“ ኢትዮጵያ ትቀበራለች” የህወሀት ደጋፊዎች

“ራስ አሉላ አባነጋ ከዘላለማዊ እንቅልፋቸው ለአፍታ ቀና ብለው ይህን ጉድ ቢያዩ እንዴት ያዝኑ ይሆኑ?” በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን!

የብሔር ፌድራሊዝም መጨረሻ ምን እንደሚመስል ትግራይ ላይ በተፈጠረው ችግር በደንብ እንደ ኢትዮጵያዊ እያየን ነው!

“በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የህወሀት ደጋፊዎች እብደት በጊዜ ሉጋም ካልተበጀለት መሬት ላይ ላለው ምስኪን የትግራይ ወገናችን መዘዙ አደገኛ ነው። ህወሀት ከመቃብር እንዲወጣና ለሌላ ዙር እልቂት እንዲሰማራ የዲያስፖራ ተጋሩዎች ሚና የትየለሌ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ሰሞኑን ጌታቸው ረዳ በሰጠው ቃለመጠይቅም ይህንኑ በማረጋገጥ የሙገሳና የምስጋና መልዕክት አስተላልፎላቸዋል። ሲያዙ በመንደባለል፣ ሲለቀቁ በዳንኪራ የውጭ ሀገራትን አደባባዮች ሲያደነቁሩ የከረሙት የህወሀት ደጋፊዎች ባለፉት ቀናት ፌስቲቫል ብለው አሸሼ ገዳሜውን ሲያቀልጡት ታይተዋል። ከለንደን – ዴንቨር እስከ ካርቱም በዘለቀው የፌሽታ ትዕይንት “እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም፣ ኢትዮጵያ ትቀበራለች” የሚል መልዕክት በየአደራሹ ሲያስተጋቡ ተሰምተዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነት አንገታቸው መተማ ላይ የተቀላው አጼ ዮሀስን ይህን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? የጣሊያን ወራሪ በዶጋሊ አከርካሪውን ሰብረው ያደባዩት ራስ አሉላ ከዘላለማዊ እንቅልፋቸው ለአፍታ ቀና ብለው ይህን ጉድ ቢያዩ እንዴት ያዝኑ ይሆኑ? በየዘመናቱ፣ ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶቿና በውስጥ ባንዳዎቿ ጦርነት በተከፈተባት ጊዜ ሁሉ ከማንም ቀድመው፣ በዱር በገደሉ፣ በየጥሻውና ዋሻው ስለኢትዮጵያ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ሰጥተው ያለፉ የትግራይ ጀግኖች መስዋዕትነታቸው ተክዶ፣ የሞቱላት ሀገር እንድትፈረስ አዋጅ ሲለፈፍላት ቢሰሙ ምን ይሰማቸው ይሆን? ዛሬም ከዚህ እብደት ራሳቸውን ጠብቀው፣ የህወሀትን የጥፋት ጉዞ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እየታገሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ስሜታቸው ምንኛ ተጎድቶ ይሆን?

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የህወሀት ደጋፊዎች ቀዩን መስመር ከጣሱ ሰንብተዋል። ድልድዩን ከሰበሩ ቆይተዋል። አብዛኞቹ የህወሀት የዘረፋና የእንጋጠው ቡድን ማህበርተኛ ናቸው። በትምህርትና በስራ ከደሀው ጉሮሮ መንትፈው ባከማቹት ገንዘብ ሀብት አፍርተው፣ ውስኪ እየገለበጡ ሲምነሸነሹ የሚኖሩ ናቸው። ዶላር እየተዛቀ፣ ዩሮው እየተጠረዘ በየአካውንታቸው ሲጠራቀምላቸው የኖሩ፣ ይህ እንዳይቋረጥባቸው መሬት ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በህወህት አገዛዝ ቀንበር ውስጥ ሆኖ እንዲኖር የሚመኙ፣ የሚጸልዩ፣ የሚጎተጉቱና የምዕራብያውያንን ደጅ እየረገጡ የሚለምኑ ናቸው። ህወሀት የጀርባ አጥንቱ ተሰብሮ፣ ከመሪዎቹ አብዛኞቹ ወደመቃብርና እስር ቤት ሲሸኙ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደዋሻና ጢሻ ሲገቡ ወሽመጣቸው የተቆረጠው፣ ቅስማቸው የተሰበረው እነዚሁ በህዝብ ስቃይ አዱኛ ህይወታቸውን ሲቀጩ የነበሩት የህወሀት ዲያስፖራዎች ናቸው። የህወሀት ሞት የእነሱን የቅምጥል ህይወት እንደሚ ያስቀረው ጥርጥር የለውም። ህወሀት ከሌለ ውስኪ እየተራጩ፣ እየተምነሸነሹ፣ አሜሪካን ድሪም የሚባለውን አስደሳች የቅንጦት ኑሮን እየተንፈላሰሱ መኖር ሊቆም ነው።

ለእነዚህ የህወሀት ደጋፊዎች የትግራይ ገበሬ ከሴፍቲኔት ያልተላቀቀ ኑሮ የሚያሳስባቸው አይደለም። የኑሮ ሸክሙ አጉብጧት ወገቧን በመቀነት ሸብባ እያቃሰተች ለምትኖረው የትግራይ እናት የሚራራ አንጀት የላቸውም። በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ስራ ፍለጋ የባህር ሲሳይ፣ የህገወጥ አዘዋዋሪዎች መጫወቺያ ሆነው በረሃ ሲበላቸውና አንገታቸው በጨካኞች ሲታረድ እነዚህ የትግራይ ተወላጆች የጎደለባቸው ነገር አልነበረምና እጃቸው ከውስኪ ብርጭቆ ሳይላቀቅ፣ አይንና ጆሮአቸውን ደፍነው ቆይተዋል። ለእነሱ የትግራይ ህጻናት ስቃይ በሆሊውድ እንደተዘጋጀ ትራጄዲ ፊልም የሚኮሞኩሙት እንጂ ከዚያ ያለፈ ቦታ የለውም። ህወሀት ስትመታ እነሱ ማልቀስ የጀመሩበት ምክንያታቸው ወላጅ አልባ ሆነን እንቀራለን በሚል ስጋት መሆኑ እነሱም ሳያፍሩ ይናገሩታል፣ እኛም ጠንቅቀን እናውቃለን። የእንጀራ ገመዳቸው ሊበጠስ ነው። የዶላር ምንጩ ሊደርቅ ነው። የውስኪ ጠርሙስ አንገት ማነቁ ህልም ሊሆንባቸው ነው። ይህን ጊዜ ነው አደባባይ ወጥቶ መጮሁ፣ መንከባለሉ፣ መንደባለሉ የተጀመረው።

የህወሀት ዲይስፖራዎች ለከት ያጣ ብሄርተኝነት ከጥቅማቸው ጋር ተሳስሮ ፍጹም እብደት ውስጥ ከቶአቸዋል። የዘረኝነት ስካሩ ላይ የህልውና ጉዳይ ፈተና ሲታከልበት አይናቸውን ሸብበው፣ ጆሮአችውን ደፍነው የትግራይን ህዝብ ወደገደል ለመጨመር የጥፋት ክተት አውጀው ተነስተዋል። የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዘው ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚል፣ ሀገር ቤት ላለው የትግራይ ወገን ህዝብ አደገኛ የሆነ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ከእሳቱ በርቀት ሆነው መሬት ላይ ያለውን በስሙ የሚነግዱበትን ህዝብ እያፋጁት፣ እያስለበለቡት ይገኛሉ። በትግራይ ህጻናት ዕልቂት አንዲት መንደር ስትያዝ ከሶፋቸው ቁጭ ብለው የሳሎን ውሻቸውን እያሹ በቪዲዮ ይመለከቱና አደባባይ ወጥተው “ጀግና፣ አጆሃ” ዳንኪራውን ያቀልጡታል። ከሌላው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር በሰላም እንዳይኖር የተመረዘ አጀንዳ ይወረሩለታል፣ ገንዘብ ሰብስበው ጥይት መግዢያ ይልኩለታል፣ እሱ በእሳት ሲጠበስ፣ እንደ ቅጠል ሲረግፍ የአዞ እንባ እያነቡ ለሌላ ዙር እልቂት ያመቻቹታል።

ይህን ስካር ማን ያበርደው ይሆን? የእነዚህን የህወሀት ኦርፋኖች የእብደት ግስጋሴ ሉጋም የሚያበጅለት ቆራጥ የትግራይ ትውልድ ይመጣ ይሆን? አዝማሚያው አደገኛ ነው። ለትግራይ ህዝብ እዳ ሆነው ተጨማሪ ጉዳት ሳያስከትሉ በቃችሁ የሚላቸው የተጋሩ ሊቅ የት ነው ያለኸው?”

Leave a Reply