December 4, 2021

የዓለም ጆሮ ዳባ ማለትና – ህጻናትን ለጦርነት የሚማግደው የትህነግ ወንጀል

ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ አሰቃቂ ወንጀል እየፈጸመ ያለው አሸባሪው ህውሃት ለአለም ፍርድ ቤት በማቅረብ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን አመለከቱ፡፡

የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህውሃት ጁንታ በማፍረስና ዜጎችንና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን ተከትሎ በሽብርተኛነት መወሰኑን ይታወሳል፡፡

ይህ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀመው የህወሃት ጁንታ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ እያለ በመዛት በእኩይ ድርጊቱ ቀጥሎበት እንዳለ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር አቶ አብይ ደምሴ እንዳመለከቱት፤ ሽብርተኛው ህውሃት ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈጸመ ባለው ከባድ ወንጀለ በአለም አቀፍ ህግ መሠረት ለፍርድ መቅረብ አለበት።

የመንግስት ደጋፊዎች ናቸው በሚል ንጹሃንን ዜጎች እየጨፈጨፈ እንደሚገኝ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የጠቆሙት ምሁሩ፤ ይህን ወንጀል ለተባበሩት መንግስታትና ለአለም ሃያላን ሀገራት በአግባቡ በማሳወቅ ሽብርተኛውን ቡድን ለአለም የጦር ወንለኞች ፍርድ ቤት ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ዲፕሎማቶች በአለም አቀፍ አደባባይ በፀጥታው ምክር ቤት ያገኘነውን ድል የቡድኑን ማንነት በአለም አደባባይ በማጋለጥ ሀገር አፍራሽነቱን ማሳወቅና ተጠያቂ ማድረግ ይገባል፡፡

” ዳሩ ከተነካ መሀሉ ዳር የማይሆንበት ምክንያት ስለሌለ ሀገርን ከሽብርተኛው ቡድን ለማዳንና ለማሻገር ሁሉም የሚረባረብበት ወሳኝ ወቅት ነው” ብለዋል፡፡

ሌላው የህግ ምሁር አቶ ድንቁ ዘውዱ፤ መንግስት የውጭና የውስጥ ሴራ እየናደ የመጣበትን ዲፕሎማሲያዊና እውነት የማሳወቅ ጉዞ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

አሸባሪው ቡድን እየፈፀመ የሚገኘውን ወንጀል በመከላከል ሀገርን ከማፍረስ ሴራ ለመታደግ ሁሉም አንድነቱን አጠናክሮ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ህውሃት እየፈፀመ የሚገኘውን ወንጀል በአንድ ክልል የተናጠል መግለጫ ሣይሆን የፌደራል መንግስትና የሁሉም ክልሎች ጉዳይ መሆኑን በመረዳት እየተሰጠ ያለው አዎንታዊ ምላሽ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድነቷን የጠበቀችና የተሻለች ሀገር ለመገንባት የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

በይገባኛል የሚነሱት አካባቢዎች ጉዳይ በህግ አግባብ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመው፤ይህን ተገን በማድረግ ሀገር ለማተራመስ የሚደረገው የአሸባሪው ህውሃት ሴራ በማክሸፍ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ችላ ተብሎ በዚህ ከቀጠለ ችግሩ የአንድ ክልል ብቻ ሣይሆን የሁሉም ዜጎች ጉዳት ሊሆን ስለሚችል አንድነትን ጠብቆ ቡድኑን ስርዓት በማሲያዝ ለህግ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህር ሱራፌል ጌታሁን ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በሌሎች ክልሎች የሚገኙና ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙት ጭምር ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት በፍጥነት መረጋገጥ አለበት፡፡

ዜጎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ በማጠናከር የሀገርን ህልውናና ዳር ድንበር የማስከበሩ ተግባር ስኬታማ እንዲሆን መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡

በተለይ የምዕራባዊያን ሀገራትና መገናኛ ብዙሃን መንግስትን በሃሰት ለመክሰስ የሚጣደፉትን ያህል ህጻናት ለጦርነት በማሰለፍ አለም አቀፍ ወንጀል እየፈፀመ የሚገኘውን አሸባሪ ቡድን ለህግ እንዲቀርብ ህሊናዊ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሐምሌ 8/2013 (ኢዜአ)

Leave a Reply

Previous post መንግስት ነጭ ወያኔዎችን ሊያባርር፣ የተኩስ አቁም ውሳኔውን ሊቀይርና የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ጫፍ መድረሱን ይፋ አደረገ
Next post ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ
Close

LATEST

%d bloggers like this: