ሲመሽ – ሜሲ በአገሩ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ ደመቀ

ሜሲ በተለያዩ ጊዜያት አገሩን ለድል አለባቃቱ እንደ ጉድለት ይሰማው ነበር። ” ለገሩና ለክለቡ እኩል ዋጋ አይከፍልም” በሚልም የሚተችበትም ጊዜ ነበር። ” በቃኝ” ሲል ለብሄራዊ ቡድን ላለመጫወት የተናገረበት ጊዜም ይታወሳል። ሁሉም አልፎ ዛሬ ሚሲ በ34 ዓመቱ አገሩን አድምቆ በደስታ ሰክሯል። ብራዚልን አሸንፈው ዋንጫ እንዲወስዱ ዳኛው ፊሽካ ሲነፉ ሜሲ ተዘረረ። ባልደረቦቹ እንዳይጎዳ አድርገው ወደ ሰማይ እያጎኑ ቀለቡት። አልቃሻው ኔማር በበኩሉ አነባ። ኳስ እንዲህ ናት። የቢቢሲን ዘገባ ከታች ይመልከቱ።

ሊዮኔል ሜሲ በኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ፍልሚያ ሃገሩ አርጀንቲና ብራዚልን መርታቷን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ሁለቱ ሃገራት በግዙፉ ሪዮ ማራካኛ ስታዲዬም የፍፃሜውን ጨዋታ አድርገው አርጀንቲና በዲ ማሪያ ጎል አንድ ለባዳ ረትታለች። የ34 ዓመቱ ሜሲ የጨዋታውን ፍፃሜ የሚያበስረው ፊሽካ ሲነፋ በደስታ መሬታ ላይ ከመውደቁ የቡድን አጋሮቹ እየሮጡ ሲከቡት ይታያል።

ሜሲ ሃገሩ አርጀንቲና ዋንጫ እንድታገኝ 10 ጊዜ ትላልቅ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳካለት ዘንድሮ ነው። የስድስት ጊዜ የዓለም ኮከብ ሽልማት ባለቤቱ ሜሲ ሃገሩ አርጀንቲያ ከ28 ዓመታት በኋላ ዋንጫ እንድታነሳም አስችሏል።

አንሄል ዲ ማሪያ የማሸነፈያ ጎል በማስቆጠር የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል። ሜሲ በፍፃሜው ጨዋታ ጎልና መረብ የሚያገናኝበት አንድ ወርቃማ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የውድድሩ አዘጋጅ የሆነችው የባለፈው ኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ባለድል ብራዚል በሜዳዋ ዋንጫ የማንሳት ሕልሟ ሳያሳካላት ቀርቷል።

በሜሲ ተቃራኒ 10 ቁጥር ለብሶ የሚጫወተው ኔይማር በጨዋታው ፍፃሜ በሐዘን አንገቱን ሲደፋ ታይቷል። ኔይማር፤ ብራዚል ያለፈውን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ስታነሳ በጉዳት ምክንያት የቡድኑ አባል መሆን አልቻለም ነበር።

ባርሴሎና እያሉ ለአራት ዓመት አብረው የተጫወቱት ኔይማርና ሜሲ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ረዘም ላለ ደቂቃ ተቃቅፈው ታይተዋል። በኮቪድ-19 ምክንያት ጨዋታውን መታደም የቻሉት 7 ሺህ ሰዎች ብቻ ቢሆንም በውድድሩ ለጀመሪያ ጊዜ ነው ተመልካቾች ገብተው መታደም የቻሉት። በወረርሽኙ ምክንያት በአንድ ዓመት የዘገየው የኮፓ አሜሪካ ፍልሚያ አርጀንቲናና ኮሎምቢያ እንዲያዘጋጁት ነበር የታሰበው።

ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት አዘጋጇ ብራዚል ትሁን ተብሎ ቢወሰንም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ውሳኔው ትክክል አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ቀርበውበት ነበር። ሜሲ በአራት ዓለም ዋንጫዎችና በስድስት ኮፓ አሜሪካ ውድድሮች ሃገሩ አርጀንቲናን ወክሎ ተጫውቷል።

10 የላሊ ጋ ዋንጫ፣ 4 ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ባለድል እና የስድስት ባለንደኦር ባለቤት የሆነው ሜሲ በዓለም አቀፍ መድረክ ምንም ድል አላገኘም የሚል ትችት ይቀርብበት ነበር ከአርጀንቲና ጋር ድል ማጣጣም ያልቻለው ሜሲ በአንድ ወቅት ራሱን ከቡድኑ ማግለሉን አስታውቆ መልሶ መጫወት መጀመሩ ይታወሳል።

ከባርሴሎና ጋር ያለውን ውል ያጠናቀቀው ሜሲ ቀጣይ መዳረሻው የት ነው የሚሆነው የሚለው አሁንም አነጋጋሪ ሆኗል። ኳታር በምታዘጋጀው የ2022 ዓለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋል አይሳተፍም የሚለውም ሌላኛው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። ከቢቢሲ የትወሰደ

ፎቶ ቢቢሲ ስፖርት

Leave a Reply