ምህላ – በባሕር ዳር


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተባባሪነት ለ3 ቀናት የሚቆይ የፀሎትና ምህላ ፕሮግራም ትናንት በባሕር ዳር ከተማ በመስቀል አደባባይ ተጀምሯል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የባህር ዳር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሐም እንዳሉት በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በአገርና በዓለም ደረጃ እየከፋ የመጣውን ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ክፍፍል፣ ጥላቻ፣ የደዌና ቂም ማስወገድ የሚቻለው በፀሎት ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ወር በወሰነው መሰረት ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 4/2013 ዓም ድረስ በመላ ኢትዮጵያ በገዳማቱ በአድባራቱ፣ በገጠር አብያተ ክርስቲያናት ምህላና ፀሎት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከሐምሌ 2 እስከ ሐምሌ 4 /2013 ዓ ም የሁሉም ገዳማት፣ አድብራትና ቤተክርስቲያናት ካህናት፣ ሊቃውንትና ምዕመናን ያሉበት የማጠቃለያ የምህላና የፀሎት ፕሮግራም በባሕር ዳር ከተማ መዘጋጀቱንም አቡነ አብርሐም ተናግረዋል፡፡
በሶስት ቀን ቆይታ ምዕመናንና የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት እንደሚያመጣልን እግዜአብሔርን የምንለምንበት ጊዜ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
አቡነ አብርሐም በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋሪያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ገላትያ ሰዎች በምዕራፍ 3፣1 የፀፈውን ጠቅሰው “አዚም ያደረገባችሁ ማነው ?” የሚለውን ጠቅሰው አስተምረዋል፡፡ ማነው ፍቅርን ያሳጣችሁ፣ ጥላቻን የዘራባችሁ፣ክህደትን፣ ኑፋቄን፣ ጥርሬን ያሰረፀባችሁ?፣ “አዚሙ ከቤተሰብ እስከ ጎረቤት፣ ከጎረቤት እስከ ሀገር፣ ከሐገር እስከ መላው ዓለም አዚም ሰፍኗል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ክፉ አዚም መያዟን አክለዋል፡፡ ሁላችንም በዘር፣ በጎጥ፣ በክፍፍል፣ በጥላቻ፣ በደዌና በቂም አዚም ተለክፈናልም ነው ያሉት፡፡ አብዛኛው የትውልዱ ክፍል ስነምግባሩ የተበላሸ፣ ትዕዛዝ የማይቀበል በፈተና ውስጥ ያለ ነውም ብለዋል፡፡ እግዜአብሔር ይባርክህ ከመባል ፋንታ እድሜህን ያሳጥረው የሚባል ትውልድ እየተፈጠረ ነው የልጅ አዋቂዎች እንዳሉ ሆኖ ሲሉም ትዝብታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከአዚሙ የሚገላግለን ፍቱን፣ እውነተኛ መድኃኒት ፀሎት፣ እግዚአብሔርን ከልብ መቅረብ ብቻ እንደሆነ ለምዕመኑ አስተምረዋል፡፡
የምህላና ፀሎቱ አስተባባሪ ሊቀ ትጉሐን አማረ ጥበቡ ፕሮግራሙ እሰከ እሁድ የሚቀትል ሲሆን፣ ሰኞ እለት ደግሞ ነዳያንን በጋራ የመመገብ ስነስርዓት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ዓለምነው መኮንን (ከባሕር ዳር) DW

Leave a Reply