የሞት አዋጅ፣ የአስከሬን ሻሞ ይቁም!!

  • የህሊና ግሽበት፣ የልቡና መድረቅ፣ የሃዜነታችን መንጠፍ፣ የመልካምነታችን መክሰም … ወዘተ የሚባለው ፉከራ አይሰራም። አልገሸብንም፣አልነጠፍንም፤ አልደረቅንም፣… ወዘተ!! ቢሆንማ ኖሮ እንደ ድግሱና እንደ ውትወታው ዛሬ ላይ ባልደረስን ነበር። አንድ የማይታበለው ሃቅ ግን እጅግ ጥቂቶች ገሽበው፣ ደርቀውና ታውረው፣ እንዲሁም በስልጣን ጥማት ሰክረው ወደ ገደል እየገፉን ነው።
  • አሁን የምንናገረው ያለነው ስለ ተራ የዶሮ ቀይ ደም አይደለም። የክቡር የሰው ልጆች ደም ነው። የናቶች፣ አባቶችና ሕጻናት ደም ነው። አገርን ያለተስፋ የሚያስቀር ደም ነው። ላለፉት ሶስት ዓመታት በመመሪያ ስለፈሰው የሰው ልጅ ደም ነው። በየስፍራው ደመ ከልብ ሆነውና ተክደው የተገደሉ ደም ነው። አላስተዋልንም እንጂ ላለፉት ሶስት ዓመታት የንጹሃን ደም በየስራቻው እየጮኸ ነው። የዚህ ሁሉ ሳያንሰን ትግራይ ላይ ማእከሉን ያደረገው ጦርነት በውል የማይታወቅ ደም አፍሧል። በቃ ሊባል የገባል!!
  • ከቤት ተጠርጎ ደጅ እንደተከመረ ቆሻሻ ከሃጂዎች፣ ባንዳዎች፣ ለሆዳቸው ያደሩና አገሪቱን የዘረፉ እንግዴዎች ሳይሆኑ አገር ቤት ያሉ ወገኖች ይህ እልቂት እንዲቆም ጥበብ የተሞላበት እንቅስቃሴ መጀመር ይገባቸዋል። የትግራይ ልጆችና ምሁራኖች ወይም ቀና አሳቢዎች ቅድሚያ ሰላም እንዲወርድ ሊሰሩ ጊዜው አሁን ነው። የሕጻናት እልቂትና የወላጆች መከራ እንዲያጥር ከዩሉንታና ያልተገባ ፍላጎት በመሸሽ ለሰላም ሊሰሩ ይገባል።

የኢትዮ 12 አቋም

ኢትዮጵያዊያን መቶ ሃያ ሚሊዮን እንገመታለን። ኢትዮጵያዊያን አብሮ በመኖርና በመተዛዘን እንታወቃለን። ከሁሉም በላይ ” እነ እገሌ እሳት እንዳይጭሩ፣ ውሃ እንዳይቀዱ፣ ወንፊት እንዳይዋሱ …” የሚል እርጉም ፖለቲካ አይሰሙም። ኢትዮጵያዊያን አንዱ ሲያለቅስ አብሮ ደረት መምታትና ማንባት ባህላችን ነው። በርካታ የማህበራዊ ልምዶቻችን አብሮነትን የሚያጎላና እዚያ ላይ የተቸከለ ነው። ድሆች ነን። ግን ልክስክስ ህዝብ አይደለንም። እንደየ እምነታችን የፈጣሪ ፍርሃቻ አለን።

እጅግ ጥቂት አብሮነታችንን፣ አንድነታችንን፣ ሩህሩህነት የተላበሰውን ባህላችንን፣ ተካፍሎ የመመገብ ልምዳችንን፣ የመዋዋስና የመረዳዳት ወጋችንን እንደ ተምች ሊያመነዥጉ የተነሱ ሌት ተቀን ሊያከስሙን ይዳክራሉ። ይዘምራሉ። በፈጠራና በመላምት መርዛቸውን ይረጫሉ። ያለ መታከት ጥላቻን ያራባሉ። በክፋት አነሳስተው፣ በክፋት አጋድለው፣ አስከሬን እየተቀባበሉ ይሸቅጣሉ። አስከሬን እይራቡ ሌላው እንዲጋደል ይቀሰቅሳሉ። እነዚህ ዓይነቶቹ ጉዶች ይህን እያደረጉ በሚያገኙት ሃብት በውጭ አገር ቤት ገዝተው፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪ እየቀያየሩ፣ ልጆቻቸውን እያንቀባረሩ፣ ልጅ የሌላቸውም እንዳሻቸው እየተዳሩ ይኖራሉ። ምስኪኑ እነሱ በሚመኙት ፍጥነትና መጠን ባይሆንም ይረግፋል። ለዚህም ነው ዛሬ የሞት አዋጅና የአስከሬን ሻሞ ይቁም የምንለው።

በግርድፉ ሃሳቡን ለመነሻነት አነሳነው እንጂ ዋናው አሳቡ በትግራይ ክልል ተጀምሮ እየሰፋ ስለመጣው ጦርነት ለማንሳት ነው። ላለፉት ዘጠኝ ወራት ትግራይ ውስጥ ጦርነት ቢኖርም መላው አገሪቱ መታመም የጀመረችው ከለውጡ በፊት ነው። ትህነግ ወደ ትግራይ ካፈገፈገ በሁዋላ ምን ሆኖና ምን ነክቶት ያንን ሁሉ ጦር እንዳደራጀ፣ ምንስ ፈልጎ “የፌደራል ሃይሎች” ብሎ ማደራጀት እንደመረጠ በየ አቅጣጫው ከነሱም፣ እነሱ ከመለመሏቸውና ” አላማረንም” ብለው ከወጡ ሰምተናል። ባጭሩ ዳግም መንግስት የመሆን ዕቅድ ነበር።

ሃያ ሁለት ዓመታት የትግራይን ህዝብ፣ የኢትዮጵያን ድንበርና ሉዓላዊነት ሲጥ6እብቅ በነበረው መከላከያ ሰራዊት ላይ ” መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል” ተብሎ በሰበር ዜና እነ ሴኮ እንደነገሩን ከዛን ዕለት ጀምሮ በገሃድ ትግራይ ጦርነት ውስጥ ነች። እዚህ ላይ የጦርነቱን ፍትሃዊነትና አግባብ መዘርዘሩን ለአንባቢ በመተው ቀውሱ ላይ ማተኮር እንወዳለን።

ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ በትግራይ የረሃብ ወሬ ተነስቷል። የመሰረተ ልማት ውድመት ተሰምቷል። የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ማንም ያድረገው ማን አሳዛኝ የጦርነት ውጤት ምስሎች ወጥተዋል። ከሁሉም በላይ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል። አዛወንቶች፣ ሴቶችና ሕጻናት የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። ማንም ይወቀስ ማንም ይህ ክስረት እየባሰና እየጨመረ ነው።

መከላከያ “ትግራይን” ለቆ ከወጣ በሁዋላ፣ በትግራይ ማህጸን ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ ቡድን የለየ ጥቃት፣ እንዲሁም የኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚደርሰው የበቀል እርምጃ በዝግ በር የሚፈጸም ቢሆንም ነገሩ ሊደበቅ ከሚችለው በላይ ሆኗል።

ትህነግ ወደ መቀለ ከገባ በሁዋላ በዳግም ዘመቻ ተተምዶ በአፋርና በሱዳን ኮሪዶር ፍለጋ ጦርነት መግጠሙን እንደቀጠለ በይፋ አስታውቋል። አንዳንድ ከተሞችንም እንደያዘ እየገለጸ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህጻናት ብረት ተሸክመው ሲዋጉ፣ አንዳንዶቹ ተገድለው፣ ሌሎች ተያዘው፣ የተቀሩትም በጀብድ መልክ ፎቶ ተነስተው እየታዩ ነው።

ለማየት የሚቀፍና ልቡናን የሚፈታተን የህጻናት አስከሬን በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ እያየን ነው። ይህ አካሄድ ሊያስደነግጥ ሲገባ የጨቅላ ልጆች ምስል እያዘዋወሩ ግድያን ‘ሻሞ” የሚሉ እያየን ነው። ይህ አስደንጋጭ፣ አሳፋሪ፣ አሳዛኝ፣ እንዲሁም ቀና ልቡና ያላቸውን የሚያደማ ተግባር ሊቆም ይገባል የሚል ድምጽ ማሰማት ወደናል።

አስከሬን በመቀባበል “ሰበር ዜና” ማወጀ የሞራል መሰበርን እንጂ ሌላ የሚያሳየው ነገር የለም። አስከሬን እየተቀባበሉ አንዱን ተወዳሽ፣ ሌላውን ተነቃፊ ማድረግ የልብ መደንደን ውጤት ነው። አስከሬን እየደረደሩ “አሳየው” እያሉ መዝፈን የአስተሳሰብ መንጠፍን አመላካች ነው። በጥቅሉ ይህን ትውልድ፣ አገርና ሃብቷን ሊበላ ከየ አቅጣጫው ቆስቋሽ የበዛበት ጦርነት እንዲቆም ከትግሉ ጎን ለጎን መፍትሄ አፈላላጊዎች ሊተጉ ይገባል።

ደጅ ላይ እንደተጠራቀመ ጥራጊ ቆሻሻ የሚመሰሉ ከሃጂዎችና የነተበ ስብዕና ያላቸው ” ሰልቫጅ ” ፖለቲከኞች ሳይሆኑ በአገር ውስጥ ያሉና ሕዝብ የሚያከብራቸው ወገኖች ሁሉንም ወገን በአሸናፊነት ሊያስማማ የሚችል አሳብ በማርቀቅ ወደ አደባባይ ልትወጡ ይገባል። የእናንተ ዝምታ ግልቦችና ቀድመው የተተፉ ተላላኪዎች ራሳቸውን አማራጭ አድርገው፣ ሸምጋይ መስለው፣ እንዲነቃነቁ እድል ሰጥቷልና ዝምታችሁን ስበሩ።

ከሁሉም በላይ የሚወራውንና የሚደገሰውን ወደ ጎን በማለት አብሮ እየኖረ ያለው ምርጥ ሕዝብ በርጋታ የሚሆነውን በማስተዋል አስቀድሞ ሲያደርግ እንደነበረው አሁንም ያድርግ። ዛሬ ላይ መንግስትን ከመደገፍ ሌላ አማራጭ የለምና ሰላም እንዲሰፍን በመትጋት አብሮነትን መጠበቅ ከምንም በላይ ግድ ነው።

የትግራይ ተውላጆች ተሰባስባችሁ አማራጭ ሊሆን ይችላል የምትሉትን ሃሳብ አቅርቡና ከመስለ ወንድሞቻቸሁ ጋር ባህር ማዶ በወኪል ሳይሆን አገር ቤት በግንባር ስራ ጀምሩ። የትግራይ ህዝብ ቅድሚያ ሰላም የሚያገኝበት መንገድ ጥረጉ። የትግራይ ህዝብና አጎራባቾቹን ወደማያስፈልግ ግጭት እያመራ ያለውን አካሄድ መርመሩ። የድንበር ግጭት የነበረባቸውንና ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩ አካባቢዎችን አስመልክቶ ከሰላም በሁዋላ መፍትሄ የሚበጅበታን ፖለቲካን ሳይሆን ሕዝብንና የሕዝብን ፍላጎት በሚያስተናግድ መልኩ እልባት የሚየጋኝበትን አማራጭ በመፈለግ በገሃድ ውይይት ጀምሩ። መንግስትም ሆነ ዓማራ ክልል ይህን አበረታቱ። አለያ አሁን ባለው አያያዝ ኪሳራው እየበዛ መሄዱ አይቀረም። አሸናፊም አይኖርም!! እንደውም የከፋው ሊመጣ ይችላል። የሞት አዋጅ፣ የአስከሬን ሻሞ ይቁም!! ይቁም!!

ኢትዮጵያን የመስለቀጡ ሩጫ ከተሳካ ኦሮሚያ የለችም። አትኖርም። አፋር የለም። አይኖርም። አማራ ክልል የለም አይኖርም። አዲስ አበባን … አንዳንዴም ኢትዮጵያን የመብላቱ ዘመቻ መንፈሳዊም ይመስላል። አባቶቻችንና እናቶቻችን በየዕምነታቸው የሚያደርጉት ጸሎት እያመከነው እንጂ ከዚህም በላይ በሆነ ነበር።

በመጨረሻም በማታውቁት ጉዳይ ገብታችሁ ኢትዮጵያን እያፈረሰ ያለ ሚዲያ የምተደግፉ ወደ ላባችሁ ተመለሱ። እስከዛሬ በደረሰው ጥፋት እጅቻሁ አለበት። ከዚህ የጥፋት ሪኮርዳችሁ አታመልጡም። በጊዜው ሁሉም ይፋ ይሆናል። ግን አስከሬን ሻሞ እያሉ አገር ከሚያፈርሱት ጋር ተዳምራችሁ የታሪክ ተወቃሽ፣ በመጪው ትውልድ የምትረገሙ አትሁኑ። ከሁሉም በላይ እያለቁ ያሉ ዜጎች ደም እናነትም ቤት፣ በምድርና በፎቃቸሁ ላይ ይጮሃል!! ወደ መልካምነታችሁ ተመለሱ። የማትወጡት ጸጸት ውስጥ ሳትቀረቀሩ ዳኑ!!

Donate Button with Credit Cards

Leave a Reply