አብነት “በእምነት ማጉደል” ተባረሩ፣ ቀጣይ ሕይወታቸው የችሎት ደጅ ይሆናል፤

እንዳሻቸው ሲንፈላሰሱበት ከነበረው የሸራተን ሆቴል ከተባረሩ በሁዋላ ሻንጣቸውን ሰብስበው ለመጨረሻ ጊዜ ሲሰናበቱ የሻይ ሂሳብ እንዲከፍሉ ቢል ቀርቦላቸው በክሬዲት ካርድ ሂሳብ ከፍለው የወጡት አቶ አብነት ገ/መስቀል ከሚድሮክ ተሰናበቱ። እሳቸው በፈቃዳቸው እንደለቀቁ አስታውቀዋል። ቀጣይ ህይወታቸውን በፍርድ ቤት እንደሚያሳልፉ ተሰምቷል።

ፎርቹን ተባረሩ ወይስ ለቀቁ ሲል ያስነበበው ዜና ምስል

የፎርቹን ጋዜጣን በመጥቀስ የተለያዩ መገናኛዎች እንዳሉት፣ አቶ አብነት ከሚድሮክ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተነስተዋል። የድርጅቱ ሊቀመንበርና ባለቤት ሼኽ ሙሃመድ አላሙዲን ለአቶ አብነት ሰጥተዋቸው የነበረውን ውክልና ሙሉ ለሙሉ አንስተዋል። ከስልጣን የተነሱት “እምነት በማጉደላቸው ” ነው ተብሏል። ስንብታቸው በእምነት አጉዳይነታቸው ሳቢያ መሆኑንን ያመለከቱት በእርሳቸው ፋንታ የተተኩት አቶ ጀማል አሕመድ ናቸው። አቶ ጀማል “እምነት ማጉደል” ያሉትን በይፋ አልዘረዘሩም።

አቶ አብነት “በራሴ ፈቃድ ለቅቄያለሁ” በማለት ለሰጡት አስተያየት፣ አቶ ጀማል ” ፍጹም ሃሰት” ሲሉ በዕምነት ማጉደል መባረራቸውን ለፎርቹን የገለጹት አቶ ጀማል፣ የአቶ አብነት ወዳጅ ነበሩ። የመርካቶ ነጋዴ የነበሩት አቶ ጀማል የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ፣ አመራርና የክቡር ትሪቡን ቋሚ እድምተኛ ናቸው።

አብነት ገብረመስቀል በከፍተኛ የሃብት ምዝበራ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ኢትዮ 12 ሰምታለች። የተለያዩ ምርመራዎች እየተካሄደባቸው እንደሆነም ታውቋል። ይፋ ባይነገርም ኦዲት ተጀምሯል።

አቶ አብነት በንበረት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ወንጀሎች ክስ እንደሚመሰረትባቸው ተሰምቷል። ቀደም ሲል ከመንግስት ከፍተኛ ሰዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመመካት በበርካታ ወንጀል መሳተፋቸውን የሚያውቁ የቆየውን ቂማቸውን ለመወጣት ” ጊዜው አሁን ነው” እያሉ እንደሆነ ታውቋል።

አብነት የባለሃብቱን ቅጥር ብቻቸውን ከልለው ለመያዝ በነደፉት ስልት በርካታ ጠላት ማፍራታቸው ይታወሳል። ሰፊ የሚባል ሃብትም በዘመዶቻቸውና በቅርብ ሰዎቻቸው በሽርክና ስም ይዘዋል። በቅርቡ የድንጋይ ከሰል ማስመጣት ስራ ለትልቁ ልጃቸው እንዲሰጥ ከጫፍ ካደረሱ በሁዋላ አቶ ጀማል ደርሰው እንዳሲያዙባቸው ሰምተናል። ለድርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚገባውን ከስል ልጃቸው እንዲረከበው ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ እንዳሉት አቶ አብነት ቀሪ ህይወታቸውን ምን አልባትም በችሎት ደጅ እንደሚያሳልፉ እየገለጹ ነው። አቶ አብነት ያልተዘጋና በባለስልጣኖች ውሳኔ የተዳፈነ የግድያ ወንጀል ክስ ከፍት መዘገብ እንዳለባቸው ይታወሳል።

ባለሰው ሳምንት አቶ አብነት ሽማግሌ ወደ ሳዑዲ መላካቸውን ገልጸን መዘገባችን ይታወሳል።


Leave a Reply

%d bloggers like this: