አሸባሪው ቡድን ቤታቸውንና ንበረታቸውን ማውደሙ ተጨማሪ በግንባር ተጨማሪ ጉልበት- ሻምበል ደረጀ

አሸባሪው የህወሃት ቡድን መኖሪያ ቤቴን በማቃጠል የፈፀመው ግፍ ለሃገሬና ለህዝቤ የበለጠ እንድዋጋ አድርጎኛል ሲሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል ሻምበል ደረጀ ወልዴ ገለጹ።

ሻምበል ደረጀ ወልዴ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል ሲሆኑ ከ20 ዓመት በላይ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቁ፣ ሰብሉን ሲሰበስቡ፣ ከሚያገኙት የወር ደመወዝ በመቀነስም መንገድ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን ሲገነቡ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ቀደም ሲል በህግ ማስከበር፣ አሁን ላይ ደግሞ በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ የሚገኙት ሻምበል ደረጀ፤ ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና የሌለውና ሀገር በማፍረስ ስራ የተጠመደው የህወሓት የሽብር ቡድን ህብረተሰቡ በሰላም ውሎ በሰላም እንዳያድር በርካታ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ይናገራሉ።

የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ያስረዱት ሻምበል ደረጀ፤ ከሰሞኑ በአፋር ግንባር በህልውና ዘመቻው ላይ እያሉ አሸባሪ ቡድን በጉና በጌምድር ወረዳ ክምር ድንጋይ ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤታቸውን ከነሙሉ ንብረቱ በእሳት በማቃጠል እንዲወድም አድርጓል።

“በቤተሰባቸው ላይ የተፈፀመው ሰይጣናዊ ድርጊት የሽብር ቡድኑን እስከመጨረሻው በመደምሰስ ለሀገሬና ለህዝቤ ጠንክሬ እንድዋጋ ያደርገኛል እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሰኝ አይደለም″ ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ”እኔ ላይ ስነ ልቦናዊ ጫና ለማሳደር አስቦ ዘግናኝ ግፍ ቢፈፅምም የአካባቢው ህዝብ ተባብሮ በቤተሰቦቼ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥግ አስይዞ አቆይቶልኛል” ብለዋል።

በአፋር ክልል በተደረገው ውጊያ በአንድ ቀን ሁለት ጠንካራ ምሽጎችን ከጠላት በማስለቀቅና በመማረክ ጀብድ እንደሰሩም ተናግረዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ሀገር የማፍረስ ዕኩይ ሴራ በመላ ኢትዮጵያዊያን ትብብርና ጠንካራ ክንድ መቼም ቢሆን እንደማይሳካለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለህልውና ዘመቻው የጀመረውን ድጋፍ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል። ወጣቱ ሀገር አፍራሸ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትና ጠንካራ ደጀን ለመሆን መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ባህር ዳር፣ መስከረም 5/2014 (ኢዜአ)

Leave a Reply