የመንግሥት ሚዲያዎች ፍትሃዊነታችንን አጉድላችሁብናል – ብርቱካን

“ዛሬ እዚህ የምትቀርጹን የመንግስት ሚዲያዎች በጣም በትህትና ልነግራችሁ እፈልጋለሁኝ። የመንግስት ባለሥልጣናት ኮታቸው ላይ የተሰካው ማይክራፎን የማይወልቅ ይመስል ሌት ተቀን የእነሱን ካምፔን እና ቅስቀሳ ስታስተላልፉ ቆይታችሁ የተቃዋሚዎችን 10 እና 15 ደቂቃ ማድረጋችሁ ፍትሃዊነታችንን አጉድሎብናል። እንዳላየ ያለፍነው ግማሹ የኛ ሥልጣን ስላልሆነ ነው። የእኛን ስልጣን እንደምናከብር የሌሎችንም እናከብራለን” የምርጫ ውጤት በማሳወቂያ መርሃግብር ላይ ይህንን የተናገሩት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ሰብሳቢዋ “ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በምርጫ ብቻ ስልጣንን የምታሸጋግር አገር መሆኗን አሳይታለች” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውጤት ማሳወቂያ መርኃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። መርኃ-ግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ምርጫው እንዲሳካ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

የዛሬው መድረክም ቦርዱ የሰራቸውን ስራዎች የሚያስተዋውቅበት ብቻ ሳይሆን ከሂደቱ ሁሉም ትምህርት የሚያገኝበት እና ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በምርጫ ብቻ ስልጣንን የምታሸጋግር አገር መሆኗ በድጋሚ የሚታይበት ሂደት ነው ብለዋል።

ምርጫው ቀላል በሚባል ሁኔታ ውስጥ የተደረገ አለመሆኑን ያስታወሱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢዋ ኢትዮጵያ በበርካታ ውጣውረዶች ውስጥ ሆና፣ ዜጎች በስጋት ውስጥ ሆነው ችግሮችን በመቋቋም ዛሬ ላይ ተደርሷል ብለዋል። ምርጫውን በመታዘብ የተሳተፉው 176 አባላት ያሉት የሲቪክ ማህበራት ህብረት ለምርጫ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ከበደም በድምፅ መስጫ ቀን ለ2 ሺህ 400 በላይ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በማሰማራት በ2 ሺህ 500 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ለመታዘብ መቻሉን አስታውቀዋል።

የደባርቅ ምርጫ ክልል ኃላፊ የሆነችው ሳዲያ ዳውድም በመድረኩ ላይ ልጇን በጀርባዋ እንዳዘለች የነበራትን ልምድ ለተሳታፊዎች አጋርታለች።

በመድረኩ የምርጫ አስፈፃሚዎች የነበራቸውን ልምድ እና ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል። የምርጫ ዝግጅት ሂደት ጀምሮ የምርጫ ቁሳቁስ በየምርጫ ጣቢያዎች እንዲደርስ ማድረግ ፈታኝ ስራ እንደነበር በምርጫ ቦርድ የመራጮች እና ስነ ዜጋ ትምህርት ክፍል ሀላፊዋ አርማዬ አሰፋ ተናግረዋል። የምርጫ ቦርድ ሰራተኞች የህዝብን አደራ ለመወጣት ሌት ተቀን በመስራት የኢትዮጵያን ጠንካራ የስራ ባህል አሳይተዋል ብለዋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply