በአሸባሪው የትህነግ ተጠርጣሪ አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሠረት ተገለጸ።

በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ላይ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ ለመውጣት ሲጣጣሩ የነበሩ 42 ተጠርጣሪ የአሸባሪው ትህነግ አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ጸጋዬ አስታወቁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ በተለይ እንዳስታወቁት፤ 42ቱ ተጠርጣሪ የአሸባሪው ትህነግ አባላት በቀዳሚ ምርመራና በዋና ምርመራቸው ወቅት ጉዳያቸውን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

በተለይም ያልሆኑ ሰበባሰበቦችን በመቃረም የፍርድ ሂደቱ ዘገየ ለማስባል መሞከራቸውን ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ ፣ በሕግ አግባብና በፍትሕ መንገድ ሳይሆን በሌሎች ግፊቶች ነጻ እንወጣለን በሚል ሒሳቦችን ሠርተው ከእስር ለመውጣትም ሲጣጣሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ምርመራው በጣም ከታሰበው በላይ በፍጥነት በመጠናቀቁ ይህ ስሌታቸው እንዳልሠራ አመልክተዋል ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሠሩት ልክ ሕግ ተገቢውን ፍርድ ይሰጣቸዋል ያሉት አቶ ፈቃዱ፤ በቀጣዩ ሳምንት ተጠርጣሪዎቹ ለክስ እንደሚቀርቡ አመልክተዋል፡፡

ክሱ የወንጀል ክስ በመሆኑም ፍጥነቱ ምን ያህል ተቀናጅቶ እንደተሠራበት የሚያመላክትም ነው ብለዋል ፡፡ በብዛት በምርመራና በሰበባሰበብ እንዲሁም በምስክር ማሰማት ሂደት ችግሮች ባያጋጥሙ ኖሮ ከዚህ ባነሰ ጊዜም ክሱ ይመሠረት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው

Leave a Reply