የኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አድናቂ ነበርኩ። አሁን ድረስ የአገሬ ጀግና ናት። ትንፋሿን ውጣ በባርሴሎና ስትሰግር የፈጠረችብኝ ስሜት ዛሬም ድረስ አለ። ገዛኽኝ አበራ ማራቶንን አንቀህ ወደ አገሩ የመልስክ ውድ ሰው ነህ። አጨራረስ ላይ ያለው ብቃትህና ” ኮቴ ሙዚቃዬ ነው” ብለህ እንዴት የደከመና ብርቱ ተፎካካሪ እንደምትለይ ያጫወትከኝ የብልጠትህ ልክ አይረሳኝም።

ያ – ደራርቱ (አበባችን) ልክ እንደ አንቺ ሁሉ በሄደበት እንደ አቡሸማኔ የሚተኮስ፣ እንደ ዋላ የሚቀዝፈው ቀነኒሳም ጀግናዬ ነው። አንበሳው ተፎካካሪዎቹን እየደረመሰ ያስፈነደቀን የዓለም ጀግና አለን። ስለ ሃይሌ ገብረ ስላሴ ምንም አልልም። እዚህ ጋር ክብር ልሰጠው ብነሳ ቦታ አይበቃኝምና ለብቻው ” ለምን ከአትሌቲክስ ፌዴሪሽን ኮበለለ?” በሚለው ጉዳይ እመለስበታለሁና። በነገራችን ላይ ሆላንድ ነኽሜ ከተማ በሚገኘው በግሎባል ስፖርት ኮሙኒኬሽን መንደር ጉብኝቴ ያይሁት ክብርና ሞገስ፣ ሃይሌን “አንተ” ስል መጥራቴና በአንድ እጄ መጨበጤ እንዳሳፈረኝ መናገር እወዳለሁ። እዛ ሰፈር ንጉስ ነው። በስሙ እኔም ከብሬያለሁ። አምሰግናለሁ።

አፓ ሆቴል

እንደ ዋላ የምትንሳፈፍፈው “ትንሿ ልጅ” ጥሩዬ፣ ደረቷን ግልብጣ የምትምዘገዘገው መሰረት ደፋር፣ በረጅም ቅልጥሟ የምትወረወረው ብርሃኔ አደሬ፣ እንደ ኮረንቲ ዙር እያከረረች የምትበረው ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ስለሺ፣ አሰፋ፣ ፊጣ፣ ዝምተኛዋ መስለች መልካሙ፣ አድብታ ተወዳዳሪዎቿን የምታነደው ጌጤ ዋሚ፣ ገለቴ፣ እልፍነሽ አለሙ … እነ ሚሊዮን፣ የጅፋር ልጆች፣ … ስፍር ቁጥር የሌላቸው የኢትዮጵያ ጅግኖች ከሩጫው ጀርባ ይነሳሉ። ታሪካቸውም እንደ ተሳትፏቸው ይወሳል። የእድል ጉዳይ ሆኖ አንዳንዶቹ ይበልጥ ይገናሉ። መንግስትም ይሆናሉ። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አሁን እየሆነ ያለው ይህ ነው። ” ምን መንግስት አለና” እየተባለ ድል ከሚጠበቅበት ሜዳ ለቅሶ ማስተላለፍ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ” ስምና ዝናን ለአጉል ጉዳይ መጠቀም” የሚል ስም የሚያሰጥ ነው። ወራጅ አለ!!

ዛሬ ይህን ከላይ እንደመነሻ ያነሳሁት ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በፊትና አሁን በዛው በፍልሚያው መንደር ሆና ደራርቱ የምትሰጣቸውን አስተያየቶች አስመልክቶ የራሴን ማጣሪያ ካደረኩ በሁዋላ እንደሆነ አንባቢያን እወቁልኝ። በሌላ በኩል ” ሰማይ አይታረስ፣ ንጉስ አይከሰስ” የሚለውን ተረት ወደጎን በማድረግ በሚዛን ሃሳቤን ሰፍራችሁ ትመዝኑት ዘንዳ አሳስባለሁ።

አፓ – አና

Ana hotel

አፓና አና የጃፓን አትሌቶች አይደሉም። የሆቴል ስሞች ናቸው። አና ሆቴል የዓለም ዓቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንግዶቹን ማለትም የየአገራቱን ፕሪዚዳንቶችና ዋና ጸሃፊዎች ያሳረፈበት ሆቴል ነው። በዚህ ሆቴል የኦሊምፒክ ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሃፊ እንጂ ማንም አያርፍም። ስለዚህ ይህን ሆቴል ” እነ እገሌ ለራሳቸው ያዙ፤ እኛን አራቁን ” የሚለው ክስ አይሰራም። ከሆቴሉ ወደ ኦሊምፒክ መንደር ወይም አትሌቶች ሰፈር ለመሄድ እስከ 50 ደቂቃ ይነዳል። አፓ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሯጭ ላልሆኑ የልዑካን ቡድን አባላት የተያዘ ሆቴል ነው። እዛ ሚኒስትሮቹን ጨምሮ ኮማንደር ደራርቱ ወዳጄ ዶክተር በዛብህና ሌሎች አብረው የተጓዙ አርፈዋል። ወደ ኦሊምፒክ መንደሩ ለመጓዝ እስከ 35 ደቂቃ ይነዳል።

አንባቢዎቼ ጃፓን በኮሮና ምክንያት እንቅስቃሴ ገድባና እያንዳንዱ የገባበትን እየተከታተለች ማስጠንቀቂያ በመስጠት የምታደርገው ክትትል ትልቅ ነው። አልሰማ ያሉ ሰዎቻችን ነገሩ እንደ አገር ቤት መስሏቸው ተግስጸዋል። ስም መጥራት አልፈልግም እንጂ መዘዋወሪያ ፈቃድ ተነጠቀው የተመለሳላቸውም አይጠፉም።ጃፓን መረጃ በመስጠትና ሁሉም አገልግሎት ያለ አንዳች መደናቆር ለማግኘት ሲሰተም ዘርግታለች። ኦሊምፒክ ኮሚቴም በዚሁ ሲሰተም መርሃ ግብሩን እየሰነደ ያስቀምታል። ያከናውናል። ከዚህ ሲሰተምና ህግ ጋር እራስን አላምዶ መንቀሳቀስ ግድ ነው። ስለዚህ ሲስተሙንና ህጉን ከመላመድና ካለማክበር በሚመነጭ ስህተት ሲፈጸም ጣት መጠቋቆም አላዋቂነት ካልሆነ ሌላ ምንም ትርጉም አያሰጠውም። አንዱ ሌላውን ሲኮንን ቅድሚያ ” ነገሩ ግብቶት ወይም ግብቷት ነው? ወይስ “ዝም ብለው በአናሎግ እውቀት እያቦኩት ነው” ብሎ መጠየቀ ግድ ነው።

የመክፈቻው ቀን “አካፑልኮ”

የመክፈቻው ዕለት ኢትዮጵያ ባንዲራዋን የያዘ አንድ ሰው መታየቱ፣ አስደንጋጭ፣ አሳፋሪ ሆኖ ቀርቧል። በግል እኔም ያ ስሜት ተሰምቶኛል። ከዛ “ለምን” ብዬ ጠየኩ። የተወሰኑ እዛው ያሉ ሰዎችን አናገርኩ። አሰራሩን ለመመርመር ሞከርኩ። አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ” አንገት ያስደፋል” ሲል አንጀት በሚበላና አገር ወዳዶችን በሚያሳምም መልኩ የሰጠው መግለጫ ሲመረመር ግን ባዶ ነው። መግለጫው አሁን ልክ አሜሪካ ለስውር ፍላጎቷ ማሳኪያ ትህነግን እንደ በትር እንደምትጠቀምበት ዓይነት ነው የሆነብኝ። ፌዴሬሽኑ ጠረጴዛ ፊት የደረደራቸው ሰዎች እየተቀባበሉ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ለማሳጣት አጋጣሚው ” እልል በቅምጤ” ሆኖ እንደተሰማቸው ከንግግራቸው ለመረዳት አያዳግትም። እስኪ በምክንያት ላብራራ።

ወደ መክፈቻው ስታዲየም ለማምራት የመግቢያ ካርድ ወይም በኦንላይን እውቅና የሚሰጠው ካርድ አለ። ኢትዮጵያ ስድስት ካርድ ተሰጥቷታል። ወደ ስፍራው የሚኬደው በአውቶቡስና በቫውቸር ታክሲ ብቻ ነው። ሁሉም ሰው በዚህ መልኩ ነው የሚስተናገደው። የኦሊምፒክ ሜዳሊስትም ሆነ ዛፍ ቆራጭ ቶኪዮ ካለ ከዚህ ሲስተም ውጭ ሰዎች የሚፈይዱት ነገር የለም። ጨዋታው ከሲስተም ጋር ነው። ከተግባባን ነገሩ ሲስተሙን ማናገሩ ላይ እንጂ ሌላው ላይ ጣት መቀሰር አይነፋም!! ልክ የዓለም ሚዲያዎች ኢትዮጵያን አጋጣሚ አገኘን ብለው እንደ ባለሙያ ሳያመጣጥኑ እንደሚተኩሱት የተነገረው ሁሉ ያለ ገደብ ለህዝብ ስለሚለቀቅ ማሳጣት ቀላል ነው። እውነታው ግን ሌላ ነው።

እናም ስድስቱ የመግቢያ ቲኬት ኮማንደር ደራርቱ እጅ ነበር። ገና ከጅምሩ አክሪዲቴሽን ለመውሰድ ከልዑኩ ቺፍ ዲሚንሽን ጋር የተፈጠረ ” መሳቂያ ያደረግንን” ጉዳይም ፌዲሬሽኑ በመግለጫው ቢያካትተው ደግ ነበር። ብቻ ሁሉም ሆኖ በተባለው ሰዓት አስቀድሞ በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ ለገነት ደሬ ቫውቸሮቹን ይዛ በታክሲ ስትመጣ በካርዶቹ ላይ ባለው ኮድ ወይም ስልክ በመደወል አክቲቬት ማደረጉ ላይ ወገቤን አለችና ሲስተሙ “አላውቅሽም፣ አላስገባም” አለ። ታክሲው ማለፍ የሚችለው በቫውቸሩ ላይ ባለው ቁጥር ተደውሎ አክቲቬት ሲሆን ነበረና ታክሲው መግባት ተከልክሎ ተመልሶ ወጣ። ከላይ እንዳልኩት ጨዋታው ከሰው ጋር ሳይሆን ከሲሰተም ጋር ነውና ነገሩ በዚህ አበቃ!!

የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ አትሌቶች ያለ ካርድ መሰለፍ ቢችሉም ኢትዮያ አትሌቶቿ ለውድድሩ በተመረጠ የህክምና ጥበብ ምክንያት ሄሞግሎቢናቸው እንዳይወርድ አዲስ አበባ ልምምድ እየጨፈጨፉ ነው። የተቀሩት የዴሊጊሽን አባላት ሃበሻ ልብስ ለብሰው እንዳይሰለፉ ካርዱን የያዘችው ደራርቱ በሲስተሙ ተይዛለች። ምን ይሁን? ከረፈደ በሁዋላ ስለሆነው አይጠቅምምና ልተወው። እንግዲህ ይህን ጉድ አዝሎ ነው ” ለቅሶ ከቶኪዮ” የሚባል ዘፈን የሚዘፈነው። ” ልክ አሜሪካ እንዳሉት የሻለቃ ዳዊት ደቀመዝሙሮች ‘መንግስት የለም” በሚል መረጃ የሚላከው። ይህ አግባብ ሊተች፣ ሊቆምና በአደባባይ ሊወገዝ ይገባል። ደራርቱ ማንም ሁኚ ማን ከዚህ አግባብ አንጻር አጥፍተሻል። ፌዴሬሽንሽም በደቦ ዘፍኗል። መክፈቻው በዛ መልክ ኢትዮጵያ መወከሏ አሳዛኝ ቢሆንም ሙሉ ትዕይቱን ማቅረብ እንጂ እንደ ” አካፑልኮ” መዝናና ማየት ብዙ እርቀት አያስኬድም።

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ያላችሁን ልዩነት ህዝብ በማያውቀው እናንተ በምታውቁት የልዩነታችሁ ዋና ምክንያት ባሻችሁ አግባብ ጨርሱ። መስማማትም ካልቻላችሁ በህግ አግባብ ሂዱ። ካሽችሁም ጦርነት ክፈቱ። ግን ሕዝብ በማያውቀው የልዩነት ሰበብ አጋጣሚ ተመቸ ብላችሁ አትዥጎርጉሩት። ይህ በበርካታ አገራዊ ቀውስና ሰላም እጦት መከራውን እያየ ላለ ሕዝብ ከኦሊምፒክ ሜዳ በለቅሶ የፈጠራ ክስ ማዝነብ አዋቂ አያደረግም።

ደራርቱ ቀደም ሲል ጀምሮ መንግስት ጉያ ስር መለጠፍ ትወጂያለሽ። የአትሌቶች ተወካይ እንደዛ ፍትህ ሲዛባ በዝምታ ኖረሽ ( አተገብሽ ያለው ገዛሃኝ አበራ ምስክር ነው) ዛሬ እንደዚህ አይነት ጩኸት ማሰማትሽ ሲነቃ ” ሲያልቅ አያምር” እንዳይሆን እፈራለሁ። በርካታ ትልልቅ አትሌቶች እያጉተመተሙ ነው። ፌዴሬሽን አካባቢ ከሚያንዣብቡት ውጪ ሌሎች ቅር እየተሰኙብሽ ነው። የፌዴሬሽኑ ጸሃፊና በህግወጥ አሰራር የዳርት ፌዴሬሽን ፐሪዜዳንት የሆኑትና ከመንግስት የገንዘብ ክፍያ ስርዓት ውጪ በወጋገን ባንክ አካውንት ከፍተው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ሲያንቀስቀሱ የነበሩና የታገዱ ሰዎች መረብ ውስጥ ወደቀሽ ከሆነ ራስሽን መርመሪ።

ደግ፣ ሳቂታ፣ አልቃሻ፣ ለስላሳ ሰው እንደሆንሽ ይታወቃል። ይህንኑ መልካምነትሽን ይዘሽ ብትዘልቂ እጅግ ውብ የሚሆን ይመስለኛል። እዛ ፌዴሬሽን ውስጥ ከልጅ እስከ እውቀት ካብ ላይ ጸሃይ እንደሚሞቅ እባብ እየተገላበጡ፣ ጡረታ ሆነው እንኳን ማረፍ የማይፈልጉ፣ ለጥቅማቸው ሲሉ ነገር እየጎነጎኑ፣ የማይሞላው ከርሳቸው ስለጎደለ፣ አበል ስለቀረ … በአራት ዙሩ በወረፋ ሂዱ መባላቸውን እንደ ” አገር ክህደት” ቆጥረው ዘመቻ ለጀመሩ መተቀሚያ ከመሆን ተቆጠቢ። አንቺ ብታጠፊ የሚበላሽ ታላቅ ስምና ታሪክ ያለሽ እንቁ ነሽ። እነሱ ግን ምንም የሚጠፋ ስም የላቸውምና ራስሽን እንደ ንስር ክፍ አድርገሽ ተመልከቺ። አለያ ግን ከምን የተገኘህ “…. አብረህ ተወቀጥ” ሊሆን ይችላል።

ሚዲያዎች

ስለምን የአንድ ወገን ዘገባ ታስተናግዳላችሁ? ካልሆነስ በጥያቄ አፋጣችሁ እንዳትጠይቁ ምን ይክለክላችኋል? ስምና ዘና ከአገር ውጤትና ክብር በታች ናቸው። መልካም ገድል ሲፈጸም የሚሰጥ ክብር ላልተገባ ተግባር ሲውል ነቅሶ ማውጣት የጋዜጠኖች ስራ ነው። እንደ እኔ እነደ እኔ ኦሊምፒክና አትሌቲክስ ውዝግብ የገቡበት ጉዳይ አልቋል። ባለቀ ጉዳይ መናቆሩ ለምን አስፈለገ? የሚለው ሲተነተን “ስኳር ስኳር” የሚለውን ዘፈን የሚወዱ የሚፈትሩት የፖለቲካችን ዓይነት ሴራ ነውና አድምታችሁ ለምን አትሰሩትም። ለምን አትበረቃቅሱትም?

ገዛኸኝ አበራ

መግለጫ ሲሰጥ የፌዴሬሽን አመራር ሆነህ የመምህር አብራራውን ሚና ተክተህ አየውህ። የማውቅህ ገዛኸኝ አልመስል አልከኝ። እጅግ ብዙ ጉዳዮች እንደተጫወትን አሰብኩ። ባለቤትህን እልፍነሽ አለሙን ደራርቱ ቱሉና ዱቤ ጅሎ ባሉበት ፌዴሬሽን ከኦሊምፒክ ሲያስወጧት በመኖሪያ ቤትህ የሰጠኸውን መግለጫ በአይነ ህሊናዬ ቃኘሁት። ረዥም ዘመን ወደ ሁዋላ ሄጄ በመግለጫው ላይ የነበሩትን አትሌቶች ብዛትና ማንነት አስታወስኩ። እልፍነሽ እምባ እያነቃት የተናገችውን፣ እነሃይሌ ያስከተሉትን፣ እነጌጤ … ምን ልበልህ “የህግ ያለህ” ብለህ ስትሟገት እንዳልነበር ዛሬ በዚህ መልኩ ቢልልኝ የሚባል ሰውዬ ሲነዳህ ሳይ አዘንኩ። በሚቀጥለው ጽሁፌ እንገናኝ። የፍቅር ሃሳብ አካፍልሃለሁ።

ስለ ኦሊምፒክ

ስለ ኦሊምፒክ አሁናዊ ቁመና ብዙ መረጃ የለኝም። ችግር ካለበት ግን ችግሩ ላይ አተኩሮ አግባብ ነው በሚባል ደረጃ መተቸት፣ መረጃና ማስረጃ ላይ ተንተርሶ አከርካሬው እስኪዝል መሞገት አግባብ ነው። ካሁን በሁዋላ አተናዋለሁ። መረጃ አለን የምትሉ ላኩልኝ። ያለ አንዳች ማመንታት እስተናግዳለሁ። ስድብና ዘለፋ ብቻ ሲቀር!!


Donate Button with Credit Cards

Leave a Reply