ሴትየዋ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በመርሃግብራቸው መሰረት ሰኞ ምሽት ተጠብቀው ነበር። ሱዳን ላይ ተጨማሪ ቀን ያስፈለጋቸው ምክንያት ግልጽ አይደለም። ለመገመት ያህል የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከወዲሁ እየገለጹ ያሉት አቋም የሴትዮዋን የአዲስ አበባ ቆይታ ምቾት የሚሰጣቸው አይደለም። ኢትዮጵያውያን በሴትዮዋ የማህበራዊ ገጻቸው ገብተው እግር በእግር እየተከታተሉ የሚልኩላቸው መልዕክቶች እንቅልፍ የሚነሳቸው እንደሚሆን ይታመናል። አዲስ አበባ ሳይደርሱ የኢትዮጵያን ህዝብ ስሜት ግለቱን የሚፋጅ ሆኖባቸዋል። ወደ አዲስ አበባ ይዘው የሚመጡት አጀንዳ በኢትዮጵያ አንገት ላይ ሊያርፍ የተዘጋጀ የሰላ ካራ መሆኑ የገባቸው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከወዲሁ ቆፍጠን ኮስተር ያለ አቋማቸውን በሚደርሳቸው መንገዱ ሁሉ እየሰደዱላቸው ነው።

ህወሓት የመጨረሻ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ውስጥ ገብቷል። ከየጦር ግንባሩ የሚመጡ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ከህጻናት እስከ አዛውንት አባትና እናቶች፣ ከመነኩሴ እስከ ሼህ በግዳጅ የተሰለፈው የህወሀት ሃይል ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት ደረጃ እየተቀጠቀጠ ነው። ዛሬ አፋር ግንባር ተገኝተው የውጊያውን ሂደት በቅርበት የተከታተሉት ጠ/ሚር አብይ አህመድ በመንግስት በኩል የህወሀትን ጸሀይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥለቅ ውሳኔ ላይ መደረሱን ሊነግሩን የፈለጉ ይመስላል። እሳቸው ባይናገሩትም ሁኔታዎች ያንን እንደሚያመላክቱ ይሰማኛል። በየግንባሩ የህወሀት ሀይል እየተወቃ ነው። በአጋጣሚ፣ የጥሞናውን ጊዜ እንደ መልካም እድል ተጠቅሞ ከያዛቸው አከባቢዎች እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈርጥጦ ለቋቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ አስክሬኖችን ጭኖ ለቀጣይ ድራማ ሊያዘጋጃቸው ወደ መቀሌ ወስዷቸዋል።

ፈረንጆቹ ህወሓት በወታደራዊ ድል የበላይነትን ይይዛል የሚለው ተስፋቸው መጨናገፉን ተረድተውታል። በስውር የሳተላይት መረጃ ከመስጠት አንቶ የተለያዩ ድጋፎችን ያደረጉለት የህወሀት ሃይል ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ ሆኖ መደምሰሱ አስቀያሚ መርዶ ሆኖባቸዋል። ያለአቅሙ፣ የአይጥን ያህል ቁመና ይዞ እንደዝሆን ከሚያጓራው የህወሀት ቡድን የሚጠብቁት ነገር ከእንግዲህ የሚኖር አይመስልም። በራሳቸው መንገድ፣ የለመዱትን ቲያትር ጽፈው፣ ሌሎች ሀገራትን ባፈረሱበት መንገድ የውሸት ታሪክ አዘጋጅተው በሌላ ዙር፣ በሌላ መንገድ ለማንበርከክ እየመከሩ ነው። ወደሱዳን የሚወስደው ኮሪደር ለህወህት እንዲከፈት ማድረግ አልያም የሚመጣውን ብርቱ ማዕቀብ መጣል ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረቡት ምርጫዎች ናቸው። ሴትየዋ ይህን ለኢትዮጵያ አንገት መቀንጠሺያ የተዘጋጀውን ካራ ይዘው ነው አዲስ አበባ የገቡት። ለዚህ ማዳመቂያ የጀኖሳይድ ድራማ በተከዜ ወንዝ ላይ አዘጋጅተዋል። ድራማውን የገጻቸው ፊት፣ የዜናቸው መግቢያ እንዲያደርጉት የቤት ስራ የተሰጣቸው ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ከወዲሁ ጩኸቱን እያቀለጡት ነው።

See also  ለሻምበል በላይነህ አዘንኩለት፤ በዘረኞች መዳፍ ...

እንግዲህ ይሄን ጊዜ ነው ወገብን ጠበቅ አድርጎ፣ አንጀትን አስሮ፣ ለማይቀረው ሀገርን የማዳን ታሪካዊ ተልዕኮን ለመወጣት ኢትዮጵያዊ ሁሉ መነቃነቅ ያለበት። ሴትየዋ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ካራ ይዘው እንደሚመጡ ቀድመውኑ አሳውቀዋል። በግልጽ እንደተናገሩትም ዓላማቸው የትኛውንም በር ማስከፈት፣ ቀጥሎም መንግስትን ከህወሀት ጋር ድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ። ለኢትዮጵያ ሁለቱም ተልዕኮዎች ለህልውናዋ አደጋው ከፍተኛ ነው። አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉትም የምዕራብያውያኑ ጥያቄ ተንኮል ያለው ወጥመድ ነው። ከዚያም ያለፈ ነው። ሀገር የሚያፈርስ መርዝ የተለወሰበት ጥያቄ ነው።

ምርጫው በኢትዮጵያ ህዝብና በመንግስት እጅ ይገኛል። ስለነገው ትውልድ፣ ስለመጪው የኢትዮጵያ ህልውና፣ ክብርና አንድነቷን የተረጋገጠች ሀገር የምንሻ ከሆነ ባለሁለት ስለቱን ካራ ወደ ጎን ገፍተን በቆራጥነት ኢትዮጵያን ማዳን ነው። ከዚህ ውጪ ያለው ምርጫ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ እንድትፋቅ ለተዶለተው ሴራ እጅ ሰጥቶ፣ ሀገር አልባ ሆኖ በመቅረት እድሜ ዘመንን በባርነት አንገትን ሰብሮ፣ ከሰው በታች ሆኖ መኖር ነው። ሁለቱም ምርጫዎች ዋጋ ያስከፍላሉ። አንደኛው ጊዜያዊ የሆነ፣ ሆዳችንን አስረን፣ ቀበቶአችንን ጠበቅ ካደረግን የምንሻገረው አደጋ ነው። ሁለተኛው ግን ዘላለማዊ የሆነ፣ ሀገር አልባ የሚያደርገን፣ ልጆቻችን ሀገር ብለው የሚኖሩባት ምድር የሚያሳጣችው፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያን የሚያፈራርስ ነው። ምርጫው አሁንም በእጃችን ነው።

Messay Mekonnen

Leave a Reply