በምዕራብ ጉጂ ዞን ከ40 በላይ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ተደመሰሱ


በምዕራብ ጉጂ ዞን የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ተቀናጅተው በወሰዱት እርምጃ ከ40 በላይ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ተደመሰሱ።

በተጨማሪም 35 ሲቆስሉ ሁለት ተማርከዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለ እንደገለጹት፤ ሸኔ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ ነው።

በግንባር የመዋጋት አቅም የሌለው ሸኔ ያልያዛቸውን ከተሞች ተቆጣጥሪያለሁ፣ መንገዶችን ዘግቻለሁ እያለ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህዝብን ለማሸበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በተለይ በምዕራብ ጉጂ ዞን መዳ መጋዳ አካባቢ ሰሞኑን በተወሰደው እርምጃ ከ40 በላይ የሸኔ አባላት መደምሰሳቸውን ኮሎኔል ግርማ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም 35 ሲቆስሉ ሁለቱ ተማርከዋል ነው ያሉት።

እንደአስተባባሪው ገለጻ፤ የዕዙ መምሪያ ከአካባቢው አመራር አካላትና ፀጥታ ዘርፍ ጋር በመናበብ የቀጠናውን ሠላም ለማረጋገጥ እየሰሩ ይገኛሉ።

በእዚህም ወደ ከተሞች ሰርጎ በመግባት ጥፋት ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በተወሰደው እርምጃ በየአቅጣጫው የሚበታተኑትን የሽብር ቡድኑ አባላት ለመደምሰስ መከላከያ ሠራዊቱ ተከታትሎ ቀጠናውን ነፃ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply