ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለራ ጉብኝት አገር ውስጥ ባለመኖራቸው ምክንያት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የተላኩትን በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን ጋር ተወያይተዋል።ይህን ተከትሎም ከገኡት እንግዳ ይልቅ የሄዱት አብይ ዜና ሆነዋል። በውይይቱ ሁሌም እንደሚባለው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ታሪካዊ ፣ የቆየ ፣ በጋራ ፍላጎትና ራዕይ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተጠቅሷል።
በቱርክ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ግብዣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑ የቱርክ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬትን ጠቅሰው የቱርክ ሚዲያዎች ዘገበዋል። ከቱርክ ጉብኝታቸው በላይ ዜና የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉብኝት ሲወጡ አሜሪካ የላከቻቸውን የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ለሶስተኛ ጊዜ አዲስ አበባ መግባታቸው ነው።
ሁኔታውን የተከታተሉና አስቀድመው የመልዕክተኛውን ወደ አዲስ አበባ መምጣት የሰሙ ” ምን ውይይት ያስፈልጋል? ትህነግ ካሁን በሁዋላ ክልል ሆኜ ልቀመጥ ነው የሚለው ወይስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ሕዝብና በትህነግ መካከል ያለውን ልዩነት አሜሪካ እያወቅች ምን አይነት ሽምግልና ነው የምታራምደው?” በሚል ሲያጣጥሉ ከርመው ነበር።
ሳምናታ ፓዎር አዲስ አበባ በነበሩበት ወቅት ያላነጋገሯቸው አብይ አሕመድ መልዕክተኛውን ላይ ቢሯቸውን ቆልፈው መሄዳቸው ከላይ ከተቀመጠው አስተአየቶች ጋር የገጠመ ይመስላል። እልህ መጋባቱን ያለወደዱ ቢኖሩም፣ “ፌልትስ ማን ዙሪያውን እየዞሩ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለመናድ እንደሚያሴሩ እየታወቀ ያን ያህል ክብር መስጠቱ አስፈላጊ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋማችሁን ቀይሩ ማለታቸው ትክክል ነው” ሲሉ የተደመጡ አሉ።
ጄፍሪ ፊልትማን የኢትዮጵያ ህዝብ ለትህነግ ያለውን ስሜት እንደሚረዱ፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪቃ አንድ ሆና ሚናዋን እንድትወጣ የአገራቸው ፍላጎት መሆኑንን ጠሰው በተቃራኒው ከትህነግ ጋር ለውይይት መቀመጥን እንደ አንድ አስገዳጅ ጉዳይ ማቅረባቸው እርስ በርሱ የሚቃረን የተንኮል አካሄድ መሆኑንንም የገለጹ አሉ። አሜሪካ በቀጣናው ፋልጎቷን ለማሟላት ሰፊው ህዝብ የሚፈልገውን እንጂ፣ የሚጠላውን በማድረግ እንዴት ሊሳካላት እንደሚችል ሊገባቸው እንደማይችል ያስታወቁ አሉ።
ተቀብለው ያናገሯቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ቢያውቁትም ለምብራሪያቸው መነሻ የሽብር ቡድኑ ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ስላደረሰው ጥቃት እንዲሁም ቡድኑ እየፈጸማቸው ያለው አስከፊ ድርጊቶች ለዚህ ችግር መነሻ መሆኑንን የአገር ውስጥ መገናኛዎች ገልጸዋል።
ወራሪው የሽብር ቡድን በአሁኑ ወቅት በአፋርና በአማራ ክልሎች ግልጽ ወረራ ፣ ዝርፊያና ግድያ በማካሄድ ከፍተኛ ሰብዓዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ወንጀሎችን እየፈጸመ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል። ቡድኑ እነዚህን ሁሉ ወንጀሎች እና ክህደት በሚፈጽሙበት ጊዜ የአሜሪካ መንግስት ዝምታን መርጧል ብለዋል። ይህም በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት ውስጥ ያልተለመደና የሁለቱን የወንድማማች ሀገሮች ግንኙነት የማይመጥን ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ አያይዘውም አሜሪካ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመጥን መልኩ የወራሪ ኃይሎችን አጥፊ ድርጊቶች እንደምትኮንነው ኢትዮጵያ ተስፋ ታደርጋለችም ነው ያሉት። ቡድኑ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ቀጠናውን እያወከ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአንክሮ ሊገነዘበው ይገባልም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፊልትማን በበኩላቸው፣ የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ በሽብር ቡድኑ ላይ ያለውን አመለካከት በሚገባ እንደሚረዳ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ፣ ሰላምና አንድነት ጠብቆ ማቆየትና ማረጋገጥ የአሜሪካ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ቀጠናዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ፎቶና መነሻ ዜና ፋና