በጨጨሆ መድኃኔዓለም ገዳም ሥር የሚተዳደረው ዋሻ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በአሸባሪው ህወሐት ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ መመታቱን የደብሩ አስተዳዳሪ ገለጹ

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ላይ ጋይንት ወረዳ የፈለገ ጸሐይ በቅሎ አግት ጨጨሆ መድኃኔዓለም ካቴድራል ገዳም ሥር የሚተዳዳረው ዋሻ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በአሸባሪው ህወሐት ታጣቂዎች መመታቱን የደብሩ አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

የፈለገ ጸሐይ በቅሎ አግት ጨጨሆ መድኃኔዓለም ካቴድራል ገዳም አስተዳዳሪ መላእከ ጸሐይ አባ ብርሀነ መስቀል ይርጋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው በጨጨሆ መድኃኔዓለም ካቴድራል ገዳም ካደረሰው ጥቃት በተጨማሪ ለወረራ በመጣ ሰዓት በገዳሙ ሥር የሚተዳዳረውን ዋሻ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሰሪያ በመምታት ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሟል፡፡

የአሸባሪው ድርጊት የቤተ ክርስቲያንን ክብር ያዋረደና በሁሉም አቅጣጫ አገርን ለመበተን ያለመ በመሆኑ በተለይ በትግራይ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሊያወግዙት ይገባል፡፡

ገዳሙን ከዚህ ቀደም መሸሸጊያ አድርገውት እንደነበር የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ “አሁን ደግሞ ዒላማቸው ውስጥ በመክተት በደረጉት የከባድ መሳሪያ ጥቃት የቤተ ክርስቲያኑ መስታወት አርግፈዋል፡፡

ጣሪያውን አፍረሰዋል፡፡ ውስጥ ድረስ በመዝለቅ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ቦታዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ደርጊቱም አረመኔያዊ ነው ሲሉ ኮንነዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ ሁኔታ በገዳሙ ሥር ይተዳደር የነበረውን ዋሻ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በከባድ የጦር መምታታቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ጣሪያ ጨምሮ በውስጡ ባሉ የአምልኮ መፈጸሚያ ንዋያተ ቅዱሳን ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ባደረሰው ጥቃት በእጅጉ ማዘናቸውን የገለጹት የደብሩ አስተዳዳሪ፤ “ቤተ ክርስቲያኑ ትልቁ ማንነታችን ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ከሩቅ የሚመጡ እንግዶች የሚያርፉበት ነው፡፡ ነገር ግን ክፉዎች ጎድተውት ሄደዋል፤ እግዚአብሄር ይፍረድ ሲሉ” ሀዘኔታቸውን ገልጸዋል፡፡ የተጎዳውን ቤተ ክርስቲያን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በትብብር ወደነበረበት እንዲመልሰው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ ውጭ ናት ያሉት አስተዳዳሪው፤ በታሪክ የእነርሱን ያህል አረመኔ የለም፤ ቤተ ክርስቲያንን መደብደብ ማለት የመጨረሻ ሰዓት ላይ መድረሳቸውን ነው የሚያሳየው፤ ይህ ድርጊታቸው አረመኔነታቸውና ተስፋ የቆረጡ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው አስተያየት፤ ቤተ ክስርስቲያንን መምታት በቤተ ክስርስቲያን ውስጥ ያሉ ታሪኮችና ቅርሶችን ማጥፋት በመሆኑ የእነርሱ ሥራም ታሪክን ማውደም ላይ ያተኮረ ነው ፡፡ የጠላት ዓላማ አገርን፣ ማንነትን ሀይማኖትን ማጥፋት ነው፡፡ በዚህም የግለሰብ ቤትና ንብረትን ጨምሮ የሀይማኖት ተቋማትንም የመንግስት ተቋማትንም የማውደም ዓላማቸውን እያሳኩ ይገኛሉ፡፡

አሸባሪው የቤተ ክርስቲያንን ክብር በሚያዋርድ መልኩ ቆብና ካባ እያስለበሰ አስነዋሪ ድርጊቶችን በመፈጸም ላይ በመሆኑ የእምነት አባቶች በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ጠቅሰው፤ በተለይ በትግራይ ያሉ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም አዛውንቶች እንዲህ አይነቱን ድርጊቶች ሊያወግዙት ይገባል ብለዋል፡፡

ይህ ቀን እንደሚያልፍ ተረድተው የህይወት መስዋእት መክፍል ካለባቸውም ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም ሲሉ መክረዋል፡፡ (ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply