የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት ጀመረ

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ”ፒ ኤስ ኤ ሜድካል” ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት ጀመረ።

በግል ባለሀብት የተገነባው ይሄው  ፋብሪካ አሁን ላይ ባለው አቅም በቀን 120 ሲሊንደር ኦክስጅን የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ለ30 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል።

ፋብሪካው አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ኦክስጅን ሀፕ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር  በመተባበር የተገነባ ነው።

በፋብሪካው ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ፤ “በሀገራችን የኮሮና ቫይረስ  ወረርሽኝ በሽታን ተከትሎ የጤና ኦክስጅን ፍላጎት እያደገ መጥቷል” ነው ያሉት።

በሃገሪቱ  በቀን 3 ሺህ 127 ሲሊኒደር ኦክስጅን የሚያመርቱ ድርጅቶች ቢኖሩም የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ በደንገተኛ አደጋና በኮሮና ምክንያት ኦክስጅን ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጋር የሚጣጣም ሆኖ አለመገኘቱን ገልጸዋል።

የዚህ ፋብሪካ ወደ ስራ መግባትም የአቅርቦት ክፍተቱን ለመሙላት ከማገዝ ሌላ ሀገሪቱ ለኦክስጂን አቅርቦት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማሰቀረት ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የጤና ዘርፉን ለሚያግዙ በተለይም አሁን ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና  ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን፣ ኦክስጅንና ሌሎች ተዘማጅ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማምረት ለሚሰሩ ሀገር በቀልና የውጭ ሀገር ድርጅቶች ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ስራ ሲጀምሩ ቴክኖለጂን በመቅዳትና በማላመድ ወጣት ተመራማሪዎች ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መንግስት አዳዲስ ቴክኖሎጅን ለሚያቀርቡና ለሚያፈልቁ ተመራማሪዎች በልዩ ሁኔታ እንደሚደግፍም አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ እንዳሉት፤ በዞኑ በሚገኙ የህክምና ተቋማት የኦክስጂን አቅርቦት እጥረት ነበር።

በህክምና ተቋማት ለሚታከሙና ኦክስጅን ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ፈውስ ለመስጠት ከአዲስ አበባ፣ ደሴና አዳማ በማምጣት ችግሩን ለመቋቋም ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

የደብረ ብርሃን  ሆስፒታል ብቻ በቀን 80 ሲሊንደር ኦክስጅን በማስመጣት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚያወጣም ጠቅሰዋል።

የዚህ ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ በከተማው መገንባቱም እንግልትና  የሀብት ብክነትን ከማስቀረቱም ባለፈ ለህሙማን በቂ ኦክስጅን በሰዓቱ ለማቅረብ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በዞኑ አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለሚገነቡ ባለሃብቶችም ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል ዋና አስተዳደሪው።

የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የባለሃብቶችና የመንግስት ያልተቋረጠ ትብብር ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኪያ ሜድ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ማህደረ ዝቁ ናቸው።  

ኮሌጁ  ”ፒ ኤስ ኤ ሜድካል ” ለኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ 30 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የ10 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ ባለው አቅም በቀን 120 ሲሊንደር ኦክስጅን የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ 30 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

ፋብሪካው ኮሌጁ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ኦክስጅን ሀፕ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆ ድርጅት ጋር  በመተባበር የተገነባ እንደሆነም አመልክተዋል።

በምርቃ ስነ ስርዓት ላይ  ከፌደራል፣ ክልልና  ዞን የተውጣጡ የመንግስት ስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ተገኝተዋል። 

ENA

Leave a Reply