“ሸውራራው” የ(CNN) ዘገባ – ማንም ያድርገው ማን የከፋ ወንጀል ነው፤ ማይካድራ፣ ጪና፣ጋሊኮማስ ?

የሲ ኤን ኤን ዘገባዎች እጅግ የተጠናበሩና ፈር የለቀቁ ስለመሆናቸው ከበቂ በላይ ምስክር ማስረጃ ማቅረብ እንደሚቻል በርካቶች ገልጸዋል። ለሲ ኤን ኤን ለራሱ በአድራሻና በተመሳሳይ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በቲውተር ” እባቦች” ለማለት የደፈሩትን ጨምሮ ብዙ ተነግሮዋቸዋል። “ያደቆነ ሰይጣን ስያቄስ…” እንዲሉ ሆነና የሚሰሙ አልሆኑም። እንደውም “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር – ትህነግ በጦር ሜዳ ሲወቃ የእነሱ አፍ ይከፈታል።” የሚለው ትችት እየበዛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ያሚያወድሷቸውና ” ሃቀኛ የክፉ ቀን ደራሽ” የሚሏቸው የትህነግ ደጋፊዎች የምስጋናና አድናቆት ያጎርፉላቸዋል።

በዜግነት እንግሊዛዊት፣ በትውልድ ሱዳን የሆነችው ኒማ ኤልባጊር ተከዜ ወንዝ ተንሳፎ የተገኘን አስከሬን ምስል እያሳየች ጭካኔን በሚገልጹ ቃላቶች ያሳየችው ዘገባ ማንም ፈጸመ ማን? ማንም ላይ ቢፈጽም፣ ምንም ዓይነት ምድራዊ ምክንያት ሊቀርብበት የማይችል ግፍና ወንጀል ነው። አንድ ዜጋ በብሄሩም ሆነ በአመለካከቱ የተነሳ በዚህ መልኩ ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረግ ወይም ገሎ መጣል እጅግ የተዋረደና ቃላት ሊገልጹት የማይቻለው የሃፍረት ሃፍረት ነው።

ይህ ሲ ኤን ኤን ያወጣው ዘግናኝ መረጃ ይፋ ከመሆኑ በፊት ትህነግ በጦር ሜዳ የተገደሉበትን ምስኪን ዜጎች አስከሬን ወደ ተከዜ እያጓጓዘና የጅምላ መቃብር አዘጋጅቶ ” ተጨፈጨፍን” በሚል የኬኖሳይድ ክስ ለማሰማት በዝግጅት ላይ እንደሆነ እየተገለጸና ለዓለም ሚዲያዎች እየተነገረ ነበር። ተከዜ ተንሳፈው የተገኙ አስከሬኖች መኖራቸውን የሱዳን ባለስልጣናት ሲያስታውቁም ነበር። ኒማ እስከዛሬ የት እንደቆየች ባይታወቅም ይህን የቆየ ሪፖርት ልክ የጪና ጭፍጨፋ ይፋ ሲሆን፣ ትህነግ በከበባ ውስጥ ሲገባ ብቅ ማደረጓን ” የሸውራራነቷ ማሳያ ቁጥር አንድ” ሲሉ የገለጹ አሉ።

የቱር ኤምባሲን “ድሮን ለኢትዮጵያ አትሽጥ” በሚል የትህነግ ደጋፊዎች በተለያዩ አገራትና በተደጋጋሚ ተቃውሞ በሚያሰሙበት፣ መከላከያ ሽሬና ውቅሮ አፍንጫ ስር በደረሰበት በአሁኑ ወቅት የኒማ ሪፖርት መውጣቱ በትህነግ ሰዎች ዘንዳ ደስታን ፈጥሯል። ምክንያቱም በትህነግ የጦር ሜዳ ግስጋሴ ጋብ ብሎ የነበረው ተጽዕኖ መልሶ ያጋግል ዘንድ ትልቁን ድርሻ ስላለው ነው። ለዚህም ይመስላል ዜናው የድል ያህል እየተበተነ ያለው።

See also  ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላት ሁለንተናዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጠ/ሚ ዐቢይ

የሲ ኤን ኤን ዘገባ ምንም ዓይነት እንደምታ ቢኖረውም መንግስት ቁብ ያለው ግን አይመስልም። ይልቁኑም የመስከረም መጥባትን ተከትሎ መሬቱ ሲጠግና ለተሽከርካሪ አመቺ ሲሆን፣ ከላይ ሰማዩ ወለል ሲል ሁሉም ነገር እንደሚያበቃ እያስታወቀ ነው። በትህነግ በኩልም ሃይል የመፐወዝና ጥቃትን ለመቋቋም ዳግም የመደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑ እየተነገረ ነው። በዚህ መካከል እጅግ አዕምሮን የሚፈታተነው የሲኤኔንኤን ዘገባ ልክ የጪናን ጭፍጨፋ ታኮ ይፋ መሆኑ እንደተለመደው ኢትዮጵያን ለመክሰስ የታሰበ መሆኑንን የመንግስት ሚዲያ የሆነው አዲስ ዘመን አመልክቷል።

ትህነግ የአማራ ክልልን ወሮ የፈጸመውን ግፍና ጭፍጨፋ እንዳላየ ያለፈውን ሲ ኤን ኤን የተቃወመው አዲስ ዘመን ኒማ ምስክር አድርጋ ያነገረችው ገሬ ትህነግ መሆኑንንም አጋልጧል። አብሯት አጅቧት የነበረውንም አካል ማንነት ጠቅሶ ነው ” ሚዛን ስተሻል” ሲል ኒማን የወረፋት። መረጃውን በማስተባበል መልኩ ደምቶ ያልተሰራው የአዲስ ዘመን ትችት እንደ አንድ የመንግስት ሚዲያ በትልቅ ጉዳይ ላይ ትልቅ ትኩረት የሰጠ አይመስልም።

አዲስ ዘመን የሚከተለውን ጽፏል። ያንብቡት

ሀቅን የረሳው የሲኤንኤን (CNN) ዘገባ

“አሰቃቂው ዕይታ” የሚል ርዕስ የሰጠውን እና በሁመራ ተፈፅሟል ያለውን ግርፋት፣ ጅምላ እስር እና ግድያን በተመለከተ የምርመራ ዘገባ አቅርቧል።እነዚህ ግርፋት፣ ጅምላ እስር እና ግድያ የተፈፀሙት “በኢትዮጵያ ሠራዊት እና አጋሮቹ” ሲል በገለጻቸው ኃይሎች መሆኑንም ምስክሮቹን ጠቅሶ ደምድሟል። የዚህ የምርመራ ዘገባ መነሻ የሆነው በሱዳን ድንበር አካባቢ በሚገኝ ወንዝ ላይ የሚንሳፈፉ አስከሬኖች ዳግም መገኘታቸው እንደሆነ ሚዲያው ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ የዘገባው አዘጋጅ የሆነችው ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ ኒማ ኤልባጊር ለምስክርነት የመረጠቻቸው ሰዎች ገለልተኛ አለመሆን እና የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ደጋፊዎች መሆናቸው የዘገባውን ተዓማኒነት አጠያያቂ አድርጎታል። በተለይ ተፈፅመዋል የተባሉትን ግድያዎች በዝርዝር የሚናገረው እና የሞቱ ሰዎች አስከሬን ያለበትን ቦታ አንድ በአንድ የሚመራው ‘ገሬ’ የተባለ ግለሰብ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊ መሆኑን በገሃድ አሳይቷል። ግልሰቡ ከፊት በኩል “ለካቲት 11” (ህወሓት የተመሠረተበትን ቀን የሚጠቁም) ከኋላ በኩል ደግሞ “ወይንቕንቕ” (የአሸባሪው ህወሓት አይበገሬነትን የሚገልጽ) ጽሑፍ ያለበትን ኮፊያ አድርጓል። ‘ገሬ’ ለበርካታ ዓመታት ኑሮውን በሱዳን ያደረገ የትግራይ ተወላጅ እና ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚሰደዱ የትግራይ ተወላጆችን የሚቀበል መሆኑን ጋዜጠኛ ኒማ ገልጻለች።

See also  ኤርትራ ለአማራ ልዩ ሃይልና ፋኖ ልዩ ድግፋና ወታደራዊ ስልጠና መስጠት እንደምትቀጥል አስታውቀች

ይህ ሰው ኑሮውን በሱዳን ካደረገ መቆዩቱን የምትገልጸው ጋዜጠኛዋ፣ “ሁመራ ውስጥ በኢትዮጵያ ወታደሮች እና አጋሮች ተፈፅሟል” ላለችው ግርፋት፣ ጅምላ እስር እና ግድያ ምስክር አድርጋ ያቀረበችበት አመክንዮ ለማንም ግልጽ አይደለም። ሌላኛው አስከሬን በጫነች ጀልባ ላይ ከጋዜጠኛዋ እና ሌሎች ምስክሮች ጋር የሚታየው ግለሰብ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂ መሆኑን ካደረገው ኮፊያ መረዳት ይቻላል።

ቀድሞውኑ መንግሥትን ለመፈረጅ የሌለ ምክንያት እየፈጠሩ ክሶችን የሚያቀርቡ ወገኖችን ሰብስቦ ለእንደዚህ ዓይነቱ ከፍተኛ ውንጀላ የተሞላበት ዘገባ በምስክርነት ማቅረብ የሲኤንኤንን አቅጣጫ አመላካች ነው። ሲኤንኤን እስካሁን በገለልተኛ አካል ያልተረጋገጠውን “የሁመራ ጭፍጨፋን” በተደጋጋሚ ሲያራግብ፣ የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጭምር እያጣራው ስለሚገኘው የማይካድራ ጭፍጨፋ እስካሁን ትኩረት ሲሰጠው አይታይም።

ከማይካድራ ጭፍጨፋ በተጨማሪ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በአፋር ክልል ጋሊኮማ ስደተኞች ጣቢያ ላይ ስለፈፀሙት አረመኔያዊ ድርጊት ትንፍሽ አላለም። በቅርቡ እንኳ በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ የተፈፀመውን እና ከ200 በላይ ሰዎች የተጨፈጨፉበትን ድርጊት በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲዘግቡት ሲኤንኤን ጉዳዬ አላለውም። በዚህ ሐቅን በረሳው ዘገባው ሲኤንኤን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳደር ሞክሯል። ነገር ግን ይህ ሙከራው ከአንድ ሚዲያ የሚጠበቀውን የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርን የጣሰ መሆኑን በግልጽ ያመላከተ ነው፡፡


Leave a Reply