“ወለጋ የአማራ ነው! አማራ መሬቶቹና ርስቶቹን ያስመልሳል!” በማለት ግራ በሚያጋባና በሚታወቁ ባለሃብቶች በሚታገዘው መረጃ ቲቪ የእርስ በእርስ ዕልቂት እንዲከናወን ቅስቀሳ ሲያደርግ ከነበረው ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ጋር አቶ ለማ ለጊዜው ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የቅርብ ወዳጃቸው ለጎልጉል አስታውቋል። በቅርቡም ወደ ጣሊያን አምርተው ሥራ እንደሚጀምሩ አመልክቷል።

” ከሃጂው” ዳዊት ወልደጊዮርጊስ እሱን የመሰሉትን ከየዓይነቱ ሰብስቦ በጀመረው ዘመቻ የሽግግር መንግሥት ሰነድ ነድፎ የሞተውን ትህነግን አዝሎ እየሮጠ ይገኛል። ዳዊት ኮልኩሎ ካሰለፋቸው መካከል ራሱን በሚከረፉ ቃላት አደባባይ መላው ኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ካዋረደው ታምራት ላይኔ ይገኝበታል። ዳዊትና እሱ የሚደግፏቸው ሚዲያዎች አማካይነት ይህንኑ የሽግግር መንግሥት አዋጅ ልክ ነገ እንደሚተገበር አድርጎ እያሳወጃቸው ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ተሞክረው ከከሸፉ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ጀርባ ስሙ የሚነሳው ሰላዩ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ደጋፊ ለማሰባሰብ ሲል እሱና ታምራት ላይኔ፣ እንዲሁም በመረጃ ቲቪ ባለቤቶች ስፖንሰር አድራጊነት የአሜሪካ መንግሥት ዕውቅና እንዳለው አድርጎ የሚዲያ ማስታወቂያ ያሰራበት ዕቅድ ሰነድ ለአሜሪካ መንግሥት ከመድረሱ በፊት ሙሉ ዶሴው መንግሥት እጅ መግባቱን የጎልጉል ተባባሪ ዘጋቢ ከዲሲ አረጋግጧል።   

“ከሃጂና አስገዳይ” የሚል ስም የተሰጠው ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ተዋናይ የሆነበት የመፈንቅለ መንግሥት ንድፈ ሃሳብ “ልዩነት ቢኖርም አገር ቢቀደም ይሻላል” በሚሉ የራሱ ምልምሎች ዕርቃኑን ከወጣ በኋላ አሜሪካ ተለዋጭ ዕቅዷ አልታወቀም። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በዚህ ከሃዲ ዕቅድ ውስጥ ስማቸው የተነሳ ሰዎች ሚዲያው ባልተሰጣቸውና ባላገኙት “ክብር” ዜናውን ቢያሯሩጠውም እውነታው ሌላ እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ ለጎልጉል ደርሷል። 

በአብዛኛው አሁን ተዘጋጀ በሚባለው የከሸፈው የ”ተተኪ መንግሥት” ውስጥ ባብዛኛው ስማቸው የተካተተው እንደ ቤት ጥራጊ ቆሻሻ አገርና ህዝብ “እንትፍ” ብሎ የጣላቸው መሆናቸው በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚል ጥያቄ አስነስቶ ከርሟል።

ለግንዛቤ

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ በደርግ በተወገደ ጊዜ በትምህርት ውጭ አገር የነበረው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በራሱ አንደበት ሲናገር እንደተሰማው (የፒኤችዲ) ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አገር ቤት መጣ። እርሱ እንደሚለው ትግሉን ለመቀላቀል ቢሆንም ዋናው ዓላማ ግን በደርግ ውስጥ በመግባት ለምዕራባዊ ኃይሎች ለመሰለል እንደሆነ የበኋላ ሥራው ይናገራል። እርሱ እራሱም ቢሆን ይህንን የሁለት ቢላዋ ጨዋታ ሊያስተባብል አይችልም። እንዲያውም በአንዳንድ ቃለመጠይቆች ሞቅ ሲለው እየዘላበደ እምነቱን ሰጥቷል።

ደርግ ውስጥ በመግባት የስለላ ተግባሩን የቀጠለው ዳዊት፤ በወቅቱ ደርግን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩና ወቅቱ የጎላ አገር ወዳድነት የሚንጸባረቅበት፣ እንደ ዛሬ የጎጥ አስተሳሰብ የነገሰበት ባለመሆኑ ደርግን የተቀላቀለበትን ዋና የማፍረስ ተግባሩን አዘገየው። በቀጣይም ወታደርነቱን ሳይገፋበት የኤርትራ አስተዳዳሪ፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ወዘተ የተለያዩ ሥልጣን ላይ ከቆየ በኋላ ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን በሯን ወለል አድርጋ እንድትከፍት የሚያደርጋት ሤራ ዋና ጠንሳሽ ሆነ። ይህንኑ እንዲያመቻች “ወታደሩ” ዳዊት የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ዋና ኮሚሽነር ተደረገ።

ይህም በሰው ሰራሽ ምክንያት የደረሰብን ችጋር አጉልቶ በዓለምአቀፍ መድረክ እንዲሰማ በማስደረግ በዕርዳታ ሰበብ ለምዕራቡ ዓለም በሯን ጥርቅም አድርጋ የዘጋችው ኢትዮጵያ በግድ እንድትከፍት ጫና ተደረገባት። “እምቢ” ብትል በዓለም ዓቀፉ መድረክ ክስ እንዲቀርብባት የሚያስደርግ እንደሚሆን በተሠራው ሥራ ውስጥ የዳዊት ሚና የጎላ ነበር። ከውጭ የሚመጡትን “የዕርዳታ ሰዎች” የሚያነጋግር ወደ ውጭ አገራት በመሄድ የሚወያይ፣ የሚዋዋል … ተደርጎ የተሾመው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ሆነ። ራሱ በተለያዩ መድረኮች እንደተናገረው አየርላንዳዊውን ቦልጊዶፍን እና “We are the World” የዘፋኞች ቡድን እንዲመጣ በማስደረግ ትልቅ ድርሻ አለው።

በዳዊት ወልደጊዮርጊስ አጼ ዮሃንሳዊ ምሪት ምዕራባውያን ሰተት ብለው አዲስ አበባ ገቡ። ኢትዮጵያ ተበረበረች፤ ትህነግ እስካፍንጫው ታጠቀ፤ የዕርዳታ እህል እየሸጠ ጦር መሣሪያ እንዲገዛ ዕድሉ ተከፈተለት፤ እነ ቦብ ጊልዶፍ “አናውቅም” ቢሉም በድራማው ዋና ተዋናይ ሆኑ፤ የድራማው ዳይሬክተር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ነበር። ሁሉም ሲጠናቀቅ ዳዊት ከችጋር ሰላባዎች ጉሮሮ 300ሺ የአሜሪካ ዶላር ዘርፎ ወደ “እናት አገሩ” አሜሪካ ኮበለለ። እዚያም ሆኖ የኮ/ሎ መንግሥቱን ስም በሚያጠለሽ መልኩ እርሱ የሌለበት ይመስል “የደም ዕንባ” የሚል መጽሃፍ አሳተመ፤ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ለምዕራባውያን የፖሮፓጋንዳ ፍጆታ እንዲውል ተደረገ። ዳዊት በዓላማና በትዕዛዝ ሁሉንም ይፈጽም ስለነበር ልክ እንደ ዛሬው ያኔም የትህነግ ህጻናትን በጦርነት የመማገድ ወንጀል ዝም ተባለ።

ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ሳንቲም ሳያጎድሉ፤ የውሎ አበላቸውንና የመመለሻ ቲኬታቸውን ወደ አገርቤት በመመለስ አሜሪካ በስደት ለመኖር ሲወስኑ (በወቅቱ ቪኦኤ ላይ ቀርበው ተናግረዋል) ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ግን 300ሺህ ዶላሩን ከረሃብተኛ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ ዘርፎ የተንደላቀቀ ኑሮውን በአሜሪካ ጀመረ። ለቀጣይ የሤራ ፖለቲካም ራሱን አዘጋጀ። 

በግንቦት ወር 1980ዓም ወታደራዊ መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ሲያቅዱ የውጭውን ሤራ ሲመራ የነበረው ዳዊት ራሱ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲናገር የነበረው ሃቅ ነው። እስከ ሱዳን ድረስ በመምጣት ከሻዕቢያ፣ ከትህነግና ከኦነግ መሰል ድርጅቶች ጋር ተደራድሮ፣ ሰነዶችን ፈርሞ የሄደው ራሱ እንደሆነ በአንደበቱ መስክሯል። ይህ መፈንቅለ መንግሥት እንዲከሽፍ ካስደረጉትና ኮ/ሎ መንግሥቱ በዕልህ ተነሳስተው ጄኔራሎቹን ገድለው የጦሩ ሞራል እንዲላሽቅ፤ በቀጣይም ትህነግ (ወያኔ) ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገው ጉዞ የጽጌረዳ ምንጣፍ የተነጠፈበት እንዲሆን በማስደረግ የዳዊት የውጪ ሚና እጅግ የጎላ ነው። መፈንቅለ መንግሥቱም ከሽፎ የቀረው ዓላማው መንግሥቱን ፈንቅሎ ነጻነት ለሕዝብ ለማምጣት ሳይሆን ኤርትራን ለማስገንጠልና ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን አሻንጉሊትና ተላላኪ ለሆነው ትህነግ አሳልፎ ለመስጠት ነበር።

ትህነግ ከተወገደ በኋላ ከማንኛውም ፖለቲከኛ በመቅደም አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት የሽግግር መንግሥት ምሥረታን ሃሳብ በይፋ ያቀረበው ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ነበር። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻግራችኋለሁ ብለዋል፤ መልካም ነው ያሻግሩን፤ ግን እንዴት እንደምንሻገር ሮድማፕ ያስፈልገናል” በማለት እኔ ላሻግራችሁ ብሎ ለምዕራባውያን ሊሸጠን ሲያስማማን የነበረው ዳዊት ነበር። ዕቅዱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ አዲስ አበባ ለአንድ ወር ደጅ ሲጠና በስውር አጀንዳው መነሻነት “ወግድ” ተባለ። ትንሽ ቆይቶ አምርሮ የሚጠላቸው አቶ ካሣ ከበደ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አገር ቤት ገብተው በቀጣይ መደረግ የሚገባውን ከልምዳቸው አካፍለው በክብር መሸኘታቸው አንጨረጭሮት አሜሪካ እንደገባ በገሃድ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻውን አወጀ።

ትህነግ በኢትዮጵያ በየቦታው የቀበረውን ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ የብሔር (የዘውግ) ቦምብ ምን እንደሆነ እያወቀ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የመሸጋገሪያ ዕቅድ ብሎ ያቀረበው አንዱ ሃሳብ “በብሔር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶችን በሙሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዋጅ ማገድ አለባቸው” የሚል ነበር። ይህንን ረቂቅ በየዋህነት የተቀበሉ የዛሬ ሦስት ዓመት ጀምረው “የሽግግር ሮድማፕ (ፎኖተካርታ)” እያሉ ዳዊታዊ ዝማሬ ሲያሰሙ ሰኔ 15 ቀን በተደረገው ምርጫ የሕዝቡን ምላሽ አግኝተዋል።

በሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መስከረም ላይ ከመመሥረቱ በፊት ዳዊት የመጨረሻ የምትመስለውን ካርድ በመምዘዝ ዘመቻውን እያጡዋጧፈ ነው። እንደ ቤት ጥራጊ ተሰብስበው አንድ ቦታ ላይ የተከማቹትን እነ ታምራትን በአንድ በኩል በመሰብሰብ በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም በዕርዳታ ስም ምዕራባውያን ሰላዮች ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ለማድረግ እያሤረ ይገኛል። ዳሩ ግን ዳዊት ለዚህ ዘመቻው ካሰባቸው መካከል “ዛሬ ላይ ቅድሚያ አገሬ” ያሉ አንድ አገር ወዳድ ሰነዱን ለመንግሥት አቅርበዋል። አስቀድሞ መረጃ የነበረው መንግሥት ይህ ሰነድ የተበላበት መሆኑንን ይፋ አድርጎ ሌላ ሙከራ እንዲሞክሩ ጋብዟቸዋል። 

መረጃውን ያካፈሉን እንዳሉት ይህ ዳዊት ያዘጋጀውና አሜሪካ “እንቅልፍና ሰላም አጥታ ልትተገብረው ነው” የሚባለው ሰነድ ልክ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ማመልከቻቸውን እንደሚያቀርቡ ዜጎች የቀረበ ሰነድ ነው። የቀረበውም ትህነግ በቀጠራቸው የወስዋሽ ድርጅቶችና በውጭ ጉዳይ መ/ቤቱ (ስቴት ዲፓርትመንት) የትህነግ ውክልና ባላቸው የህዝብ ግንኙነት ኤጀንቶች አማካይነት ነው።

ይህ አሜሪካ እንደ መንግሥት አንዳችም ዓይነት ምላሽ ያልሰጠችበት ሰነድ ውስጥ ስማቸው የተካተተው አቶ ለማ መገርሳ የዜና ማሟሟቂያ እንደተደረጉ የዲሲ ተባባሪያችን አረጋግጧል። አቶ ለማ አሜሪካ ቢሆኑም አንድም ጊዜ ስዬ አብርሃንም ሆነ ዳዊት የሚባለውን ኢትዮጵያ ላይ የተጣበቀ ኩርንችት አግኝተው አናግረው አያውቁም።

በእርግጥ ሰነዱ እንደተላከላቸው መሸሸግ እንደማይቻል ያስታወቀው የመረጃ ምንጭ ከዚያ ባለፈ ግን የሳቸው ተሳትፎ ምንም ነው። አሁን አሜሪካ ሆነው ሰርግ፣ ቤተክርስቲያንና ማህበራዊ ግንኙነት ላይ አተኩረው ያሉትና ብዙ ጊዜያቸውን ከትዳር ጓዳቸው ጋር የሚያሳልፉት አቶ ለማ ስማቸው ከዚህ ያለቅጥ ከተወራለት ንቅናቄ ጋር የተነሳው “የኦሮሞ ውክልና አለን” ለማስባልና በዚሁ ሰበብ ከትህነግ ጋር መቀሌ ድረስ በመሄድ አብረው ለመሥራት ደጅ ሲጠኑ የነበሩ ጽንፈኛ ኦሮሞዎችን ለማስገባት ታስቦ እንደሆነ ዘግቧል።

“ወለጋ የአማራ ነው! አማራ መሬቶቹና ርስቶቹን ያስመልሳል!” በማለት ግራ በሚያጋባና በሚታወቁ ባለሃብቶች በሚታገዘው መረጃ ቲቪ የእርስ በእርስ ዕልቂት እንዲከናወን ቅስቀሳ ሲያደርግ ከነበረው ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ጋር አቶ ለማ ለጊዜው ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የቅርብ ወዳጃቸው ለጎልጉል አስታውቋል። በቅርቡም ወደ ጣሊያን አምርተው ሥራ እንደሚጀምሩ አመልክቷል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


Donate Button with Credit Cards

Leave a Reply