በአዲስ አበባ ከደረጃ በታች የሆኑ 11 ትምህርት ቤቶች እውቅና ተሰረዘ!

የአዲስ አበባ የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ከደረጃ በታች ናቸው ያላቸውን የ11 ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፍቃድ መሰረዙን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በከተማዋ የሚገኙ 672 ነባር እና 51 አዲስ ትምህርት ቤቶች ተመዝነው ለሚቀጥለው ዓመት ማሻሻያ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው 61 ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ስራ አስኪያጇ ባለፈው ዓመት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው 65 ትምህርት ቤቶች 60ዎቹ በተደረገ ክትትል የደረጃ ማሻሻል በማድረጋቸው የእውቅና ፈቃድ እንደተሰጣቸው አንስተዋል፡፡ምንም አይነት ማስተካከያና ማሻሻያ ያላደረጉ 5፣ ዘንድሮ በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መስፈርቱን ያላሟሉ 6 ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፍቃዳቸው መሰረዙን አስታውቀዋል፡፡

ፍቃዳቸው ከተሰረዘው መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ሱፐር ኪድስ፣ ኢንዱራንስ አዲስ፣ ኤልሻዳይ ወረዳ 12፣ ጵሾን ወረዳ 9፣ ቪካስ እና ሮሆቦት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሀሞና እና እመሙዝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማም ሁንዴ ጉዲና የመጀመሪያ ደረጃ እና ማይ ፊፍ ቅድመ መደበኛ እንዲሁም ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አዶናይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንደሚገኙበት አብራርተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

See also  ቻይና ለኢትዮጵያ ያበረከተችው 300 ሺህ ዶዝ ሲኖፋርም የኮቪድ-19 ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ ገባ

Leave a Reply