[የዘመን ሃቅ] አለማየሁ እሸቴ ” ማን ይሆን ትልቅ ሰው?”

“ማን ይኾን ትልቅ ሰው”

ደራሲ፥ ተስፋዬ አበበ

ያንዱ ቤት ሲጎድል አንዱ እየተረፈው፣

ክፉና በጎዉን ዘመን ሲያሳልፈው፤

እኔ ግን መራመድ ከቶ አልቻልኩም ገና፣

ትኋን ደሜን መጦ ጨርሶታልና፣

ያ'ሥር ሣንቲም ቆሎ ክርሽም አደርግና፣

አንዷን ጣሣ ውኃ ጭልጥ አደርግና፣

ተመስገን እላለሁ ኑሮ ይባልና፤

መኖር በዚህ ዓለም ከፍላጎት ጋር ነው፣

ልናዘዝ በቁሜ ያጣ እንደሞተ ነው፤

የዬዬ ወሸኔ የዋኔ ጭፋሮ፤

እዚያው ፈላ ሞላ ላምናም ለዘንድሮ፤

ጊዜ ጎዳኝ እንጂ እኔ ስው አላማ፣

የአህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ፤

እውነት ስትጠፋ ፍርዱ ሲጓደል፣

ሕጉ ላለው ሆነች ቂም ለመበቀል፤

እጅ እግር አጣምሮ ትራስ ተንተርሶ፣

የበሉት እንጀራ ይወጣል ደም ጎርሶ፤

Ethio 12

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሲነሳ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ድምጻውያን መካከል አንዱ ነው። ከኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ሸክላ ህትመትም ጋር ስሙ አብሮ ይነሳል።

የሙዚቃ ሥራቸውን በሸክላ ቀድመው ካሳተሙ የመጀመሪያዎቹ ድምጻዊያን መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል-አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ።

አለማየሁ የተለያዩ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ በሙዚቃ ወዳጆች ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ክብር አስገኝተውለታል።

በቄንጠኛ አለባበሱና የፀጉር ስታይሉ [አበጣጠሩ] በዘመኑ ወጣቶች ልብ ውስጥ የገባም ነበር።

ድምጻዊ አለማየሁ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረበት የልብ ህመም ምክንያት በ79 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ድምጻዊ አለማየሁ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን እስከ ሦስት ዓመቱ ድረስ ከእናቱ ጋር ደሴ ነበር ያደገው። ከዚያም የሦስት ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ ወደ አዲስ አበባ አመጡት። አዲስ አበባ መጥቶም ‘ክርስቲያን ትሬኒንግ ኢንስቲቲዩት’ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን መከታተሉን ለሸገር ተናግሮ ነበር።

በትምህርት ቤቱም መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመር ይታወቅ ነበር፤ በእንግሊዝኛ ቋንቋም ጭምር። ድምጹም እጅግ የተወደደ ነበር።

እንዲህ እንዲህ እያለ የሙዚቃው ስሜት እየኮረኮረው መጣ። በዘመኑ ተወዳጅና እውቅ የነበሩ የምዕራባውያን ድምጻውያንን ሙዚቃ ማንጎራጎር ያዘ።

በተለይ የሮክ የሙዚቃ ስልት ለአለማየሁ ነፍሱ ነበር።

የአሜሪካውያኑን ድምጻዊያን ፓት ቦን፣ ቢል ሃሊይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊን የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አብዝቶ ይጫወት ነበር።

የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃ አብዝቶ በመጫወቱ፣ በፀጉር አበጣጠሩና ዘመናዊ አለባበሱ ‘ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ’ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶታል።

አለማየሁ ስለፀጉር አበጣጠሩ “የፀጉር ስታይሉ ረዥም ስለነበር፤ ፀጉሬ አፍንጫየን ሸፍኖት ነበር የምሄደው” ሲል በአንድ ወቅት ለሸገር ራዲዮ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግሮ ነበር።

በዚህ እውቅናን እያተረፈ የመጣው አለማየሁ በጀነራል ዊንጌት፣ በዳግማዊ ምንሊክና በሌሎችም ትምህርት ቤቶች እየተጋበዘ ይዘፍን ነበር።

በወቅቱ ለአማርኛ ዘፈን ግድ አልነበረውም፤ እምብዛም አይጫወትምም ነበር።

“ከዘፈንኩም የጥላሁን ገሠሠን ‘እንክርዳድ እንክርድድ የተንከረደደ’ የሚለውን ነበር” ብሏል በዚያው ለሸገር በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ።

ለዚህ ደግሞ ይመለከታቸው የነበሩ የምዕራባውያን ፊልሞች አስተዋፅኦ ነበራቸው።

በአዲስ አበባ እምብርት -ፒያሳ የነበረው ‘አድዋ ሲኒማ’ እና አሁንም ድረስ ያሉት ‘ኢምፓየር’ እና ‘ኢትዮጵያ’ ሲኒማ ቤቶች በወቅቱ የሚያሳዩት የምዕራባውያን ፊልሞችን ነበር።

አለማየሁ ጎራ እያለ የሚኮመኩማቸው እነዚህ ፊልሞች የልጅነት ቀልቡን ይስቡት ነበር።

በሆሊውድ የፊልምና የሙዚቃ ሥራ ልቡ የሸፈተው አለማየሁ ወደዚያው ሊያቀናም ጉዞ ጀምሮ ያውቃል።

አለማየሁ ከአባቱ ኪስ ያገኛትን መቶ ብር ይዞ ነበር ከጓደኛው ጋር ሆሊውድ ለመድረስ መንገድ የጀመሩት፤ ይሁን እንጂ ያለሙበት ሳይደርሱ ምጽዋ ላይ ተይዞ ወደ ቤተሰቡ ተመልሷል።

እዚያ በቆዩበት ጊዜም ያቀነቅናቸው በነበረው ምዕራባውያን ዘፈኖቹ የምፅዋ መርከበኞችን በፍቅሩ ጥሏቸው እንደነበር ይነገራል።

አለማየሁና የሙዚቃ ሥራዎቹ

ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አዲስ አበባ ውስጥ በአርበኞች ትምህርት ቤት እየተከታተለ ባለበት ወቅት ነበር ነፍሱ ለሙዚቃ አድራ በ1955 ዓ.ም የፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራን የተቀላቀለው።

እዚያው ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለአድናቂዎቹ አድርሷል።

ከዚያ በኋላ በሮሃ ባንድ፣ በሸበሌ ባንድ፣ በአይቤክስ ባንድ፣ በዓለም ግርማ ባንድ፣ የራሱ በሆነው ሶሊኮስ ባንድ እና በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን አበርክቷል።

‘የወይን ሐረጊቱ’፣ ‘እንዲህ ነው ወይ መውደድ’፣ ‘ማሪኝ ብየሻለሁ’፣ ‘ማን ይሆን ትልቅ ሰው’፣ ‘እንደ አሞራ’፣ ‘ምሽቱ ደመቀ’፣ ‘ችግርሽ በእኔ አልፏል’፣ ‘የሰው ቤት የሰው ነው’፣ ‘ደንየው ደነባ’፣ ‘ወልደሽ ተኪ እናቴ’፣ ‘ለሰሚው ይገርማል’፣ ‘ማን ይሆን ትልቅ ሰው’፣ ‘ስቀሽ አታስቂኝ’፣ ‘የአባይ ዳር እንኮይ’፣ ‘ኮቱማ ፍቅርዬ’፣ ‘አዲስ አበባ ቤቴ’፣ ‘እንግዳዬ ነሽ’፣ ‘ተማር ልጄ’ እና ሌሎችም።

‘ተማር ልጄ’ እስካሁንም ድረስ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚገስፁበትና የሚመክሩበት እንዲሁም የትምህርት ጉዳይ በሚወራበት ቦታ ሁሉ የሚነሳ የሙዚቃ ሥራው ነው።

ይህ የሙዚቃ ሥራው ከተሠራ ከ35 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በዚሁ ዘፈኑም እአአ በ2015 በጀርመን አገር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ድምጻዊው በሥራዎቹ በኢትዮጵያ በሚዘጋጀው የ5ኛው ለዛ ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚም ነበር።

“በብዙኃኑ ሀቅ የሚሸቅጥ አርቲስት መሆን አይገባውም”

አለማየሁ ኪነ-ጥበብ የዘመኑን ሀቅ ይዞ መሄድ አለበት የሚል እምነት አለው። ያለ ፍርሃትም ለወቅቱ አስጊ የነበሩ ዜማዎችንም ተቀኝቷል። ለዚህም ነው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ዘፈኖችን ያለ ፍርሃት ያቀነቀነው።

“ሃይ ዘራፍ እያሉ እያረረ አንጀቴ፣

እኔስ አረባሁም ወልደሽ ተኪ እናቴ” የሚለውን የፍትሕና እኩልነት መጓደልን የተናገረበትን ስንኝ በዋቢነት መምዘዝ ይቻላል።

“በሕይወቴ መፍራት አልወድም። አርቲስት ማለት ብዙኃኑ ሲራብ የሚራብ፣ ሲቸገር የሚቸገር፣ ታሪኩንና ጀግንነቱን በግልጽ የሚናገር እንጂ የብዙኃኑን ሀቅ የሚሸቅጥ ከሆነ አርቲስት መሆን አይገባውም” ሲልም በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።

ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ በቤተሰብ ሕይወቱም በአርአያነት ይጠቀሳል። የዝነኛነትን ጎራ ሳይቀላቀል ከተዋወቃት ፍቅረኛውና ባለቤቱ ጋር ከአርባ ዓመታት በላይ በሞቀ ትዳር ውስጥ ቆይቷል። ሰባት ልጆችን አፍርተው የልጅ ልጅም አይተዋል።

አለማየሁ ባለቤቱን ‘አባየ’ ሲል ነው የሚጠራት። በአንድ ወቅት ምክንያቱን ተጠይቆ “እናቴ ከሞተች በኋላ እናቴ እርሷ ናት” ሲል ነበር የመለሰው። ‘በአገርና በሚስት ቀልድ የለም’ ከሚሉት ወገንም ነበር አለማየሁ።

ኮፒ ከቢቢሲ አማርኛ

የአለማየሁ እሸቴ ድንገተኛ ህልፈት በርካቶችን አስደንግጧል፤ በርካቶችም የተሰማቸውን ሐዘን እየገለጹ ነው።

የድምፃዊው ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድምፃዊው ህልፈት የተሰማውን ሀዘን አየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ

  • ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴበአንጋፋው ድምጻዊና ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ ድምጻውያን አንዱ የሆነው አርቲስት አለማየሁ እሸቴን ዜና እረፍት እጅግ አዝኛለሁ፤ ዘመን ተሻጋሪና ቁም ነገር አዘል ግጥምና ዜማዎቹ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ለዘለዓለም ይኖራሉ ብለዋል፣
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀገሩን አጥብቆ በመውደድና ለሀገሩ ከልብ በመሥራት ለብዙ ከያንያን አርአያ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴ በማረፉ እጅግ አዝኛለሁ፤ ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ይኖራሉ። ለኢትዮጵያ የሠራ ያርፋል እንጂ አይሞትም ብለዋል፣
  • ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንበኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያበረከተልን ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ፍሬዎቹ በቀጣይ ትውልድን እያነፁ የሀገርን ከፍታ እያሳዩ የሚዘልቁ ናቸው ብለዋል በመልዕክታቸው፣
  • የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤበአለማየሁ እሸቴ ህልፈተ ህይወት እጅጉን አዝኛለሁ፤ ዓለማየሁ እሸቴ ለሚወዳት ኢትዮጵያ በጥበብ ስራዎቹ ብዙ ያደረገ ሃገር ወዳድ ባለሙያ ነበር ብለዋል፣
  • የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ኢትዮጵያ የብዙ ሀገር ወዳድና ሀገራቸውን በኪነጥበቡ መድረክ ከፍ የሚያደርጉ ህዝቦች ያሉባት ምድር ናት፤ ስለሀገሩ የሚሰራውን አንጋፋ አርቲስት አለማየሁ እሸቴን አተናል ብለው፤ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ለሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ተመኝተዋል። በአንድ ወቅት አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበረው ቆይታ “የቀድሞ ሹማምንቶችና ገዢዎችን ብንመለከታቸው በነበሩበት ዘመን ሁሉ የዘሩት ክፋትና አመጽ ነበር፤ ሰው እርስ በእርስ የሚባላ የማይስማማ ሆኖ ቆይቷል….” ሲል ሃሳቡን አጋርቶን ነበር።

Leave a Reply