ማነው የእናቶችን እንባ የሚያብሰው፣ ማነው የልባቸውን ስብራት የሚክሰው፣ ስንቶች አልቅሰዋል፣ ስንቶች በግፍ ቤታቸውን ዘግተዋል፣ እናቶች አባቶቻቸውን ያጡ ልጆችን እንዲያሳድጉ ተገድደዋል፣ እናት እና ልጅ፣ ባልና ሚስት እየተነፋፈቁ ተለያይተዋል።

ለዚያውም እስከ ወዲያኛው፣ እስከመጨረሻው። እንባቸው እንደ ዥረት ያለማቋረጥ ይፈስሳል፣ አንጀታቸው እርር እያለ ይላወሳል፣ ሳግ እየተናነቃቸው ያችን ክፉ ቀን ያስታውሳሉ። የልጆቻቸውን አባት እያሰቡ ይባትታሉ። ቤታቸው ተዘግቷል፣ ማዕረጋቸውን ተነጥቀዋል። ግርማቸውን ተገፈዋል፣ አምሳላቸውን አጥተዋልና ዋይታቸው ልብን ይሰብራል። ፈጣሪያቸውን አምነው፣ የጎተራቸውን ዘር ከማሳ ላይ በትነው፣ አርሰው፣ አንደፋርሰው፣ ከሰፊ አውድማ ላይ ምርታቸውን አፍሰው ከመብላት ውጭ ቂም አልፈጠረባቸው፣ በደል አልተገኘባቸው፣ ግፍ አልፈጠረባቸውም፣ ዳሩ የምድር ግፍ በእሳቸው ላይ አረፈባቸው፣ በደል ሳይገኝባቸው በደል ተፈጸመባቸው፣ ግፍ ሳይገኝባቸው ግፍ ተሰራባቸው።

ፈሪ የመታውን ሳይሆን የተመለከተውን ይማታል። ለመታው አቅም ሲያንሰው እጁን ከንፁሃን ላይ አነሳ። በማይጠብሪ ግንባር የገባው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወቅን ቆርጦ ሊመጣ ሲል እስከ ወዲያኛው ተቆረጠ። ብዙው ተደመሰሰ፣ እጅ ሰጠ። ሌላውም ነብስ አውጭኝ ፈረጠጠ። ታዲያ የፈራው ሲመለስ ዝም ብሎ አልተመለሰም፣ የጀግኖችን ዱላ አልቻለም ነበርና ንፁሃንን እየገደለ ሮጠ።

በዳባት ወረዳ የፍኖተ ሰላም መድኃኔዓለም ዙሪያ በዋይታ ተመልቷል፣ እናቴ፣ አባቴ፣ እህቴ ወንድሜ እያለ የሚያለቅስ ድምጽ ከሩቅ ይጠራል። ወደ ውስጥ ተጠጋን፣ ደረታቸውን የሚደቁ፣ ፊታቸውን የሚነጩ ብዙዎች ናቸው። ልብ ይሰብራል፤ ያሳዝናል። እነርሱን አይቶ እንባውን የሚቆጣጠር ማን አለና? ከእነርሱ ጋር ያለቅሳል እንጂ። አንድም በሰሪው አልፈረሰም፣ ይልቅስ በግፈኞች ፈርሰው፣ ተገድለው ነው ወገኖቻቸውን የሚያስለቅሱት፣ እርሱ እንደሠራቸው በቀናቸው ቢወስዳቸውማ የእርሱ ኀይል አይደል፤ ማን ያመዋል፣ ማንስ ይወቅሰዋል፣ ስልጣኑ የእርሱ ነውና።

በማይጠምሪ ግንባር በጭና ቀበሌ ግፍ የደረሰባቸው ናቸው በፍኖተ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የሚያለቅሱት፣ የሚያስለቅሱት፣ ወደ አንደኛዋ እናት ተጠጋሁ፣ እንባቸው እየተናነቃቸው፣ ሳግ እየያዛቸው ማውራት ተስኗቸዋል። ወይዘሮ ካሳዬ ዘውዱ ይባላሉ፣ አንጄታቸውን ስለ አሳረረው ነገር ጠየኳቸው። ባለቤታቸውን ሰማኝ ብርቁን በግፍ ተነጥቀው ነው የሚያለቅሱት። “ኧረ ተዎኝ ልጄ ውኃው በልቶኛል ቀኑ ጨልሞብኛል። ምኑን ነግሬህ፣ በደሌን እንዴት ልናገር?” የእንባቸው ብዛት ሰው መሆንን ያስጠላል።

ለማጽናናት ሞከርኩ፣ በደላቸውን ይነግሩኝ ጀመር ”ቤቴን ዘግቼ ልጆቼን ይዤ ተቀምጨ ነበር፣ ባለቤቴ ለከብቶች ሳር ላጭድ ብሎ ወጣ፣ እባክህን ይገድሉሃል አትውጣ አልኩት። ዝም ብሎኝ ወጣ። ሳሩን አጭዶ ተመልሶ ቤት ሊገባ ሲል ስምንት ሆነው መጥተው ድፍት አደረጉት“ ነው ያሉኝ። እንባቸው እንደ ዥረት መፍሰሱን ቀጥሏል፣ አንጄታቸው ይንሰፈሰፋል “ድፍት አድርገውት ሲሄዱ እየጎተትኩ ወደ ቤት አስገባሁት፣ ከልጆቼ ጋር አልጋ ላይ አስተኛሁት፣ ከአምስት ልጆቼ ጋር አቅፌው ተኛሁ። ውጣ እያሉ ተኮሱብን፣ ሬሳውን ከሕፃናቶቹ ጋር ታቅፌ ድምጤን አጥፍቼ ዝም አልኩኝ። ሳንቃው እንጨት ስለነበር አተረፈን።

ሦስት ቀን ቆየሁ። በሦስተኛው ቀን መከላከያው ደረሰ። መከላከያው ከብቶቼን ሁሉ ፈትቶ አወጣኝ። ልጆቼን ይዤ ወጥቼ ዘመድ ጠርቼ ባለቤቴን ቀበርኩ” አሉኝ ምን አይነት ፍርጃ ነው፣ ምን አይነት በደል ነው፣ ካሳው ስንት ነው? የእነዚያን ትንንሽ ልጆች ልብ ማነው የሚጠግነው? ሀሙስ ተገድለው እሁድ ተቀበሩ። ” እህህህ….. ማይረጌ ኩራቴ፣ አራሹ ገበሬ ወይኔ፣ አራሽ ነው፣ አርሶ ከመብላት ውጭ ሌላ አያውቅም። ጀግናዬን ነው የገደሉት“ በተሰበረው ልባቸው እያስታወሱ በለቅሶ ጥለውኝ ጭልጥ አሉ። እንባቸው የውስጣቸውን በደል ጠርጎ ያወጣላቸው ዘንድ ዝም አልኳቸው። ያለ ከልካይ አፈሰሱት፣ አንጄቴን አላወሱት።

ከመሞታቸው በፊት ስለነበረው ሲያስታውሱ “አንቺ ልጆችሽን ይዘሽ ሂጅ አለኝ፣ አንተም እንሂድ አልኩት አልሄድም አለኝ። እኔም አንተን ጥዬ አልሄድም አልኩት። በዚያው ተቀመጥን፣ እሺ ቤት ውስጥ ሁን አልኩት፣ ከብቶቹ እምቧ እምቧ ሲሉ አሳዘኑት፣ ቤቱን ከፍቶ ወጣ። ለከብቶች ሳር ይዞ ሲመጣ ማነህ ብለው ድፍት አደረጉት” ነበር ያሉን። ልጆቻቸው ያለቅሳሉ፣ እሳቸውም እንደዚያው ነው። ቀኑም ሌሊቱም ጨልሟባቸው ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ በወሰደው ርምጃ እያለቁ ሄዱ የመከላከያውን በትር መቋቋም ሲያቅታቸው ቄሶችንም እያወጡ ገደሏቸው። ሕፃናትን መቷቸው። ሠራዊቱ ሲያቀምሳቸው የንዴት መወጫ አደረጉን ነው ያሉን።

”ቢቆዩ ሁላችንም ይጨርሱን ነበር፣ በመከላከያ ሠራዊት ልጆቼን አተረፍኩ፣ መከላከያው እስኪበቃቸው አቀመሳቸው። እኔ ግን ያለ አጋዥ ቀረሁ። ብቻዬን ቀረሁ ነው ያሉን። አሸባሪው ትህነግ በዚያ አካባቢ በርካታ ንፁሃንን ገድሏል። ዳሩ እርሱም ሞቷል። በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ያለውን ዋይታ የሰማ ሁሉ ጌታ ሆይ ምነው ዘገየህ፣ ክንድህን አንሳ፣ ጠላቶችን ቅጣ እንጂ እስከ መቸ ትታገሳለህ፣ እስከ መቸ እድሜ ትጨምርላቸዋለህ፣ ፊትህን አዙር፣ በኀይልህም ቅጣ እንጂ ይላል።

አዎን ሞቱ ቢመርም ድሉ ግን አይቀርም። በጀግኖች ቆራጥነት የትግራይ ወራሪ ይደመሰሳል። እንባ የበዛባቸው እናቶችም ይካሳሉ። ዋይታቸው እየተከተለኝ ከአጠገባቸው ራኩኝ። በግፍ ወገኖቻቸውን የተነጠቁ ንፁሃን እንባ አልለይህ አለኝ።

ታዲያ ይህን አረመኔ ቡድን ማን ዝም ይላል? አይደለም ተግባሩ ስሙ እንዲጠፋ ማጥፋት እንጂ።

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ – ከማይጠብሪ ግንባር ደባርቅ፡ ጳጉሜን 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

Leave a Reply