ሲዳማ ወደ ግዳጅ ቀጠና ከተተ! አጫጭር ዜናዎች

የሀገርን ሰላም ለማስከበር የተንቀሳቀሰው የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ግዳጅ ቀጠና መድረሱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል የቀረበለትን ሀገራዊ ጥሪ በከፍተኛ ደስታ በመቀበል እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት የአሸባሪውን ትህነግ ጁንታ ሴራ ለማክሸፍ በግዳጅ ቀጠና መድረሱን የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅሶ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡

ኢራቅ

በኢራቅ በኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ ማዕከል በተነሳ እሳት ከ50 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ፡፡ አደጋው ናሲሪያ በተባለችው ከተማ በሚገኘው አል ሁሴን ሆስፒታል የደረሰ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በሆስፒታሉ የሚገኝ ኦክስጅን መፈንዳት ለአደጋው መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡ ማገገሚያ መዕከሉ ከሶስት ወራት በፊት የተገነባ ሲሆን፥ 70 ታካሚዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

አደጋው በደረሰበት ወቅትም 63 ታካሚዎች ሆስፒታሉ ውስጥ ነበሩ ተብሏል፡፡ አደጋውን ተከትሎ በአካባቢው ተቃውሞ መቀስቀሱን የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡

በደቡብ አፍሪካ

በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው ግጭት 72 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የሀገሪቱ ፍርድ ቤት እንዲታሰሩ ውሳኔ ማሳለፉን በመቃወም በተነሳው ግጭት እና ሁከት የዜጎች ህይወት ሲያልፍ የንብረት መውደም እና ዝርፊያም እየተካሄደ ነው፡፡

ይህን ብጥብጥ ለማስቆም መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ብዙዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በሃገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን የንጹሃን ዜጎች ግድያ እና የንብረት መውደም እንዲሁም ሁከት አውግዟል፡፡

የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት በመግለጫቸው፥ በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እና በፍጥነት ወደነበረበት እንዲመለስ ጥሪ አቅርበዋል፡

አሜሪካ

የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ባደረገው መረጃ፥ በአሜሪካ ለወራት እየቀነሰ የነበረው የኮቪድ19 ቫይረስ ስርጭት መጠን ካለፉት ሶስት ሳምንታት ወዲህ እንደገና እያሻቀበ ነው፡፡የዴልታ ዝርያ ያለው የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት እየተሰራጨ መምጣት፣ የክትባት አቅርቦት መዘግየት እና በአሜሪካ የነጻነት ቀን ላይ ብዛት ያለው ህዝብ አደባባይ መውጣቱ ለቫይረሱ ዳግም መጨመር ምክንያት ሳይሆን አልቀረም ተብሏል፡፡

ሰኞ ዕለት ብቻ 23 ሺህ 600 ሰዎች በቫይረሲ ሲያዙ ፥ ይህም በፈረንጆቹ ሰኔ 23 ቀን ከተመዘገበው 11 ሺህ 300 ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ ሆኖ ታይቷል፡፡ማይን እና ደቡብ ዳኮታ ግዛቶች ቫይረሱ በስፋት የተስፋፋባቸው ቦታዎች ሆነዋል፡፡

የቫይረሱን መስፋፋት ተከትሎም የተከተቡም ሆኑያልተከተቡ ዜጎች ማስክ እንዲያደርጉ፣ ከሌሎች ሀገራት የሚገቡ መንገደኞችም ለ10 ቀናት በማቆያ እንዲቆዩ፣ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች ህዝባዊ ስብሰባዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች እንዳይገኙ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ስለ ኮቪድ19 የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ዜጎች ከማጋራት ሆነ ከመፃፍ እንዲቆጠቡ መመሪያ ወጥቷል፡፡

የጆን ሆፕኪንስ አሁናዊ መረጃ እንደሚያመላክተው እስከ ረቡዕ ድረስ 33 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች በኮቪድ19 ሲያዙ፥ 607 ሺህ 763 ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን

Leave a Reply