ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክክር ውጥን (MIND Ethiopia) የተባለ የስምንት ሀገር አቀፍ ተቋማት ጥምረት፤ ከአራት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ። ሀገራዊ የምክክር መድረኩ “በጣም ዘገየ ከተባለ በታህሳስ ወር” እንደሚካሄድ ከጥምረቱ አባላት አንዱ የሆነው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚስተዋሉ ስር የሰደዱ ችግሮች “ዘለግ ያለ መፍትሔ ማበጀት” እንደሆነ ዛሬ ሐሙስ ጷጉሜ 4፤ 2013 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል። በምክክሩ ላይ 22 ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።  

ከባለድርሻ አካላቱ ውስጥ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ሴቶች፣ ህዳጣን ማህበረሰቦች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን እና የዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮች ይገኙበታል ተብሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ ጉልህ የተሳትፎ ሚና እንደሚኖራቸው በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።  

የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ

ከሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ጋር በተያያዘ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በውጊያ ላይ የሚገኘው የህወሓት ተሳትፎ ጉዳይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ አስነስቷል። “ማይንድ ኢትዮጵያ” ከሰባት ወራት በፊት ባካሄደው የቅድም ምርጫ ምክክር ላይ ህወሓት አለመሳተፉን አቶ ንጉሱ አስታውሰዋል። መጪው የምክክር ሂደት “ሁሉን አካታች መሆኑን” አጽንኦት የሰጡት የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ፤ “ነገር ግን እከሌ ካልገባ ይህንን ሂደት አናካሂድም ብለን ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ህወሓት በተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት መፈረጁ፤ በምክክር መድረኩ የመሳተፍ እድሉን ያሳጣው እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ንጉሱ፤ “በመርህ ደረጃ ማንንም አናገልም። ነገር ግን በህግ ጉዳይ እኛ የምንቀይረው ነገር የለም። የታሰሩ ሰዎች ተፈትተው ይሳተፉ ማለትም አንችልም” ሲሉ መልሰዋል።  

“በመርህ ደረጃ ማንንም አናገልም። ነገር ግን በህግ ጉዳይ እኛ የምንቀይረው ነገር የለም። የታሰሩ ሰዎች ተፈትተው ይሳተፉ ማለትም አንችልም”

አቶ ንጉሱ አክሊሉ – የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ

በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ መንግስት ሊኖረው የሚችለው ሚናም ሌላው ጥያቄ የተነሳበት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያውያን ለአካታች የምክክር መድረክ የተሰኘው ድርጅት አባል የሆኑት ዶ/ር አንዳርጌ ታዬ፤ በመርህ ደረጃ የምክክር መድረኩ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የምክክር መድረኩን የሚያመቻቸው ጥምረት ውስጥ፤ መንግስታዊው የሰላም ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ መንግስት በአዋጅ የተመሰረተው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ናቸው። ከስምንቱ የጥምረቱ አባላት መካከል በኢትዮጵያ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይገኝበታል።  

የባልደራስ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታነህ ባልቻ

በመጪው ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ ይሳተፋሉ ተብለው ከሚጠበቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ ይጠቀሳሉ። የባልደራስ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የምክክር መድረክ ላይ ህገ መንግስቱን የማሻሻል ጉዳይ በአብይ አጀንዳነት መያዙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ፓርቲያቸው ከምክክር መድረኩ በኋላ “ህገ መንግስቱን የማሻሻል እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት የሚያስችል መሰረት ይመቻቻል” ብሎ እንደሚጠብቅ ጠቁመዋል። የባልደራሱ ምክትል ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ምክክር መድረኩን “መልካም ጅማሮ” ሲሉ ቢጠሩትም፤ በምክክር መድረኩ የሚነሱ ሀሳቦች “በመንግስት ተፈጻሚ ላይሆኑ ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳለባቸው ግን አልሸሸጉም። 

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም

የምክክር መድረኩን “ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ አስቀድመን ማድረግ ብንችል ብዙ ሊጠቅምን ይችል ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የሰጡት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም፤ ምክክሩ ሁሉንም ችግሮች ባይፈታም ለአብዛኛዎቹ ችግሮች ምክንያት ለሆኑት ዋና ዋና ችግሮች መፍትሔ ያበጃል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በምክክር መድረኩ የህገ መንግስት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች፣ ፍትሃዊ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል እንዲሁም የሀገረ መንግስትና የማህበረሰብ ግንባታ በዋና አጀንዳነት ይነሳሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።     

መጪውን ሀገራዊ የምክክር መድረክ የሚያመቻቸው “ማይንድ ኢትዮጵያ” ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ያለመ መድረክ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ነበር። ይህ የጥምረቱ ዕቅድ የተደናቀፈው በጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት እንደሆነ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።። በሀገሪቱ የሚከሰቱ “ተገማች ያልሆኑ የጸጥታ ችግሮች” የምክክር መድረኩ የሚካሄድበትን ወቅት ለመወሰን አዳጋች እንዳደረገውም አስረድተዋል። 

ምንጭና ፎቶ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Reply