ ምክንያት ሲሆን ለሚሊዮኖች ቅዱስ ተግባር የኩራትህ ምንጭ ነው።

አንተ ለህልውና በረሃ ለበረሃ ስትንከራተት ወዝህን የጨርክለት አካል ፣ ድካምህን ጠብቆ ከጎዳህ በተንኮል ተወልዶ አድጎ ጎልምሳ በስተ እርጅና ግጦ ያልጨረሳት ሀገርህን ለማፍረስ ተነስቶ የነበረው ታጥቦ የማይጠራ እድፋም ፣ በክንድ የተወገረው እኩይ ከተበተነበት ለመለቃቀም ስትጥር ከምድር እርጉሞች የሚተባበር ፣ መንገድህ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ፣ ሲገጥምህ ጥያቄ አቁመህ ወደ ውስጥህ ታነባለህ። ጥያቄውን ከእንዴት ? ወደ ለምን ታዲያ የሚል ከፍ ያለ ደረጃ ታሳድገዋለህ።

ጠላት ጠላትነቱ ከማን ጋራ ነው?

አንተ ዘረኝነትን ብትፀየፍም ዘረኞች የገደሉህ በኢትዮጵያዊ ማንነትህ ምክንያት ነው። ከእናት አንጀት ጋር ከሚመሳሰለው ርህሩህነት ጋር ነው። በእኩል ማገልገል መለያህ ነው። ፀባቸው ከህዝባዊ ወገንተኝነትህ ጋር ነው።

በመንደርተኝነት የተለከፉ ፣ በእብሪት የተነፉ ፣ የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የቀጣናው እራስምታቶች የተወለዱበትን ወገን ምርጥ ሌላውን የማይረባ ብለው በአፍ ብቻ ወገናችን ለሚሉት ሰብከውታል። የመጣህለትን መጣብህ ብሎታል። ስብከታቸውን ተቃብሎ አንተ ላይ የተነሳው ሁሉ ጠላትነቱ ከአንተ ጋር ብቻ አይደለም። ከመቶ ሚሊየን ከሚልቀው የሀገርህ ህዝቦች ጋር ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ነውርን ይጠየፋል። ሲቆጣ ነብር ሲራራ እናት ነው። ለቃሉ እና ለእምነቱ ይሞታል። ከሃዲነትን የበላበት ወጪት ሰባሪ ይለዋል። የበላበትን ወጪት የሰበረ ፣ ወርቅ እሴቱን የሸረሸረ ፣ ጠላትነቱ ከአንተ ጋር ሳይሆን ከነዚህ የሀገራችን ህዝቦች መንፈሳዊ ፀጋዎች ጋር ነው። እምነት ፍቅርና ህብር !

አማራጭ የሌለው አማራጭ

በፅናትና በጀግንነት ለሀገርህ ተዋድቀሃል። ከስጋቶች ሁሉ የከፋ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የነበረውን እርኩስ አቅም አሽመድምደህ እንደ ዱቄት በትነሃል። ግን ደግሞ ብናኙን እየናፈቁ ፣ ጥላቻን እየሰነቁ ፣ በአካልህ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍቃሪ ልብህ ላይ ጦር ሲሸቀሽቁ ካልወሰንክ መቼም አትወስንም። አሁን ካልባነንክ መቼም አትባንንም።

አፈር የመሰለውን ፊትህን በፍቅር እጆቹ እያሻሸልህ ፣ የደረቀው ከንፈርህን በውሃ እያረሰ ፣ መጥኖ እያጎረሰ ፣ ድካምህን በብርታት ፣ ሐዘንህን በደስታ የሚቀይር ወገን እንዳለህ መቼም ቢሆን ከጠላት የማያብር ሁኔታው ሲያመቸው የማይቀየር ወገን እንዳለህ ታስብና ትናፍቃለህ። እናም ትወስናለህ።

ውሳኔህን ለመፅናት በፍቅርና በስስት የሚያዩ የወገን አይኖች ፣ በልተህ የጠገብክ የማይመስላቸው እንስፍስፍ አንጀቶች ፣ አይዞህ በርታ የሚሉ አበረታች ቃላት። እንዲሁም ስትቆስል የሚጨርስህ ፣ ስትጠማ መርዝ የሚያጠጣ ሳይሆን ፈተናህን አብሮ የሚጋፈጥ ፣ የድልህ ምስጢር የሆነ ብርቱ ክንድ እንዳለህ ትዝ ሲልህ ውሳኔህ የበለጠ ይፀናል። ምሬትህ የምርና ምክንያታዊ ይሆናል።

እናም ወደ ደጀንህ ተጠግተህ ፣ ቂም በቀልን እንደ ትላንቱ ዛሬም ትተህ ፣ ከፍቅር ምክንያታዊ ባልሆነ የዘር ጉዳይ ላይ ተመስርቶ ፣ በጥላቻ ሰክሮ ፣ የካደህ አካል ብርሃንን ከጨለማ ፣ ሰዎችን ከዓሣማ እንዲለይ ጊዜ ትሰጠዋለህ። እኩይ ቢበረክትም ሰውን በጅምላ አትፈርጅምና ከሐጥአን መካከል ላሉ ቅዱሳን ትራራለህ።

ደጀን አለህ። በፍቅር ደግፎ ጥንካሬን ያበዛዋል። ሐዘንህን ይሰርዘዋል። አንተም በብቃት ላይ ብቃት ፣ በፅናት ላይ ፅናት ፣ ከአበው በወረስከው ጀግንነት ላይ የላቀ ጀግንነት ፣ ጨምረህ ለትላንት ሳይሆን ለነገ ጦርነት ትዘጋጃለህ። ደግሞም ታሸንፋለህ። ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን አርበኞች እንጂ የባንዳዎቹ ውላጅ አይደለህም።

እኛም እንጠይቃለን

ጥያቄው ለአንተ አይደለም። አንተማ ከልብ ሠርተሃል። ያለህን ሰጥተሃል። ግን ደግሞ ተከድተሃል። ከዚህ የተነሳም ለምን ? ብለህ ጠይቀህ ወስነሃል። አሁን ከፊትህ ከባባድ ሥራ ከኋላህ የወገን ባለጋራ የለብህም። በተገቢው ሠዓት በተገቢው ቦታ ወገንህን ተቀላቅለሃል።

የኛ ጥያቄ በአጋጣሚ ብዕር የጨበጡ አደባባይ የወጡ መፃፍ ማንበብና መናገር ስለቻሉ ብቻ ውሳኔህን ለማንጓጠጥ ያልሆነ ትርጉም ለመስጠት ምናልባትም በዚህ አ ጋጣሚ የተለየ ትርፍ ለማግኘት ለሚሯሯጡ ቁስልህ ላይ የነገር ካራ ለመክተት ለሚሞክሩ የስም ኢትዮጵያውያን ነው።

ሁለንተናውን ሀገሬ ለምትላት ሀገር ለሰጠ እምነቱ ላልተለወጠ የብሔራዊ ዓርማዋ ዘብ የሆነው ወንድምህ የገጠመው ቢገጥምህ የሆነውን ብትሆን ያጣውን ብታጣ ምላሽህ ወይም ምላሻችሁምን ይሆን ነበር። መልሱን ለእናንተ ፡፡

ሠላም ለኢትዮጵያ ፡፡ ድል ለጀግናው የህዝብ ልጅ !

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ

Leave a Reply