Site icon ETHIOREVIEW

«ጁንታው ለህፃናት አደንዛዥ እፅ በመስጠት ለሞት እየዳረጋቸው ነው…»ትንሹ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ

“ሀሽሽ ይሰጡናል። ሳቡት እንባላለን። ስንስበው የምናደርገውን አናውቅም፤ ዝም ብለን እንጓዛለን፤ ጓደኞቻችን እየሞቱ እያየን ዝም ብለን እንሄዳለን

ግርማይ በሪሁን ይባላል። የ13 ዓመት ልጅ ነው። የተወለደው በአላማጣ አጠገብ በምትገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ግርማይ በእናትና በአባት እጅ ተቀማጥሎ የማደግ እድል አልነበረውም።

እናቱ በልጅነት እድሜው አልፈዋል። አባቱ የትዳር አጋር ትሆናቸው ዘንድ ሌላ ሚስት አገቡ። በጠዋት እድል የዞረችበት የሚመስለው ግርማይ ከአዲሰቷ ሴት ጋር አልተስማሙም። ቤት ጥሎ ወጣ። በአላማጣ ከተማም የጎዳና ልጅ ሆነ። የተገኘውን እየሠራ ሲገኝ እየበላ ሲታጣ ደግሞ ፆሙን እያደረ ሕይወትን ይገፋት ጀመር።

አሸባሪው ህወሓት በዚያ አካባቢ ያልፈፀመው በደል አልነበረም። ከበደል ሁሉ የከፋውን በደል ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ፈፀመ። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕግ ለማስከበር ተገደደ። ወሰደም። ብዙዎችንም ደመሰሰ፣ ብዙዎችን አሰረ፣ ጥቂቶች ዋሻ ውስጥ ገቡ።

በዚህ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት ሲወስደው የነበረውን የሕግ ማስከበር ርምጃ ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ይሆን ዘንድ ሲል ተኩስ አቆመ። የተረፉ የትህነግ ሰዎችም ከቀደመ ባሕሪያቸው ሳይድኑ ለሌላ ጦርነት ተዘጋጁ። ጦርም ለኮሱ።

የትግራይ ታጣቂዎች አካባቢዎችን እየወረሩ አላማጣ ከተማ ገቡ። ሕፃኑ ግርማይና ሌሎች ጓደኞቹ በአላማጣ ከተማ ተገኙ። ታጣቂዎችም በአላማጣ ከተማ ያሉ ሕፃናትን ይሰበስቡ ጀመር። ከግርማይ ጋር ሕፃናትን ሰብስበው የምትጭኑት ነገር አለ ብለው ወሰዷቸው።

“ኑ የምትጭኑት ነገር አለ ብለው ሰበሰቡን፣ ወስደው ካምፕ ውስጥ አስገቡን፣ በየቀኑ አንዳንድ ዳቦ ይሰጡን ነበር፣ በመካከል ግን ወደ ጦርነት አስገቡን፣ ወደ ድልብም ወሰዱን። በዚያም ቆዬን 25ቱን መልሰው ወደ ሃራ ወሰዱ በሃራ በነበረው ውጊያ 24ቱ ሞቱ እኔ ተረፍኩ። ከዛ መትረፌን ሳውቅ ወደመርሳ ሄድኩ። ሐይቅ ስደርስም ተያዝኩ” ነው ያለን።

“ሀሽሽ ይሰጡናል። ሳቡት እንባላለን። ስንስበው የምናደርገውን አናውቅም። ዝም ብለን እንጓዛለን። ጓደኞቻችን እየሞቱ እያየን ዝም ብለን እንሄዳለን። ክላሽ ተሰጥቶኝ ነበር። ዒላማ ግን አላስተማሩንም። ብቻ ሀሺሹን ስትጠቀም የማታደርገው ነገር የለም። አልስብም ያለ ይገደላል። እነርሱ እኛን ወደፊት ገፍተው ከኋላ ይቀራሉ። ፊት ፊት የሚሄደው ይሞታል” ነው ያለው ህጻኑ “ምርኮኛ”።

አሸባሪው ቡድን ውሸት ይነግራቸዋል። የሕልም እንጀራ ያበላቸዋል። ግፉ እናሸንፋለን፣ የሚያሸንፈን ኃይል የለም እያሉም እንደሚያታልሏቸው ነው የነገረን። ብዙ ሰው ሲረግፍ በትንሽ እድሜው አይቷል። “ለመከላከያ እጅ አትስጡ፣ ትሞታላችሁ ይሉናል። እኔ ግን ዝም ብዬ መጣሁ እንኳን ሊገድሉኝ ተንከባከቡኝ። እኔ ደህና ነኝ 24 ጓደኞቼን እያየሁ አጥቻለሁ። ሌሎቹ 25ቱ የት እንዳሉ አላውቅም። ሞተውም ይሁናል” ግርማይ በሀዘን ይናገራል።

ከዚህ ከመጣሁ ተመችቶኛል። ሌሎች ሕፃናትም እጃቸውን ይስጡና ከሞት ይትረፉ፣ ስናሸንፍ የመንግሥት ሥራ እንሰጣችኋላን፤ ብር ይሰጣችኋል እያሉ ነው የሚያታልሉት ነው ያለው። “አባቴ የት እንዳለሁ አያውቅም። – (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version