አብይ አህመድ ” ሁሉንም ታሪክ ይመዘግበዋል” ሲሉ ለጆ ባይደን ደብዳቤ ላኩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የሽብር ቡድኑን የሸር ተግባራት እና የአገራቸውን አቋም የሚያንጸባርቅ ግልጽ ደብዳቤ መላካቸውን በግል የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በደብዳቤያቸው፤ “ይህን ግልጽ ደብዳቤ እየጻፍኩ ባለሁበት ወቅት እንኳ የሽብር ቡድኑ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ባደረሰው ጥቃት ሴቶች፣ ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፣ ኑሯቸው ተናግቷል፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው ተገድለዋል፣ የግል ንብረታቸው እና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሆን ተብሎ በሽብር ቡድኑ እንዲወድሙ ተደርጓል” ብለዋል፡፡

“ይህን ግልጽ ደብዳቤ በምልክበት በዚህ ወቅት የሽብር ቡድኑ የትግራይ ልጆቻችንን እና ህዝባችንን ሆን ብሎ የጦር መጠቀሚያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡

“የትግራይ ህዝብ ቀደም ሲል ከደርግ መንግስት ጋር በነበረ ጦርነት ቀጥሎም ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት ለበርካታ ችግሮች የተጋለጠ ህዝብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ይህ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት የትግራይ ህጻናት እና አጠቃላይ ህዝቡ ሰላም እንደሚያገኙ ከፍተኛ ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡

“በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የትግራይ ህጻናት እኩዮች ትምህርት ለመጀመር በጉጉት እየተጠባባቁ ሲሆን በትግራይ ክልል የሚገኙ ህጻናቶቻችን ግን በሽብር ቡድኑ ዕኩይ ተግባራት ምክንያት ለዚህ አልታደሉም” ብለዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ላይ ሌላው ያነሱት ነጥብ ጥቅምት ወር ላይ የሽብር ቡድኑ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት እና ህግ ለማስከበር በተደረገ ጥረት ውስጥ በርካቶች ለችግር መዳረጋቸውን እና የሽብር ቡድኑ ህጻናትን እና ሌሎች ሲቪል ሰዎችን በግድ ወደ ጦርነት እያሰለፈ እንደሆነ አንስተው ይህም በዓለም አቀፍ ህግጋት በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

“የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ የሽብር ቡድኑን ንጹሃንን የማፈናቀል እና ለከፋ ችግር የመዳረግ ዕኩይ ተግባራት እየተመለከተ ዝምታን በመምረጡ የጀመረውን የሽብር ተግባራት በአማራ እና አፋር ክልሎች በማስቀጠል ለበርካታ ህጻናት እና ሴቶች እንባ መፍሰስ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

“መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ለማመቻቸት እንዲሁም ሁኔታዎች ወደ መልካም እንዲቀየሩ ያደረገውን ጥረት ሁሉ በአዎናተዊ ያልተቀበለው እና በጀመረው ዕኩይ ተግባሩ ሲቀጥል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚፈጸሙ ጥፋቶችን ሁሉ በመንግስት ላይ እያላከከ በመቀጠሉ ምክንያት የሽብር ቡድኑ በጀመረው ህገ-ወጥነት እንዲቀጥል ዕድል ሰጥቶታል፡፡

“ኢትዮጵያ የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁማ የመልማት አቅም ካላቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስለመሆኗ ያለፉት ወራት አፈጻጸሞቻችን ምስክር ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በትግራይ ክልል በተከናወነው የህግ-ማስከበር ስራን ዓላማ በማዛባት እና ትክክል ያልሆነ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እየተደረገ ያለው ጥረት፣ ለማሳደር የሚሞከረው ጫና፣ በሁለት ቢለዋ የሚበላ መንግስት አድርጎ ለመሳል የሚደረገው ጥረት መሬት ካለው እውነታ ጋር የሚገናኝ አይደለም” ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በአካባቢያዊ ጸጥታ ጉዳዮች እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የረጅም ጊዜ ወዳጆች እና አጋር አገራት እንደመሆናቸው መጠን አሁን ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ አሜሪካ እያራመደች ያለው ፖሊሲ ከአገሬ ፍላጎት ጋር የሚቃረን ከመሆኑም በተጨማሪ ለዚህች ታላቅ አገር ትንግርት ከመሆኑም ባለፈ ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብት ጉዳይነት ያለፈ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡“የሽብር ቡድኑ አገሪቱን ባስተዳደረባቸው ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጸሙ በነበሩ የሰብዓዊ መብት እንዲሁም የሲቪል እና የፖለቲካዊ መብት ጥሰቶች በከፍተኛ ትወቀስ እንደነበር አስታውሰው በትግራይ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ የተለያየ ማንነት ያላቸቀው በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለጥቂቶች የፖለቲካ ስልጣን ማስጠበቅ ሲባል መብቶቻቸው ተጨፍልቆ ቆይቷል።

“በዚህም በሰብኣዊ መብት አያያዝ ዙሪያ፣ ነዋሪዎችን ከቀያቸው የማፈናቀል፣ የመንግስት ስልጣንን እና የመንግስት ተቋማትን የጥቂት ግለሰቦች መጠቀሚያ ከማድረግ ጀምሮ የአገሪቱን ሀብት ጥቂቶች ሲመዘብሩት ቢቆዩም ላለፉት 27 ዓመታት ተጠያቂነት ሳይሰፍን በቆዩባቸው ዓመታት አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት በዚህ ረገድ ምንም ሲሉ አልተደመጡም፡፡

“እኤአ ከ2015 እስከ 2018 በነበሩት ዓመታት ውስጥ በህወሃት አስተዳደር ዘመን በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች የተንገፈገፈው ህዝብ ብሶቱን በግልጽ ያወጣባቸው ዓመታት ነበሩ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ “የሽብር ቡድኑ ስልጣኑን ለማራዘም ሲጠቀምባቸው ከነበሩ ስልቶች መካከል አንዱ አንደኛውን ብሔረሰብ ከሌላው ጋር ማጋጨት እኔ ወደ ስጣን በመጣሁበት ወቅትም መልካቸውን በመቀየር አንዴ አንዱን ብሔረሰብ ተጨቁነሃል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በገንዘብ በመደገፍ ጭምር ቀጥሎበት ነበር” ሲሉ አስገንዝበዋል።

አሁን ላይ ደግሞ ይህ የሽብር ቡድን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተማሟጋቾችን እና የዲሞክራሲ ተቋማትን በመጠቀም ለራሱ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሊጠቀምባቸው እና የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ ያላትን አገር ሊበትን እየጣረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

“አሁን ላይ በምዕራብ አገራት ፖሊሲ አውጪዎች፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢነት ድርጅት ስም እንዲሁም በዴሞክራሲ በልጽገናል በሚሉ አካላት በሙሉ እንዲሁም በሽብር ቡድኑ አቀናባሪነት በአገራችን ላይ እየሆነ ያለውን ሁሉ ታሪክ ይመዘግበዋል” ብለዋል፡፡

ውስን ችግሮች የነበሩበት እና ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያ በቀጣይ እንዲገነባ ለሚፈልጉት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የጣለ ለዚህም ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ያሳዩበት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነጻ፣ ግልጽና ሰላማዊ አገራዊ ምርጫ ማከናወኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ምርጫ ላይ ለአርባ ሚሊዮን ትንሽ ፈር የቀረው ህዝብ ወጥቶ ድምጽ መስጠቱን አንስተዋል፡፡   

በዚህም ቀደም ሲል ከተካሄዱት ምርጫዎች በብዙ መልኩ ልዩ የሆነ እና ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ የተቻለው አስቀድሞ በምርጫ አስፈጻሚ ተቋማችን ነጻነት ላይ ጠንካራ ስራ በመሰራቱ እንደሆነ አስታውሰው፤ አስቀድሞ በተለያዩ አካላት ምርጫው ውጤታማ እንደማይሆን ሲተነብዩ የነበሩ አካላትን አፍ ማስዘጋቱንም ጠቅሰዋል፡፡

“ህዝቡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የብልጽግና ፓርቲ አገሪቱን እንዲመራ ድምጽ ሰጥቶታል፤ በዚህም መሰረት አሁን በሽብር ቡድኑ እየተሰነዘሩ ያሉትን ጥፋቶች ቀልብሰን ለህዝቡ የሚመጥነውን ክብር፣ ሰላም እና ልማት ለማምጣት ጠንክረን እንሰራለን፡፡

“በቀጣይም የአገራት፣ የአህጉር እና የዓለም ደህንነት አሜሪካ ከበርካታ የዓለም አገራት ጋር የምትሰራባቸው እና ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብርባቸው ማጠንጠኛዎች ሆነው እንደሚቀጥሉ አምናለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ አሜሪካ ይህን የሽብር ቡድን እኤአ በ1980 በሽርተኝነት መዝገቧ ላይ ማስፈሯን አስታውሰዋል።

“አገራችንንም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለማወክ ከተነሳ የሽብር ቡድን ጎን ለመሰለፍ ለምን እንደመረጠ ግልጽ አይደለም” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ አልሸባብ የተባለውን የሽብር ቡድን ለማጥፋት በምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ በዋና አጋርነት ተሰልፋ የቆች እና አሁንም የሆነች መሆኑን አስታውሰው፤ “ይህ የሽብር ቡድን አገራችንን እና አካባቢውን ለማወክ የሚያደርገውን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በምናደርገው የመከላከል ተግባር ሁሉ አሜሪካ ከጎናችን ትቆማለች ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡  

የአሜሪካ መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማስፋፋት በሚል ማዕቀፍ በሌሎች አገራት ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት የአሜሪካ ህዝብ እንደሚደግፈው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የዲሞክራሲ ስርዓትን ባህልና ታሪክን በተፈጥሮ የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለማጎልበት ጠንካራ ስራ መስራት ጀምራለች” ብለዋል፡፡

“ምንም እንኳን ሁሌም ታሪክ እውነታን ሳይደብቅ የሆነ ጊዜ እንደሚወጣው ባምንም አሁን ላይ የአሜሪካ ህዝብ እና የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ባለፉት ጥቂት ወራት በተሳሳቱ በዓለም አቀፍ ዘገባዎች፣ ሪፖርቶች፣ ትርክቶች እና ሆን ተብለው በተዛቡ መረጃዎች ኢትዮጵያን እና መሰል አገራትን በተመለከተ የተሳሳተ ምስል እንዲኖራቸው ተደርጓል” ብለዋል፡፡

Leave a Reply