የኦሮሚያ ክልልን ሰላም ያውክ የነበረውን የጥፋት ሃይል መቆጣጠር መቻሉን ፖሊስ አስታወቀ

የጸጥታው መዋቅር ተጠናክሮ በመስራቱ የኦሮሚያ ክልልን ሰላም ያውክ የነበረውን የጥፋት ሃይል መቆጣጠር መቻሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በጅማ ከተማ ለጸጥታ ሃይል አባላት የምስጋናና የእውቅና መርሃ ግብር ተካሄዷል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ቅጥረኛና ከሃዲው ሃይል በክልሉ ተሰግስጎ ሰላም ሲያውክ ነበር።

የጸጥታ ሃይሉ ባደረገው የተጠናከረና የተደራጀ እንቅስቃሴ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ተላላኪው ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ከልማት ወደ ኋላ ለማስቀረት ከውጭ ጠላቶች ጋር ተባባሪ ሆኖ ሰላም በማደፍረስ ሲሰራ እንደነበር አንስተው፤ “አሁን ግን ያንን መግታት ተችሏል” ብለዋል፡፡

ተላላኪው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ንጹሃን ዜጎችን እያጠቃ ስጋት በመፍጠር የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ ሲሰራ እንደነበርም ተደርሶባቸዋል ሲሉ አውስተዋል፡፡

“ከአሸባሪው የህወሐት ሃይል አጀንዳ ተሰጥቶትና በጀት ተመድቦለት ሲንቀሳቀስ የነበረውን ተላላኪ ሃይል የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ የቻለው የጸጥታው መዋቅር ምስጋና ይገባዋል፤ ለወደፊቱም የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በተጠንቀቅ መቆም ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በአካባቢው ያለው የፖሊስና ሌላውም የጸጥታ ሃይል የትኛውንም የጥፋት እንቅስቃሴ ቀድሞ መከላከል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተመክሮበታል እንደ ሀገርም አቅጣጫ ተቀምጧል በማለት አመላክተዋል፡፡ (ኢዜአ)

Leave a Reply