ሕዝብ ለመንግስት ስንተኛ ልጁ ነው?

“ሕዝብ ምንድነው” ቢሉት
“ቢገደል ቢገዱል የማያልቅ”
እንዳለው ደራሲው፡፡

By ኤልያስ ሽታኹን
(ዝብርቅርቅ)

መጀመሪያ አፈታሪክህን ይነጥቁሀል

ለጥቆ ታሪክህን
ለጥቆ አፍህን….
በመጨረሻ
አፍ የሌለው ታሪክ::
ወይም
ታሪክ የሌለው አፍ::

እንመለስ
ሕዝብ ለመንግሥት ስንተኛ ልጁ ነው?

መንግሥት የሚለው ቃል በምድር ላይ ብቻ የሚቆም ፅንሰ-ሀሳብ አይደለም፡፡ በሰማይ እወዲያኛውም ዓለም የፈጣሪ መንግሥት እንዳለ ሀይማኖት የመሰከረው መፅሀፍ ያጠነከረው ሀቅ ነው፡፡ “…መንግሥትህም ትምጣ ….” እያልን እንፀልይ የለ፡፡
(ያኛው መንግሥት ግን የማይወጣ የማይወርድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡)

ነገሩን ስናደምቀው…….
መንግሥት የሚለውን ቃል ስንሰማ የአፍሪቃ ወጣቶች ላይ የሚመጣው ምስል አንድ አይነት ነው፡፡ምስሉ ካየነው ከሰማነው አይደል የሚቀዳው፡፡

አንዳንዶች
“የአፍሪቃ ጨለማነት ከራሳቸው ከተወላጆቹ አፍሪቃውያን ይመነጫል” ባይ ናቸው፡፡
አንዳንዶች ደግሞ
“የአፍሪቃ ወድቆ መቅረት የተጠና የተሰላ የታሰበበት በዘመን ሂደት የተደገሰበት ነው” ብለው ይናገራሉ፡፡ ብቻ ወዲህም አልን ወዲያ የአህጉሪቱ የመከራ ስንክሳር ዛሬም ያልተቋጨ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ጦርነት ያደገችበት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡
አብዛኞቹ የሰላም ኖቤል እንጂ የትምህርት የዕውቀት ኖቤል አለመውሰዳችንም የሚነግረን ሀቅ በተቃራኒው ሰላም አልባ መሆናችንን ነው፡፡ (ነገር ግን በስነፅሁፉም እነ ነጂብ መሀፉዝን ሳንረሳ ማለት ነው፡፡)

ወደ መሬት ስናወርደው…..
የአፍሪቃ የሥነ መንግሥት ጉዳይ በእንቶፈንቶ የተሞላ ነው፡፡
“ከአፍሪቃ ቤተ-መንግሥቶች የአስተዋይ ባልቴቶች ማጀት የተሻለ ነው፡፡”
የሰው ዘር ምንጭ አፍሪቃ ለሰው የማትመች ሆናለች፡፡
ፖለቲካዋ ከሀይማኖቷ ሀይማኖቷ ከተፈጥሮ ሀብቷ የተፈጥሮ ሀብቷ ከሙስናዋ ተደበላልቆባት መስማትም ማየትም መናገርም የማትችል መሬት ከሆነች ሰነበተች፡፡

እንዲያውም…
በቀለ ተገኝ መኮንን በተረጎሙት የምዕራባውያን ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ(፩)
መጽሐፍ ላይ የሁለቱን ትዳር በዚህ መልክ ይተርኩታል፡፡
“….የግብፁ ንጉሥ ለሞላው የሀገሪቱ መሬት ባለቤት ነበረ፡፡ ሥርዓተ አምልኮቱ ለብዙኃን አማልክት(ጣዖታት)የሚሰገድበት ሆኖ በተለይ ከንጉሡ ጋር በቅርብ ይዛመዳል የሚባል አንድ የአማልክት አምላክ ነበረ፡፡ በሀገር አገዛዝና በሕዝብ አስተዳደር ረገድ ከወታደራዊ ምስፍና ጎንልጎን የቀሳውስት ምስፍናም ነበረ፡፡
በተለይም ቀሳውስቱ መሳፍንት የንጉሡ ጉልበት ደከም ሲል ወይም በአጣዳፊ ጦርነት ሲጠመድ የነጋሤ መንግሥቱን ሥልጣን ለመቀናቀን የሚያስችል ብርታት ነበራቸው፡፡ ጫካውን መንጥሮና ጠፍ መሬቱን አልምቶ ከዓመት ዓመት ላበቱን እያንጠፈጠፈ በእርሻ የሚተዳደረው ሀገረሰብ ንጉሡና ለበታቾቹ መሳፍንት ማለትም ለጦር አበጋዞች ለቀሳውስቱ መሳፍንት ከቤት አገልጋይ ከባሪያ ያልተሻለ ገባር ሆኖ በችጋር ሲፈናጠር ይኖር ነበር::”

See also  ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ስንዴ እንድትልክ የሚያስችል ስምምነት ተደረሰ

ወገን የማታውቁትን አይደለም የምነግራችሁ፡፡ የረሳችሁትን አልያም ለምዳችሁ የናቃችሁትን እንጂ፡፡ የሆነ ጊዜ ባነበብኩት ጥናት የአፍሪቃ መከራ አምጪ መሪዎች መሀል 70 በመቶ የሚሆኑት የሽግግር ነን ብለው ስልጣኑን የተቆናጠጡ ናቸው፡፡

 • ( ስልጣን መቆናጠጥ የሚለው አገላለፅ ይደንቃል፡፡ መቆናጠጥ ማለት አንድን ነገር መያዝ በሚችሉበት አካል ሁሉ ወጥሮ መሰብሰብ በእጅ መዳፍ ውስጥ ማስገባት እንደማለት ነው፡፡ ምንም ቀዳዳ አይገኝበትም፡፡ መቆናጠጥ ነዋ፡፡ ከዛ ሕዝብን ወደ መቆን….ይገባል እንደማለት ነው፡፡)
  ከቀደመው ያየነውም ይሄንኑ ነው፡፡

ሀገረ ኡጋንዳን ከቀኝግዛት መሪዎች የተረከባት ሌላኛው ተወላጅ ቀኝ ቀዢዋ ኢዲ አሚን ዳዳ የሽግግር መንግስት የመከራ ምንጭነት ምስክር ነው፡፡

 • ኢዲ አሚን 1916 ወይም 1918 እንደተወለደ ይነገርለታል፡፡ የቀን ስራ እየሰራ በእናቱ ቤት ያደገው ኢዲ አሚን ከ4 ክፍል የዘለለ የአስኳላ ታሪክ የለውም፡፡ በእንግሊዝ ጦር ውስጥ ወጥ ቤት በመሆን ተቀጥሮም አገልግሏል፡፡ በዚህ የአግልግሎት ዘመኑ ነው እንግዲህ ከ10 አለቅነት እስከ ጀነራልነት የደረሰው፡፡
  “ሙሉ ስሜም ‘ክቡር ጀነራል ፊልድ ማርሻል የጆግራፊ ፕሮፌሰር ሀጅ የኡጋንዳ የምንግዜም ፕሬዘዳንት ኢዲ አሚን ዳዳ’ ነው” አለ፡፡ይሄ ስም እና ማዕረግ ያጎደለ ሰው ከህይወት ድጎድላል፡፡
  ኢዲ አሚን ከ1963-1971 ዓ.ም ኡጋንዳን ገዛ፡፡

ሰውየው ለአንድ ሳምንት ላሸጋግራችሁ መጣሁ አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ በዚህ ሳምንት የሀገሪቱን ስር መሰረት የሚሆኑ ተቋማትን እንፈጥራለን አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ዲሞክራሲያዊ ነፃ ምርጫ እናደርጋለን አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ ከዚህ ቡኃላ ጥጋብ ነው አለ፡፡ ሰላም ነው አለ፡፡ እድገት ነው አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን አሉ፡፡ ጊዜ እና ሰይጣን ለኢድያሚን ምን ሹክ እንዳሉት አይታወቅም፡፡
በሳምንቱ በቀጥታ ስርጭት ” ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኡጋንዳ መሪ እኔ ነኝ፡፡ የማይከሰስ መሪ የማይታረስን መሬት ይዣለሁ፡፡ የኡጋንዳ የዘላለም ንጉስ በሚል ተቀጥላ ጥሩኝ፡፡ ” አለ፡፡ አለ፡፡ ኡጋንዳውያን አሜን ጠፋባቸው፡፡
ክፋ መሪ አሜንህንም ያጠፋብሀል፡፡ ለያዥ ለገናዥ የከበደ ዘመን አሳለፉ፡፡ በየአቅጣጫው የሚነሳውን ግርግር እያስታከከ የመቃብር መሬት እስኪጠብ ወጣቶችን በወጡበት አስቀራቸው፡፡ ፀጥ ለጥ ቀጥ አደርጎ አንቀጥቅጦ ገዛ፡፡ ሽግግር ያለው ስርአት ሺ’ ግርግር ወለደ፡፡
ልክ እንዲሁም ከንጉሳዊው ስርዓት ወደ ሌላ ንጉሳዊ ስርዓት(ደርግን ማለቴ ነው) የተሸጋገርንበት የ66ቱ አብዮትም ርዕሱ ሽግግር ነው፡፡
ውስጠ ታሪኩ ግን ግርግር ነው፡፡

See also  ምንም ሳያርፍ 13,560 k.m የበረረው ወፍ የአለም ሪከርድ ሰበረ

ሌላ መሬት ስናወርደው…..
በሀገረ ጦቢያም :- የሽግግር መንግስት ..የምርጫ መራዘም… የህገ-መንግስት መጣስ….የመገንጠል ድፍረት….ሌላም ሌላም ሲባል ሰማሁ፡፡ ሰማን፡፡ ይህ ሀሉ ነገር ሲፈተፈት “ህዝብ” የሚባል ክቡር ክቡድ ነገር የት ተጥሎ ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ምሁር እና ፖለቲከኞቻችን ለህዝብ ያላቸውን ንቀት በስድብ መግለፁን አቁመዋል፡፡ ተመስገን፡፡ አሁን ንቀቱን ጭራሹን ህዝቡን በመርሳት መግለፅ ጀምረዋል፡፡ የተረሳ ህዝብ ለመታወስ ሲል ድንጋይ መወርወር ግድ የሆነባት አህጉረ አፍሪቃ ነገሯ ግራ ነው፡፡ ከሁሉም ገራሚው ነገር ከታሪክ ያልተማሩ ነገር ግን ታሪክ በየካምፓሱ የሚያስተምሩ ሰዎች እንደማየት ምን ያስደነግጣል፡፡

ወገን ቁማሩ የተበላ ቢመስልም፡፡ የትኛውም ፖርቲ ደጋፊ ባልሆንም የኢትዮጵያ ምንነት እና ማንነት ግን ደጋፊ ነኝ፡፡ ምንነቷን ከማንነቷ የሚነጠሉትን ሁሉ ነጥዬ ማየት እችልበታለሁ፡፡ መብትም ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅለቱን ታዘቡልኝ፡፡

ህገመንግሰቱ ላይ ቤተ-መንግስቱ ላይ በየቀኑ ስንተነትን መዋላችን አጀብ ነው፡፡ በዚህ 50 አመታት ውስጥ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መተቸት ቀሏል፡፡ ፖለቲካውም ቀሏልና፡፡ ህገ መንግስቱን እኔም እኩዮቼም እንተቸዋለን፡፡
አስቅኙ ነገር ህገ-መንግስቱ 1987 ዓ.ም ሲፀድቅ እኔ እናቴ ሆድ ውስጥ ነበርኩ፡፡
በኔ የሚተች በወጣቶች የሚነቀፍ ቀሊል አውድ ሆኖ መቅረቱ የየዕለት ትዝብታችን፡፡ ስለዚህ ለከበረችው ሀገር የከበረ ሀሳብ እንፍጠር፡፡
እንደነ አክሊሉ ሀበተወልድ የነጠረ የጠጠረ ሀሳብ እናምጣ ወይ ለሚችሉት ትተን እንውጣ፡፡
ወገን…
ወደ ከባዱ ግን ወደ ትክክሉ ፖለቲካ መሄድ ድልም እድልም ይጠይቃል፡፡

ሕዝብ ለመንግሥት ስንተኛ ልጁ ነው?
ሕዝብ ለመንግሥት ምኑ ነው? ቁጥሩ? ስታስቲክሱ?መራጩ?ምንጩ? ምኑ ነው?

በዕውቀት ሰበብ
እምነትህን=አፈታሪክ
አፈታሪክ=ተረት
ተረት=የላም በረት ብለህ አናንቀህ መጨረሻ የሚያስጠልልህ ታጣለህ?
እንዳትመለስ ወደየት?

በመጨረሻ

 • “ሕዝብ ምንድነው” ቢሉት
  “ቢገደል ቢገዱል የማያልቅ”
  እንዳለው ደራሲው፡፡

በመጨረሻ

 • “ንጉሥ ተክለጊዎርጊስ ሦስት ዓመት ገዙ፡፡ አልነገሡም፡፡”
  መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ

መግዛት ሌላ መንገሥ ሌላ፡፡

Leave a Reply