የህውሃት አሸባሪ ቡድን ሰብዓዊነት የጎደለው ግፍ እየፈፀመብን ነው — የኤርትራ ስደተኞች

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ህጎችን በመጣስ ሰብዓዊነት በጎደለው መንገድ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈርና አፈና እየፈጸመባቸው መሆኑን የኤርትራ ስደተኞች ገለጹ።

አዲ ሃሩሽ፣ ማይአይኒ፣ ህንጻጽና ሽመልባ ከተባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት የሸሹ ስደተኞቹ ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ እየገቡ ናቸው።

ከስደተኞቹ መካከል አቶ ሰለሞን ተስፋማርያም ለኢዜአ እንደተናገሩት ህንጻጽና ሽመልባ በተባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች በርካታ ስደተኞች መገደላቸውን ሰምተዋል።

በተጨማሪም ማይአይኒ በተባለው መጠለያ ጣቢያም ሰሞኑን ስድስት ስደተኞች መገደላቸውን ጠቅሰው፤ ከሟቾች ውስጥ ሱሌማን መሐመድ የተባለ ስደተኛ ሥርዓተ ቀብር ብቻ ሲፈጸም፣ሌሎቹ ስደተኞች እስከ አሁን እንዳልተቀበሩ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ለስደተኞች ተብሎ የመጡ መድኃኒትና የህክምና መገልገያዎችን በመዝረፉ ሶስት ስደተኞች በሕክምና እጦት መሞታቸውንና ሁለት ወላድ እናቶች ደግሞ በስቃይ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በማይ አይኒ መጠለያ ጣቢያ ሰሞኑን ታፍነው የተወሰዱ ከ70 በላይ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታም እንደማይታወቅ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

”እኛ ስደተኞች እንጂ የማንም ፖለቲካ አጋዥም ተቃዋሚና ቀስቃሽ አይደለንም፤ ስደተኛ በሰላም መኖር አለበት፤ የአለም አቀፍ ማሕብረሰብም ይህን ህገ-ወጥ ቡድን ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አጥብቆ ሊያወግዝ ይገባል” ብለዋል፡፡

”በህወሃት አሸባሪ ቡድን በስደተኞች ላይ ለመናገር የሚከብድ ብዙ በደልና ግፍ ተፈጽሞብናል” ያሉት ደግሞ ሌላው ኤርትራዊ ስደተኛ አቶ ግደይ ተስፋዝጊ ናቸው፡፡

”በርካታ ሴት ስደተኞች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል” ያሉት አቶ ግደይ፣ ከአራት ዓመት አድሜ በታች የሆኑ ህጻናት ሳይቀሩ ታፍነው ተወስደዋል ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡

”በመሆኑም የስደተኞች ደህንነት ወደ ሚጠበቅባቸው ስፍራዎች በአስቸኳይ ተጓጉዘን የምንጠለልበትን መንገድ መንግሥት ያመቻችልን” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

”ስደተኛው በግፍ እየተገደለ እየተጨፈጨፈና እየተዘረፈ ነው” ያሉት ደግሞ ከህንጸጽ መጠለያ ጣቢያ ከአሸበሪ ቡድኑ ጥቃት አምልጠው ደባርቅ ከተማ የገቡት አቶ ገብረተንሳይ ዳዊት ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ህክምና፣ ምግብና የውሃ አቅርቦት እንደሌለ ጠቅሰው፤ “የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎችም ስደተኞችን ለማስገደል በመጠለያ ጣቢያዎች ከባድ መሳሪያዎች ጭምር ጠምደዋል” ብለዋል፡፡

”የህወሃት እኩይ ድርጊት የጨለማ ታሪክ ትቶ የሚያልፍ ነው” ያሉት አቶ ገብረተንሳይ ”እኛ የማንም ፖለቲካ ተከታይ አይደለንም፤ ዓለም አቀፍ ስደተኞች ነን” ብለዋል፡፡

የማይፀምሪ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ በሪሁን በበኩላቸው በትግራይ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ስደተኞች እየተገደሉ፣ እየተደፈሩና ንብረታቸው እየተዘረፈ መሆኑን ለማስተባባሪያው መረጃ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

”በአሁኑ ወቅት ወደ ደባርቅና አዳርቃይ ከተሞች በርካታ ስደተኞች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው እየመጡ ናቸው”ያሉት አስተባባሪው፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ ካምፖች ስደተኞቹን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

“በቀጣይ ቀናትም ከአዲሃሩሽና ከማይአይኒ የስደተኞች መጠለያዎች ከ25 ሺህ በላይ ስደተኞች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

ስደተኞቹን ከስጋት ለማላቀቅም በዳባት ከተማ ዓለም ዋጭ በተባለው ሥፍራ ከ10 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚያስተናግድ መጠለያ ለማዘጋጀት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ ENA

Leave a Reply