በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!
ከ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
መንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የቢሆንስ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario) መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የእለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራክት እና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል) በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (Scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (Scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ሕወሃት የሚያደርሳቸውን ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱ እና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ሕወሃት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉ እና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው በአጭር ጊዜ ከሕወሃት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ሕወሃት ያደረሳቸውን ወንጀሎች እና የሚፈጽማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎች እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።
መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለሕወሃት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆም እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሕወሃትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ እና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።
ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንጠይቃለን፥
- በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ሕወሃት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ሕወሃት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
- በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ሕወሃት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ሕወሃትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍ እና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
- አሁን ያለው ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
- የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
- የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግ እና ሕወሃት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመል እና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
- ዜጎች ለሕወሃት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነት እና ሕይወቱን ለመሰዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
- ሕወሃትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበት እና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።
ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ