የ2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ሶስቱ አገራት በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት ነው – ኢ/ር ጌዲዮን

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ሶስቱ አገራት በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት መሆኑን የግድቡ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ገለጹ።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እኤአ በ2015 በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን ካርቱም የህዳሴ ግድብ ድርድርን አስመልክቶ የመርሆዎች ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።የመርህ ስምምነቱ አስር አንቀጾችን ያካተተ ሲሆን የሶስቱንም አገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ይታወቃል።

ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በዚሁ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በፈረሙት የመርህ ስምምነት መሰረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው ገልጸዋል።

በግድቡ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሶስቱም አገራት ባለሙያዎች አስቀድመው የተስማሙባቸው ነጥቦችም በዚሁ የመርህ ስምምነት መካተታቸውን ኢንጅነር ጌዲዮን አስታውሰዋል።የመርሆዎች ስምምነቱ አገራቱ ስምምነቱን በተፈራረሙ በ15 ወራት ውስጥ ሁለት ጥናቶች እንዲካሄዱ ቢደነግግም ግብጽና ሱዳን ጥናቱ እንዳይካሄድ በያዙት ግትር አቋም ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግብጽና ሱዳን የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ የሚሰጡትን የተዛባ መረጃ ሊመረምር እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡የግድቡን የውሃ ሙሌት የተመለከቱት የመርህ ስምምነቱ አንቀጾች በግብፅና ሱዳን የውሃ ባለሙያዎች የሚታወቁና ከመግባባት ላይ የተደረሰባቸው መሆናቸውንም አንስተዋል።


    See also  የበርሊን ማራቶን ባለማዕረግ ትግስት እነ ዱቤ ጂሎ ቢሳተፉ ታዝረከርካቸው ነበር

    Leave a Reply